የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፍጥረት 47:13-27

ዘፍጥረት 47:13-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በም​ድ​ርም ሁሉ እህል አል​ነ​በ​ረም፤ ራብ እጅግ ጸን​ቶ​አ​ልና፤ ከራ​ብም የተ​ነሣ የግ​ብፅ ምድ​ርና የከ​ነ​ዓን ምድር ተጐዳ። ዮሴ​ፍም ከግ​ብፅ ምድ​ርና ከከ​ነ​ዓን ምድር በእ​ህል ሸመታ የተ​ገ​ኘ​ውን ብሩን ሁሉ አከ​ማቸ፤ ዮሴ​ፍም ብሩን ወደ ፈር​ዖን ቤት አስ​ገ​ባው። ብሩም በግ​ብፅ ምድ​ርና በከ​ነ​ዓን ምድር አለቀ፤ የግ​ብፅ ሰዎ​ችም ሁሉ ወደ ዮሴፍ መጡ፤ እን​ዲህ ሲሉ፥ “በፊ​ትህ እን​ዳ​ን​ሞት እህል ስጠን፤ ብሩ አል​ቆ​ብ​ና​ልና።” ዮሴ​ፍም፥ “ከብ​ቶ​ቻ​ች​ሁን አም​ጡ​ልኝ፤ ብር ከአ​ለ​ቀ​ባ​ችሁ በከ​ብ​ቶ​ቻ​ችሁ ፈንታ እህል እሰ​ጣ​ች​ኋ​ለሁ” አለ። ከብ​ቶ​ቻ​ቸ​ው​ንም ወደ ዮሴፍ አመጡ፤ ዮሴ​ፍም በፈ​ረ​ሶ​ቻ​ቸው፥ በበ​ጎ​ቻ​ቸ​ውም፥ በላ​ሞ​ቻ​ቸ​ውም፥ በአ​ህ​ዮ​ቻ​ቸ​ውም ፈንታ እህ​ልን ሰጣ​ቸው፤ በዚ​ያች ዓመ​ትም ስለ ከብ​ቶ​ቻ​ቸው ሁሉ ፈንታ እህ​ልን መገ​ባ​ቸው። ያችም ዓመት ተፈ​ጸ​መች፤ በሁ​ለ​ተ​ኛ​ዋም ዓመት ወደ እርሱ መጥ​ተው እን​ዲህ አሉት፥ “እኛ ለጌ​ታ​ችን ሞተን እን​ዳ​ና​ል​ቅ​በት እህል ስጠን፤ ብሩ በፍ​ጹም አለቀ፤ ንብ​ረ​ታ​ች​ንና ከብ​ታ​ች​ንም በጌ​ታ​ችን ዘንድ ነው፤ ከሰ​ው​ነ​ታ​ች​ንና ከም​ድ​ራ​ችን በቀር በጌ​ታ​ችን ፊት አን​ዳች የቀ​ረን የለም፤ እን​ግ​ዲህ እኛ በፊ​ትህ እን​ዳ​ን​ሞት፥ ምድ​ራ​ች​ንም እን​ዳ​ት​ጠፋ፥ እኛ​ንም፥ ምድ​ራ​ች​ን​ንም በእ​ህል ግዛን፤ እኛም ለፈ​ር​ዖን አገ​ል​ጋ​ዮች እን​ሁን፤ ምድ​ራ​ች​ንም ለእ​ርሱ ትሁን፤ እኛ እን​ድ​ን​ድን፥ እን​ዳ​ን​ሞ​ትም፥ ምድ​ራ​ች​ንም እን​ዳ​ት​ጠፋ እን​ዘራ ዘንድ ዘር ስጠን።” ዮሴ​ፍም የግ​ብ​ፅን ምድር ሁሉ ለፈ​ር​ዖን ገዛ፤ የግ​ብፅ ሰዎች ሁሉ ራብ ስለ​ጸ​ና​ባ​ቸው ርስ​ታ​ቸ​ውን ሸጠ​ዋ​ልና፤ ምድ​ሪቱ ለፈ​ር​ዖን ሆነች። ሕዝ​ቡ​ንም ሁሉ ከግ​ብፅ ዳርቻ አን​ሥቶ እስከ ሌላው ዳር​ቻዋ ድረስ አገ​ል​ጋ​ዮች አደ​ረ​ጋ​ቸው። ዮሴፍ የካ​ህ​ና​ትን ምድር ብቻ አል​ገ​ዛም፤ ፈር​ዖን ለካ​ህ​ናቱ ድርጎ ይሰ​ጣ​ቸው ነበ​ርና፥ ፈር​ዖ​ንም የሰ​ጣ​ቸ​ውን ድርጎ ይበሉ ነበር፤ ስለ​ዚ​ህም ምድ​ራ​ቸ​ውን አል​ሸ​ጡም። ዮሴ​ፍም የግ​ብ​ፅን ሰዎች ሁሉ እን​ዲህ አላ​ቸው፥ “እነሆ ዛሬ እና​ን​ተ​ንና ምድ​ራ​ች​ሁን ለፈ​ር​ዖን ገዝ​ቻ​ች​ኋ​ለሁ፤ ለእ​ና​ንተ ዘር ውሰ​ዱና ምድ​ሪ​ቱን ዝሩ፤ በመ​ከ​ርም ጊዜ ፍሬ​ውን ከአ​ም​ስት እጅ አን​ዱን እጅ ለፈ​ር​ዖን ስጡ፤ አራ​ቱም እጅ ለእ​ና​ንተ ለራ​ሳ​ችሁ፥ ለእ​ር​ሻው ዘርና ለእ​ና​ንተ ምግብ፥ ለቤተ ሰባ​ች​ሁም ሁሉ ሲሳይ ይሁን።” እነ​ር​ሱም፥ “አንተ አዳ​ን​ኸን፤ በጌ​ታ​ች​ንም ፊት ሞገ​ስን አገ​ኘን፤ ለፈ​ር​ዖ​ንም አገ​ል​ጋ​ዮች እን​ሆ​ና​ለን” አሉት። ዮሴ​ፍም ለፈ​ር​ዖን ካል​ሆ​ነ​ችው ከካ​ህ​ናቱ ምድር በቀር አም​ስ​ተ​ኛው እጅ ለፈ​ር​ዖን እን​ዲ​ሆን በግ​ብፅ ምድር እስከ ዛሬ ሕግ አደ​ረ​ጋት። እስ​ራ​ኤ​ልም በግ​ብፅ ምድር በጌ​ሤም ሀገር ተቀ​መጠ፤ እር​ስ​ዋም ርስ​ታ​ቸው ሆነች፤ በዙ፤ እጅ​ግም ተባዙ።

ዘፍጥረት 47:13-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

በመላው ምድር እህል ባለመኖሩ ራቡ እየጸና ሄደ፤ ከዚህ የተነሣም ግብፅና ከነዓን በራብ እጅግ ተጐዱ፤ ዮሴፍ የግብፅና የከነዓን ሰዎች እህል በመሸመት የከፈሉትን ገንዘብ ሁሉ ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ቤተ መንግሥት አስገባ። የግብፅና የከነዓን ሕዝቦችም ገንዘባቸው ባለቀ ጊዜ፣ ግብፃውያን ሁሉ ወደ ዮሴፍ ቀርበው፣ “የምንበላው እህል ስጠን፤ ገንዘባችን አልቆብናል፤ ዐይንህ እያየ እንዴት በራብ እንለቅ?” አሉት። ዮሴፍም፣ “ከብቶቻችሁን አምጡ፤ ገንዘባችሁ ካለቀ በከብቶቻችሁ ለውጥ እህል እሰጣችኋለሁ” አለ። ስለዚህ ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ አመጡ፤ እርሱም በፈረሶቻቸው፣ በበጎቻቸው፣ በፍየሎቻቸው፣ በከብቶቻቸውና በአህዮቻቸው ለውጥ እህል ሰጣቸው። በከብቶቻቸው ልዋጭ ባገኙት ምግብ የዚያን ዓመት ራብ እንዲወጡት አደረገ። ያም ዓመት ካለፈ በኋላ ሕዝቡ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ዮሴፍ መጥተው እንዲህ አሉት፣ “እንግዲህ ከጌታችን የምንሰውረው ምንም ነገር የለም፤ ገንዘባችን አልቋል፤ ከብቶቻችንንም አስረክበንሃል፤ እንግዲህ ለጌታችን የምንሰጠው፣ ከመሬታችንና ከእኛ ከራሳችን በስተቀር አንዳች ነገር የለም። ታዲያ፣ እያየኸን እንዴት እንለቅ? መሬታችንስ ለምን ጠፍ ሆኖ ይቅር? እኛንና መሬታችንን ውሰድና በለውጡ እህል ስጠን፤ እኛ የፈርዖን ገባሮች እንሁን፤ መሬታችንም የእርሱ ርስት ይሁን፤ እኛም እንዳንሞት መሬታችንም ጠፍ ሆኖ እንዳይቀር የምንዘራው ዘር ስጠን።” ስለዚህ ዮሴፍ የግብፅን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛለት፤ ራቡም እጅግ ስለ ጸናባቸው ግብፃውያን ሁሉ አንዳቸውም