የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 47

47
ዮሴፍ የዘመዶቹን መምጣት ለፈርዖን መናገሩ
1ዮሴፍም ወደ ፈርዖን ሄዶ “አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውንና ፍየሎቻቸውን ከብቶቻቸውንና ሌላም ያላቸውን ነገር ሁሉ ይዘው ከከነዓን ወደዚህ መጥተዋል፤ አሁንም በጌሴም ምድር ይገኛሉ” አለው። 2ከወንድሞቹ መካከል መርጦ ያመጣቸውንም አምስቱን ወንድሞቹን ወደ ፈርዖን አቀረባቸው። 3ፈርዖንም ወንድሞቹን፦ “ሥራችሁ ምንድነው?” አላቸው። እነርሱም ፈርዖንን፦ “እኛ አገልጋዮችህ፥ እኝም አባቶቻችንም፥ በግ አርቢዎች ነን” አሉት። 4“በምድር ልንቀመጥ በእንግድነት መጣን፥ ራብ በከነዓን ምድር እጅግ ጸንቶአልና፥ የአገልጋዮችህ በጎች የሚሰማሩበት ስፍራ የለም፥ አሁንም አገልጋዮችህ በጌሤም ምድር እንድንቀመጥ እንለምንሃለን።” አሉት ፈርዖንን። 5ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፦ “አባትህና ወንድሞችህ መጥተውልሃል፥ 6የግብጽ ምድር በፊትህ ናት፥ በመልካሙ ምድር አባትህንና ወንድሞችህን አኑራቸው፥ በጌሤም ምድር ይኑሩ፤ ከእነርሱ መካከል ችሎታ ያላቸው ሰዎች ካሉ፥ በእኔ እንስሶች ላይ የበላይ ኀላፊዎች አድርገህ ሹማቸው።” 7ዮሴፍም ያዕቆብን አባቱን አስገብቶ በፈርዖን ፊት አቆመው፥ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው። 8ፈርዖንም ያዕቆብን፦ “የዕድሜህ ዘመን ስንት ዓመት ነው?” አለው። 9ያዕቆብም ለፈርዖን አለው፦ “የእንግድነቴ ዘመን መቶ ሠላሳ ዓመት ነው፥ የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፋም ሆኑብኝ፥ አባቶቼ በእንግድነት የተቀመጡበትንም ዘመን አያህሉም።” 10ፈርዖንን ባርኮም ያዕቆብ ከፈርዖንም ፊት ወጣ። 11ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን አኖረ፥ ፈርዖን እንዳዘዘም በግብጽ ምድር በተሻለችው የራምሴ ምድር በይዞታ ሰጣቸው። 12ዮሴፍም ለአባቱና ለወንድሞቹ ለአባቱም ቤተ ሰዎች ሁሉ እንደ ልጆቻቸው መጠን እህል ሰጣቸው።
የዮሴፍ የግብርና ደንብ
13ራብም እጅግ ጸንቶአልና፥ በምድር ሁሉ እህል አልነበረም፥ ከራብም የተነሣ የግብጽ ምድርና የከነዓን ምድር ተጎዳ። 14ዮሴፍም የግብጽና የከነዓን ሕዝቦች የመጡ እህል ሲሸምቱ፥ ዮሴፍ ገንዘቡን ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ግምጃ ቤት ያስገባው ነበር። 15በግብጽ ምድርና በከነዓን ምድር ብሩም በሸመታ አለቀ፥ የግብጽ ሰዎች ሁሉም ወደ ዮሴፍ እየመጡ፦ “የምንመገበው ስጠን፥ ስለምን በፊትህ እንሞታለን? ብሩ አልቆብናልና” አሉት። 16ዮሴፍም፦ “ከብቶቻችሁን አምጡልኝ፥ ብር ካለቀባችሁ በከብቶቻችሁ ፋንታ እህል እሰጣችኋለሁ” አለ። 17ከብቶቻቸውንም ወደ ዮሴፍ አመጡ፥ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው በበጎቻቸውም በላሞቻቸውም በአህዮቻቸውም ፋንታ እህልን ሰጣቸው፥ ያንንም ዓመት በከብቶቻቸው ሁሉ ልዋጭ ህልን መገባቸው። 