መጽሐፈ ኢዮብ 20
20
ጾፋር
1ናዕማታዊው ጾፋርም እንዲህ ሲል መለሰ፦
2“ኢዮብ ሆይ! የሕሊናዬ ብስጭት መልስ እንድሰጥህ አስገደደኝ፤
ስለዚህም ነው ለመናገር የቸኰልኩት።
3የምሰማው እኔን የሚያዋርድ ተግሣጽ ነው፤
የማስተዋል ችሎታዬ መልስ እንድሰጥ ይመራኛል።
4“ሰው በምድር ላይ ከተገኘበት ጊዜ ጀምሮ
ከጥንት እንደዚህ እንደ ሆነ ታውቃለህ።
5የክፉ ሰው ድንፋታ ለአጭር ጊዜ ነው፤
እግዚአብሔርንም የሚክዱ ሰዎች ደስታቸው በቅጽበት የሚጠፋ ነው።
6ክፉ ሰው ምንም እንኳ በትዕቢቱ እስከ ሰማይ ከፍ ቢልም
ዐናቱም ደመናን ቢነካ
7እርሱ እንደ ራሱ ኩስ በፍጹም ይጠረጋል፤
ያዩት የነበሩ ሰዎችም ወዴት ነው? ይላሉ።
8እንደ ሕልም ብን ብሎ ስለሚጠፋ አይገኝም፤
እንደ ሌሊት ራእይም ይጠፋል።
9ከሚኖርበት ቦታ ደብዛው ስለሚጠፋ፥
አንድ ጊዜ የተመለከተው ሰው ዳግመኛ አያየውም።
10ልጆቹ እየተለማመጡ
አባታቸው ከድኾች በግፍ የቀማውን ገንዘብ ይከፍላሉ።
11ኀይል የተሞላው የወጣትነት ሰውነቱ
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዐፈር ይሆናል።
12“ምንም እንኳ ክፋት በአፉ ውስጥ እንደ ምግብ ቢጣፍጠው፥
በምላሱ ቢያጣጥመው፥
13እንዳያልቅበትም በአፉ ይዞ
እያላመጠ ቢያቈየውም፥
14በሆዱ ውስጥ ግን ወደ መራራነት ይለወጣል፤
እንደ እባብ መርዝም ይሆንበታል።
15ክፉ ሰው የበላውን ሀብት በግዱ ይመልሳል፤
በሆዱ ውስጥ ያለውንም ሁሉ እግዚአብሔር ያስተፋዋል።
16ክፉ ሰው የሚበላው ሁሉ መርዝ ይሆንበታል፤
መርዝም ሆኖ ይገድለዋል።
17የወይራ ዘይት እንደ ጐርፍ ሲወርድ፥
ማርና ወተት እንደ ጅረት ውሃ ሲፈስ ሳያይ ይሞታል።
18የድካሙን ፍሬ መልሶ ያስረክባል እንጂ አይበላም፤
ነግዶ ባተረፈውም ሀብት አይደሰትበትም።
19ይህም የሚሆነው ድኻን ስለ ጨቈነና
ያልሠራውንም ቤት በግፍ ስለ ወሰደ ነው።
20ስግብግብነቱ ዕረፍት ነሥቶታል፤
ያካበተው ሀብትም ሊያድነው አይችልም።
21ሀብቱ ሁሉ ተሟጦ ስለሚያልቅ
የሚቀምሰው ነገር አያገኝም።
22ምንም እንኳ ሀብታም ቢሆን ብስጭት ይደርስበታል፤
ብዙ ችግርም ያጋጥመዋል።
23በልቼ እጠግባለሁ ሲል እግዚአብሔር ኀይለኛ ቊጣውን ያወርድበታል።
መዓቱንም በእርሱ ላይ ያዘንብበታል።
24ከብረት ሰይፍ ቢያመልጥ
በነሐስ ፍላጻ ይወጋል፤
25ፍላጻውም ዘልቆ በስተጀርባው ይወጣል፤
የሚያብለጨልጨው ጫፉ ጒበቱን በጣጥሶ ያልፋል፤
በታላቅ ፍርሀትም ልቡ ይሸበራል።
26ያካበተው ንብረት ሁሉ ጥቅጥቅ ባለ ጨለማ ውስጥ ይወድማል፤
በሰው እጅ ያልተቀጣጠለ እሳትም ያቃጥለዋል፤
በቤቱ ውስጥ የሚተርፈውን ንብረት ሁሉ ያጋየዋል።
27የሠራውን ኃጢአት ሰማይ ሁሉ ይገልጥበታል፤
ምድርም በጠላትነት ትነሣበታለች።
28በእግዚአብሔርም የቊጣ ቀን
የቤቱ ንብረት ሁሉ በጐርፍ ተጠራርጎ ይወሰዳል።
29እግዚአብሔር ለዐመፀኞች የወሰነላቸው ዕድል ፈንታ፥
የክፉ ሰዎች ዋጋ ይኸው ነው።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 20: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997