ሳይቀሩ መሬታቸውን ሸጡ፤ ምድሪቱም የፈርዖን ርስት ሆነች። ዮሴፍም የግብፅን ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የፈርዖን ገባር አደረገው። ሆኖም ዮሴፍ የካህናቱን መሬት አልገዛም፤ ምክንያቱም ካህናቱ ከፈርዖን ቋሚ ድርጎ ስለሚያገኙና ፈርዖን ከሚሰጣቸው ድርጎ በቂ ምግብ ስለ ነበራቸው ነው፤ ከዚህም የተነሣ መሬታቸውን አልሸጡም። ዮሴፍ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፣ ዛሬ እናንተንም መሬታችሁንም ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁና ይህን ዘር ወስዳችሁ በመሬት ላይ ዝሩ። መከሩ በሚሰበሰብበት ጊዜ ግን ከአምስት እጅ አንዱን ለፈርዖን ታስገባላችሁ፤ ከአምስት እጅ አራቱን ደግሞ ለመሬታችሁ ዘር፣ እንዲሁም ለራሳችሁ፣ ለቤተ ሰቦቻችሁና ለልጆቻችሁ ምግብ ታደርጉታላችሁ።” እነርሱም፣ “እንግዲህ ሕይወታችንን አትርፈህልናል፤ በጌታችን ፊት ሞገስ ካገኘን፣ ለፈርዖን ገባሮች እንሆናለን” አሉት። ስለዚህ ዮሴፍ የምርቱ አንድ አምስተኛ ለፈርዖን እንዲገባ የሚያዝ የመሬት ሕግ አወጣ፤ ይህም ሕግ እስከ ዛሬ ይሠራበታል። በዚያን ጊዜ በፈርዖን እጅ ያልገባው መሬት የካህናቱ ብቻ ነበር። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን በግብፅ አገር በጌሤም ይኖሩ ነበር፤ በዚያም ሀብት ንብረት ዐፈሩ፤ ቍጥራቸውም እጅግ እየበዛ ይሄድ ጀመር።

ዘፍጥረት 47:13-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በምድርም ሁሉ እህል አልነበረም ራብ እጅግ ጸንቶአልና ከራብም የተነሣ የግብፅ ምድርና የከነዓን ምድር ተጎዳ። ዮሴፍም ከግብፅ ምድርና ከከነዓን ምድር በእህል ሸመት የተገኘውን ብሩን ሁሉ አከማቸ ዮሴፍ ብሩን ወደ ፈርዖን ቤት አስገባው። ብሩም በግብፅ ምድርን በከነዓን ምድር አለቀ፤ የግብፅ ሰዎችም ሁሉ ወደ ዮሴፍ መጡ እንዲህ ሲሉ፦ እንጀራ ስጠን ስለ ምን በፊትህ እንሞታለን? ብሩ አልቆብናልና። ዮሴፍም፦ ከብቶቻችሁን አምጡልኝ ብር ካለቀባችሁ በከብቶቻችሁ ፋንታ እህል እሰጣችኍለሁ አለ። ከብቶቻቸውንም ወደ ዮሴፍ አመጡ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው በበጎቻቸውም በላሞቻቸውም በአህዮቻቸውም ፋንታ እህልን ሰጣቸው በዚያች ዓመትም ስለ ከብቶቻቸው ሁሉ ፋንት እህልን መገባቸው። ዓመቱም ተፈጸመ በሁለተኛውም ዓመት ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ አሉት፦ እኛ ከጌታችን አንሰውርም ብሩ በፍጹም አለቀ ከብታችንም ከጌታችን ጋር ነው ከሰውነታችንና ከምድራችን በቀር በጌታችን ፊት አንዳች የቀረ የለም እኛ በፈትህ ስለ ምን እንሞታለን? ምድራችንስ ስለ ምን ትጠፋለች? እኛንም ምድራችንንም በእህል ግዛን እኛም ለፈርዖን ባሪያዎች እንሁን ምድራችንም ለእርሱ ትሁን እኝ እንድንድን እንዳንሞትም ምድራችንም እንዳትጠፋ ዘር ስጠን። ዮሴፍም የግብፅ ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛ የግብፅ ሰዎች ሁሉ ራብ ስለ ጸናባቸው ርስታቸውን ሸጠዋልን ምድሪቱ ለፈርዖን ሆነች። ሕዝቡንም ሁሉ ከግብፅ ዳርቻ አንሥቶ እስከ ሌላው ዳርቻዋ ድረስ ባርያዎች አደረጋቸው። የካህናትን ምድር ብቻ አልገዛም ካህናቱ ከፈርዖን የሰጣቸውን ድርጎ ይበሉ ነበር ስለዚህም ምድራቸውን አልሸጡም። ዮሴፍም ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ እነሆ ዛሬ እናንተንና ምድራችሁን ለፈርዖን ገዝቻችኍለሁ ዘር ውሰዱና ምድሪቱን ዝሩ በመከርም ጊዜ ፍሬውን ከአምስት እጅ አንዱን እጅ ለፈርዖን ስጡ አራቱም እጅ ለእናንተ ለራሳችሁ ለእርሻው ዘርና ለእናንተ ምግብ ለቤተ ሰዋችሁና ለሕፃናቶቻችሁም ሲሳይ ይሁን። እርሱም፦ አንተ አዳንኸን በጌታችን ፊት ሞገስን አናግኝ ለፈርዖንም ባሪያዎች እንሆናለን አሉት። ዮሴፍም ለፈርዖን ካልሆነችው ከካህናቱ ምድር በቀር አምስተኛው እጅ ለፈርዓን እንዲሆን በግብፅ ምድር እስከ ዛሬ ድረስ ሕግ አደረጋት። እስራኤልም በግብፅ ምድር በጌሤም አገር ተቀመጠ ገዙአትም ረቡ እጅግም በዙ።

ዘፍጥረት 47:13-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ይሁን እንጂ ራቡ እየጸና ስለ ሄደ፥ ከየትም አገር እህል ለማግኘት አልተቻለም ነበር፤ የግብጽና የከነዓን ሕዝቦችም በረሀቡ እጅግ ተጐድተው ነበር። ስለዚህ የግብጽና የከነዓን ሕዝቦች ወደ ዮሴፍ እየመጡ እህል ሲሸምቱ፥ ዮሴፍ ገንዘቡን ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ግምጃ ቤት ያስገባው ነበር። በዚህ ሁኔታ የግብጽና የከነዓን ሕዝቦች ገንዘባቸውን በእህል ሸመታ ስለ ጨረሱ፥ ግብጻውያን ወደ ዮሴፍ ተሰብስበው መጥተው “የምንመገበው እህል ስጠን! ገንዘባችንን ስለ ጨረስን በራብ ማለቃችን ነው!” አሉት። ዮሴፍም “ገንዘባችሁ ካለቀ ከብቶቻችሁን አምጡና በእነርሱ ለውጥ እህል እሰጣችኋለሁ” አለ። እነርሱም ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ አመጡ፤ እርሱም በፈረሶቻቸውና በአህዮቻቸው፥ በበጎቻቸውና በፍየሎቻቸው በከብቶቻቸውም ለውጥ እህል