18ዓመቱም ተፈጸመ፥ በሁለተኛውም ዓመት ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ አሉት፦ “እኛ ከጌታችን አንሰውርም፥ ብሩ በፍጹም አለቀ፥ ከብታችንም ከጌታችን ጋር ነው፥ ከሰውነታችንና ከምድራችን በቀር በጌታችን ፊት አንዳች የቀረ የለም፥ 19እኛ በፈትህ ስለምን እንሞታለን? ምድራችንስ ስለምን ትጠፋለች? እኛንም ምድራችንንም በእህል ግዛን፥ እኛም ለፈርዖን ባርያዎች እንሁን፥ ምድራችንም ለእርሱ ትሁን፥ እኛ እንድንድን እንዳንሞትም ምድራችንም እንዳትጠፋ ዘር ስጠን።”
20ዮሴፍም የግብጽን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛ፥ የግብጽ ሰዎች ሁሉ ራብ ስለ ጸናባቸው ርስታቸውን ሸጠዋልና፥ ምድሪቱ ለፈርዖን ሆነች። 21ሕዝቡንም ሁሉ ከግብጽ ዳርቻ አንሥቶ እስከ ሌላው ዳርቻዋ ድረስ ባርያዎች አደረጋቸው። 22የካህናትን ምድር ብቻ አልገዛም፥ ካህናቱ ከፈርዖን ዘንድ ድርጎ ያገኙ ነበርና፥ ፈርዖንም የሰጣቸውን ድርጎ ይበሉ ነበር፥ ስለዚህም ምድራቸውን አልሸጡም። 23ዮሴፍም ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “እነሆ ዛሬ እናንተንና ምድራችሁን ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁ፥ ዘር ውሰዱና ምድሪቱን ዝሩ፥ 24በመከርም ጊዜ ፍሬውን ከአምስት እጅ አንዱን እጅ ለፈርዖን ስጡ፥ አራቱም እጅ ለእናንተ ለራሳችሁ፥ ለእርሻው ዘርና ለእናንተ ምግብ፥ ለቤተ ሰዋችሁና ለሕፃናቶቻችሁም ምግብ ይሁን።” 25እነርሱም፦ “አንተ ሕይወታችንን አተረፍክ፥ ጌታችንን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ፥ ለፈርዖንም ባርያዎች እንሆናለን” አሉት። 26ዮሴፍም ለፈርዖን ካልሆነችው ከካህናቱ ምድር በቀር አምስተኛው እጅ ለፈርዓን እንዲሆን በግብጽ ምድር እስከ ዛሬ ድረስ ሕግ አደረጋት።
ያዕቆብ የመጨረሻ ልመና
27እስራኤልም በግብጽ ምድር በጌሤም አገር ተቀመጠ፥ ገዙአትም፥ ረቡ፥ እጅግም በዙ። 28ያዕቆብም በግብጽ ምድር ዐሥራ ሰባት ዓመት ተቀመጠ፥ የያዕቆብም የሕይወቱ ዘመን መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነው። 29#ዘፍ. 49፥29-32፤ 50፥6።የእስራኤልም የሞቱ ቀን ቀረበ፥ ልጁን ዮሴፍንም ጠርቶ እንዲህ አለው፦ “በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደሆንሁ እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፥ በግብጽ ምድርም እንዳትቀብረኝ በታማኝነትና እውነት ቃል ግባልኝ፥ 30ከአባቶቼም ጋር በተኛሁ ጊዜ ከግብጽ ምድር አውጥተህ ትወስደኛለህ፥ በመቃብራቸውም ትቀብረኛለህ።” እርሱም፦ “እንደ ቃልህ አደርጋሁ” አለ። 31እርሱም፦ “ማልልኝ” አለው። ዮሴፍም ማለለት፥ እስራኤልም በአልጋው ራስ ላይ ሰገደ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