መጽሐፈ ኢዮብ 19
19
1ኢዮብም መለሰ፤ እንዲህም አለ፦
2“ነፍሴን የምትነዘንዙት፥
በቃልስ የምታደቅቁኝ እስከ መቼ ነው?
3ይኸው ስትሰድቡኝ ዐሥር ጊዜ ነው፥
ስታሰቃዩኝም አላፈራችሁም።
4በእውነትም የሳትሁ እንደሆነ፥
ስሕተቴ ከእኔ ጋር ትኖራለች።
5በእውነትም ብትኩራሩብኝ፥
በመዋረዴም ብታሳብቡ፥
6እንግዲህ እግዚአብሔር ጥፋተኛ እንዳደረገኝ፥
በመረቡም እንደ ከበበኝ እወቁ።
7እነሆ፥ ስለ ተደረገብኝ ግፍ ብጮኽ ማንም አይመልስልኝም፥
ድረሱልኝ ብዬ ብጣራ ፍርድ የለኝም።
8እንዳላልፍ መንገዴን ዘግቶታል፥
በጎዳናዬም ጨለማ አኑሮበታል።
9ክብሬን ገፈፈኝ፥
ዘውዴንም ከራሴ ላይ ወሰደ።
10በዚህና በዚያም አፈረሰኝ፥ እኔም ሄድሁ፥
ተስፋዬንም እንደ ዛፍ ነቀለው፥
11ቁጣውንም አነደደብኝ፥
እንደ ጠላቱም ቈጠረኝ።
12ሠራዊቱ አብረው መጡ፥
መንገዳቸውንም በላዬ አዘጋጁ፥
በድንኳኔም ዙሪያ ሰፈሩ።”
13“ወንድሞቼን ከእኔ ዘንድ አራቀ፥
የሚያውቁኝም አጥብቀው ተለዩኝ።
14ዘመዶቼ ተቋረጡ፥
ወዳጆቼም ረሱኝ።
15እንግዶቼ በቤቴ፥ ሴቶች አገልጋዮቼም እንደ መጻተኛ ቈጠሩኝ፥
በዓይናቸውም እንደ እንግዳ ሆንሁ።
16አገልጋዬን ብጠራ አይመልስልኝም፥ በአፌም መለማመጥ አለብኝ።
17ሚስቴ እስትንፋሴን ጠላች፥
የእናቴም ማኅፀን ልጆች ተጸየፉኝ።
18ሕፃናት እንኳ አጠቁኝ፥
ብነሣም በእኔ ላይ ይናገራሉ።
19 #
ሲራ. 6፥8። አማካሪዎቼ ሁሉ ተጸየፉኝ፥
እኔ የምወድዳቸው በላዬ ተገለበጡ።
20አጥንቴ ከቁርበቴና ከሥጋዬ ጋር ተጣበቀ፥
ድድ ብቻ ቀርቶልኝ አመለጥሁ።
21እናንተ ወዳጆቼ ሆይ፥ ራሩልኝ፥ ራሩልኝ፥
የእግዚአብሔር እጅ መትታኛለችና።
22ስለምን እናንተ እንደ እግዚአብሔር ታሳድዱኛላችሁ?
ከሥጋዬስ ስለምን አትጠግቡም?”
23“ምነው አሁን ቃሌ ቢጻፍ!
ምነው በመጽሐፍ ውስጥ ቢታተም!
24ምነው በብረት ብርና በእርሳስ
በዓለቱ ላይ ለዘለዓለም ቢቀረጽ!
25እኔን ግን የሚቤዥኝ ሕያው እንደሆነ፥
በመጨረሻም ዘመን በምድር ላይ እንደሚቆም፥
26ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥
በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንደማይ አውቃለሁ።
27እኔ ራሴ አየዋለሁ፥
ዐይኖቼም ይመለከቱታል፥
ከእኔም ሌላ አይደለም።
ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል።
28በእውነት፦ እንዴት እናሳድደዋለን?
የነገሩ ሥር በእርሱ ዘንድ ተገኝቶአል ብትሉ፥
29ፍርድ እንዳለ ታውቁ ዘንድ
ቁጣ የሰይፍን ቅጣት ያመጣልና
ከሰይፍ ፍሩ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 19: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