መጽሐፈ ኢዮብ 21
21
ኢዮብ
1ኢዮብም እንዲህ ሲል መለሰ፦
2“እስቲ ንግግሬን በጥሞና አድምጡኝ፤
በዚህም እኔን እንዳጽናናችሁኝ ይቈጠርላችሁ።
3አንድ ጊዜ ለመናገር ዕድል ስጡኝ፤
ከዚያ በኋላ እንደ ፈለጋችሁ መሳለቅ ትችላላችሁ።
4“እኔ የማዝነው በሰብአዊ ፍጡር ላይ ነውን?
ታዲያ፥ ትዕግሥቴ ቢያልቅ ምን ያስገርማል?
5እስቲ ወደ እኔ ተመልከቱ፤
መናገር እስኪያቅታችሁ ድረስ ሁኔታዬ ያሠቅቃችኋል።
6እኔ እንኳ ሳስበው ያስደነግጠኛል፤
ሰውነቴንም በፍርሃት ያንቀጠቅጠዋል።
7“ክፉ ሰዎች ዕድሜአቸው ረዝሞ፥ ሃብታቸው በዝቶ
በምድር ላይ ስለምን ይኖራሉ?
8ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው
አድገውና ተደላድለው ሲኖሩ ለምን ያያሉ?
9ያለ አንዳች ሥጋት በሰላም ይኖራሉ፤
የእግዚአብሔር መቅሠፍት ደርሶባቸው አያውቅም፤
10ከብቶቻቸው ያለአንዳች ችግር ይረባሉ፤
ላሞቻቸውም ምንም ሳይጨነግፉ ይወልዳሉ።
11ልጆቻቸውን እንደ በግ መንጋ ያሰማራሉ፤
ሕፃናታቸውም ይቦርቃሉ።
12አታሞ እየመቱ፥ በገና እየደረደሩ፥
እምቢልታ እየነፉ፥ በደስታ ይዘፍናሉ።
13ዕድሜአቸውን በተድላ ደስታ ያሳልፋሉ፤
ያለ ሥቃይም ከዚህ ዓለም በሞት ይለያሉ።
14“ይህም ሆኖ ሳለ እግዚአብሔርን
‘ከእኛ ራቅ፤ የአንተን መንገድ ማወቅ አንፈልግም’ ይሉታል።
15‘እናመልከው ዘንድ ሁሉን ቻይ አምላክ ማነው?
ወደ እርሱስ መጸለይ ምን ይጠቅመናል?’ ይላሉ።
16ይህንንም የሚሉት በእጃቸው ያለው ሀብት ሁሉ
በራሳቸው ጥረት የተገኘ ስለሚመስላቸው ነው፤
እኔ ግን የክፉ ሰዎችን ሐሳብ አልቀበልም።
17“ለመሆኑ የክፉ ሰዎች መብራት ጠፍቶ ያውቃልን?
መቅሠፍትስ በእነርሱ ላይ ወርዶ ያውቃልን?
እግዚአብሔር በቊጣው ቀጥቶአቸው ያውቃልን?
18እንደ ገለባ በነፋስ የተወሰዱበት፥
እንደ ትቢያም በዐውሎ ነፋስ የተጠረጉበት ጊዜ አለን?
19“እናንተ ‘እግዚአብሔር በአባቶች በደል
ልጆችን ይቀጣል’ ትላላችሁ፤
እስቲ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን ራሳቸውን ይቅጣቸው፤
ይህ ከሆነ በደለኛነታቸውን ሊገነዘቡት ይችላሉ።
20ኃጢአተኞች ራሳቸው በሠሩት በደል ቅጣታቸውን ይቀበሉ፤
ሁሉን የሚችል አምላክ ቊጣውን ያውርድባቸው፤
21ሰው ከሞተ በኋላ፥
ስለ ልጆቹ ምን ደንታ ይኖረዋል?
22እግዚአብሔር በታላላቅ ሰዎች ላይ እንኳ ይፈርዳል፤
ታዲያ፥ ሰው ለእርሱ የፍርድን ዕውቀት ሊያስተምር ይችላልን?
23“አንዳንድ ሰዎች እስከ ሕይወታቸው መጨረሻ
ምንም ችግር ሳይደርስባቸው ብርቱዎችና ጤናማዎች ሆነው፥
24ሰውነታቸው ወፍሮ እንዳማረባቸው፥
አጥንታቸውም በመቅን እንደ ተሞላ (እንደ ለመለመ) ይሞታሉ።
25ሌሎች ግን መሪር ሐዘን ሳይለያቸው፥
በችግር እንደ ተቈራመዱ መልካም ነገር ሳያገኙ ይሞታሉ።
26ሁሉም ወደ መቃብር በአንድ ላይ ወርደው ዐፈር ይሆናሉ፤
ትልም ይወርሳቸዋል።
27“እነሆ፥ እኔን ለመበደል በማሰብ
በአእምሮአችሁ ያቀዳችሁትን ተንኰል ዐውቃለሁ።
28እናንተ ‘የዚያ የትልቅ ሰው ቤት የት ነው?’
የክፉውስ ሰው መኖሪያ የት ነው? ትላላችሁ።
29መንገደኞችን አልጠየቃችሁምን?
የተናገሩትንስ ምስክርነት አትቀበሉምን?
30እነዚያ ‘ክፉ ሰዎች መቅሠፍት በሚመጣበት ጊዜ ጒዳት አይደርስባቸውም፤
የእግዚአብሔር ቊጣም ሲገለጥ ያመልጣሉ’ ሲሉ ተናግረዋል።
31ክፉውን ሰው ስለ መጥፎ ጠባዩ የሚወቅሰው ማን ነው?
በክፉ ሥራውስ የሚቀጣው ማን ነው?
32ከሞተ በኋላም አስከሬኑን ተሸክመው ወደ መቃብርም ይወስዱታል፤
መቃብሩ ይጠበቃል፤
33በሸለቆ ያለው ዐፈር ይመቻችለታል፤
ሰዎች ሁሉ ይከተሉታል፤
እጅግ ብዙ ሕዝብም በፊቱ ይሄዳል።
34“ታዲያ፥ እናንተ ከንቱ በሆነ አነጋገር
ልታጽናኑኝ ለምን ትሞክራላችሁ?
የምትመልሱልኝ መልስ ሁሉ ሐሰት ነው።”
ኤሊፋዝ
(22፥1—27፥23)
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 21: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997