መጽሐፈ ኢዮብ 18
18
ቤልዳድ
1ሹሐዊው ቢልዳድም እንዲህ ሲል መለሰ፦
2“ኢዮብ ሆይ! ለምን እንደዚህ ንግግር ታበዛለህ?
እስቲ አድምጥ፤ እኛም እንናገር።
3ስለምን አንተ እኛን እንደ እንስሶች ትቈጥረናለህ?
ለምንስ እንደ ደንቆሮዎች የማናስተውል አድርገህ ትመለከተናለህ?
4አንተ ብትቈጣ ራስህን ትጐዳለህ እንጂ
በአንተ ቊጣ ምድር ባዶ አትሆንም።
አለቶችም ከስፍራቸው አይነቃነቁም።
5“የኃጢአተኛ መብራት ይጠፋል፤
የእሳቱም ነበልባል ዳግመኛ አይታይም።
6በእርሱ ድንኳን ውስጥ ያለው መብራት ይጠፋል፤
ብርሃኑም ይጨልማል። #ኢዮብ 21፥17።
7የብርቱ ዕርምጃው ርዝመት እያጠረ ይሄዳል፤
የራሱም የተንኰል ዕቅድ ይጥለዋል።
8በገዛ ራሱ እርምጃ አሽክላ ውስጥ ይገባል፤
እግሩም በመረቡ ውስጥ ይተበተባል።
9አሽክላ ተረከዙን ይይዘዋል፤
ወጥመድም አጣብቆ ያስቀረዋል።
10በመሬት ላይ የሸምቀቆ ገመድ ተዘርግቶለታል፤
በመንገዱም ወጥመድ ተዘጋጅቶአል።
11“ፍርሀት በዙሪያው ከቦታል፤
በኋላው እየተከተለም ያሳድደዋል።
12ኀይሉ በራብ አልቆአል፤
ቀጠናም እርሱን ሊያጠፋው ተዘጋጅቶአል።
13በሽታ ሰውነቱን ያመነምነዋል፤
ሞትም ጨርሶ ይረከበዋል።
14ያለ ስጋት ተማምኖ ከሚኖርበት ቤት ይባረራል፤
የሰው ሁሉ ገዢ ወደ ሆነው ወደ ሞት ይወሰዳል።
15በቤቱ ውስጥ ምንም ነገር አይቀርለትም፤
በመኖሪያውም ውስጥ ዲን ይበተናል።
16ሥሩ ከመሠረቱ እንደሚደርቅና
ቅርንጫፎቹም እንደሚረግፉ ዛፍ ይሆናል።
17በምድር ላይ የሚያስታውሰው አይኖርም።
ዝናውም ከምድር ይጠፋል።
18ከብርሃን ወደ ጨለማ ይባረራል፤
ከሕያዋን ምድርም ይወገዳል።
19በወገኖቹ መካከል ለእርሱ ተተኪ የሚሆን ትውልድ አይገኝለትም፤
በመኖሪያውም ዘር አይተርፍለትም።
20የምዕራብና የምሥራቅ ሰዎች በእርሱ ላይ በደረሰው መከራ
እጅግ ፈርተው ተንቀጠቀጡ።
21ምን ጊዜም የክፉ ሰዎች መጨረሻ ይኸው ነው፤
እግዚአብሔርንም የማይፈሩ ሰዎች ዕድል ፈንታቸው ይህ ነው።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 18: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997