ሰጣቸው፤ ያንንም ዓመት በሙሉ በከብቶቻቸው ልዋጭ እህል ሰጣቸው። በሚቀጥለውም ዓመት ወደ እርሱ መጡና እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን ሆይ! ከአንተ የምንሰውረው ነገር የለም፤ ገንዘባችን ሁሉ አልቆአል፤ ከብቶቻችንንም ለአንተ አስረክበናል፤ እንግዲህ ለጌታችን የምንሰጠው ከሰውነታችንና ከመሬታችን በቀር ሌላ ምንም ነገር የለንም። እኛና ምድራችን በፊትህ እንጥፋን? እኛንና መሬታችንን ገዝተህ እህል ስጠን፤ እኛ የንጉሡ ባሪያዎች እንሆናለን፤ መሬታችንም የእርሱ ይሁን፤ በልተን በሕይወት እንድንኖር እህል ስጠን፤ በመሬታችን ላይ የምንዘራውም ዘር ስጠን።” ዮሴፍ በግብጽ ያለውን መሬት ሁሉ ለንጉሡ ገዛ፤ ከራቡ ጽናት የተነሣ ግብጻውያን ሁሉ መሬታቸውን መሸጥ ግድ ሆነባቸው፤ በዚህ ዐይነት መሬት ሁሉ የንጉሡ ንብረት ሆነ። ዮሴፍ በግብጽ አገር ዳር እስከ ዳር ያሉት ሰዎች ሁሉ የንጉሡ ባሪያዎች እንዲሆኑ አደረገ። ዮሴፍ ያልገዛው የካህናቱን መሬት ብቻ ነው፤ ካህናት ከፈርዖን በየጊዜው ድርጎ ይቀበሉ ስለ ነበር መሬታቸውን ለመሸጥ አልተገደዱም። ዮሴፍ ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፥ እንግዲህ እናንተንና መሬታችሁን ለፈርዖን ስለ ገዛሁ ዘር ውሰዱና በመሬታችሁ ላይ ዝሩ። ነገር ግን በመከር ጊዜ ከምታመርቱት ከአምስት አንዱን እጅ ለፈርዖን መስጠት አለባችሁ፤ የቀረው አራት አምስተኛው እጅ ግን ለመሬታችሁ ዘር፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ ለቤተሰባችሁም ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ።” ሕዝቡም “ጌታችን ሆይ፥ ሕይወታችንን ስላዳንክልንና መልካም ነገር ስላደረግህልን ሁላችንም የፈርዖን ባሪያዎች እንሆናለን” አሉት። በዚህ ዐይነት ዮሴፍ ከመከር ሁሉ አንድ አምስተኛው እጅ ለፈርዖን እንዲሰጥ የግብጽን መሬት ይዞታ በሚመለከት ሕግ አወጣ፤ ይህም ሕግ እስከ ዛሬ ድረስ ይሠራበታል፤ የፈርዖን ንብረት ያልሆነው የካህናት መሬት ብቻ ነው። እስራኤላውያን በግብጽ አገር ጌሴም በተባለ ምድር ይኖሩ ነበር፤ እዚያም ብዙ ሀብት አገኙ፤ ብዙ ልጆችም ወለዱ።

ዘፍጥረት 47:13-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ራብም እጅግ ጸንቶአልና፥ በምድር ሁሉ እህል አልነበረም፥ ከራብም የተነሣ የግብጽ ምድርና የከነዓን ምድር ተጎዳ። ዮሴፍም የግብጽና የከነዓን ሕዝቦች የመጡ እህል ሲሸምቱ፥ ዮሴፍ ገንዘቡን ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ግምጃ ቤት ያስገባው ነበር። በግብጽ ምድርና በከነዓን ምድር ብሩም በሸመታ አለቀ፥ የግብጽ ሰዎች ሁሉም ወደ ዮሴፍ እየመጡ፦ “የምንመገበው ስጠን፥ ስለምን በፊትህ እንሞታለን? ብሩ አልቆብናልና” አሉት። ዮሴፍም፦ “ከብቶቻችሁን አምጡልኝ፥ ብር ካለቀባችሁ በከብቶቻችሁ ፋንታ እህል እሰጣችኋለሁ” አለ። ከብቶቻቸውንም ወደ ዮሴፍ አመጡ፥ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው በበጎቻቸውም በላሞቻቸውም በአህዮቻቸውም ፋንታ እህልን ሰጣቸው፥ ያንንም ዓመት በከብቶቻቸው ሁሉ ልዋጭ ህልን መገባቸው። ዓመቱም ተፈጸመ፥ በሁለተኛውም ዓመት ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ አሉት፦ “እኛ ከጌታችን አንሰውርም፥ ብሩ በፍጹም አለቀ፥ ከብታችንም ከጌታችን ጋር ነው፥ ከሰውነታችንና ከምድራችን በቀር በጌታችን ፊት አንዳች የቀረ የለም፥ እኛ በፈትህ ስለምን እንሞታለን? ምድራችንስ ስለምን ትጠፋለች? እኛንም ምድራችንንም በእህል ግዛን፥ እኛም ለፈርዖን ባርያዎች እንሁን፥ ምድራችንም ለእርሱ ትሁን፥ እኛ እንድንድን እንዳንሞትም ምድራችንም እንዳትጠፋ ዘር ስጠን።” ዮሴፍም የግብጽን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛ፥ የግብጽ ሰዎች ሁሉ ራብ ስለ ጸናባቸው ርስታቸውን ሸጠዋልና፥ ምድሪቱ ለፈርዖን ሆነች። ሕዝቡንም ሁሉ ከግብጽ ዳርቻ አንሥቶ እስከ ሌላው ዳርቻዋ ድረስ ባርያዎች አደረጋቸው። የካህናትን ምድር ብቻ አልገዛም፥ ካህናቱ ከፈርዖን ዘንድ ድርጎ ያገኙ ነበርና፥ ፈርዖንም የሰጣቸውን ድርጎ ይበሉ ነበር፥ ስለዚህም ምድራቸውን አልሸጡም። ዮሴፍም ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “እነሆ ዛሬ እናንተንና ምድራችሁን ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁ፥ ዘር ውሰዱና ምድሪቱን ዝሩ፥ በመከርም ጊዜ ፍሬውን ከአምስት እጅ አንዱን እጅ ለፈርዖን ስጡ፥ አራቱም እጅ ለእናንተ ለራሳችሁ፥ ለእርሻው ዘርና ለእናንተ ምግብ፥ ለቤተ ሰዋችሁና ለሕፃናቶቻችሁም ምግብ ይሁን።” እነርሱም፦ “አንተ ሕይወታችንን አተረፍክ፥ ጌታችንን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ፥ ለፈርዖንም ባርያዎች እንሆናለን” አሉት። ዮሴፍም ለፈርዖን ካልሆነችው ከካህናቱ ምድር በቀር አምስተኛው እጅ ለፈርዓን እንዲሆን በግብጽ ምድር እስከ ዛሬ ድረስ ሕግ አደረጋት። እስራኤልም በግብጽ ምድር በጌሤም አገር ተቀመጠ፥ ገዙአትም፥ ረቡ፥ እጅግም በዙ።