ይሁን እንጂ ራቡ እየጸና ስለ ሄደ፥ ከየትም አገር እህል ለማግኘት አልተቻለም ነበር፤ የግብጽና የከነዓን ሕዝቦችም በረሀቡ እጅግ ተጐድተው ነበር። ስለዚህ የግብጽና የከነዓን ሕዝቦች ወደ ዮሴፍ እየመጡ እህል ሲሸምቱ፥ ዮሴፍ ገንዘቡን ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ግምጃ ቤት ያስገባው ነበር። በዚህ ሁኔታ የግብጽና የከነዓን ሕዝቦች ገንዘባቸውን በእህል ሸመታ ስለ ጨረሱ፥ ግብጻውያን ወደ ዮሴፍ ተሰብስበው መጥተው “የምንመገበው እህል ስጠን! ገንዘባችንን ስለ ጨረስን በራብ ማለቃችን ነው!” አሉት። ዮሴፍም “ገንዘባችሁ ካለቀ ከብቶቻችሁን አምጡና በእነርሱ ለውጥ እህል እሰጣችኋለሁ” አለ። እነርሱም ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ አመጡ፤ እርሱም በፈረሶቻቸውና በአህዮቻቸው፥ በበጎቻቸውና በፍየሎቻቸው በከብቶቻቸውም ለውጥ እህል ሰጣቸው፤ ያንንም ዓመት በሙሉ በከብቶቻቸው ልዋጭ እህል ሰጣቸው። በሚቀጥለውም ዓመት ወደ እርሱ መጡና እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን ሆይ! ከአንተ የምንሰውረው ነገር የለም፤ ገንዘባችን ሁሉ አልቆአል፤ ከብቶቻችንንም ለአንተ አስረክበናል፤ እንግዲህ ለጌታችን የምንሰጠው ከሰውነታችንና ከመሬታችን በቀር ሌላ ምንም ነገር የለንም። እኛና ምድራችን በፊትህ እንጥፋን? እኛንና መሬታችንን ገዝተህ እህል ስጠን፤ እኛ የንጉሡ ባሪያዎች እንሆናለን፤ መሬታችንም የእርሱ ይሁን፤ በልተን በሕይወት እንድንኖር እህል ስጠን፤ በመሬታችን ላይ የምንዘራውም ዘር ስጠን።” ዮሴፍ በግብጽ ያለውን መሬት ሁሉ ለንጉሡ ገዛ፤ ከራቡ ጽናት የተነሣ ግብጻውያን ሁሉ መሬታቸውን መሸጥ ግድ ሆነባቸው፤ በዚህ ዐይነት መሬት ሁሉ የንጉሡ ንብረት ሆነ። ዮሴፍ በግብጽ አገር ዳር እስከ ዳር ያሉት ሰዎች ሁሉ የንጉሡ ባሪያዎች እንዲሆኑ አደረገ። ዮሴፍ ያልገዛው የካህናቱን መሬት ብቻ ነው፤ ካህናት ከፈርዖን በየጊዜው ድርጎ ይቀበሉ ስለ ነበር መሬታቸውን ለመሸጥ አልተገደዱም። ዮሴፍ ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፥ እንግዲህ እናንተንና መሬታችሁን ለፈርዖን ስለ ገዛሁ ዘር ውሰዱና በመሬታችሁ ላይ ዝሩ። ነገር ግን በመከር ጊዜ ከምታመርቱት ከአምስት አንዱን እጅ ለፈርዖን መስጠት አለባችሁ፤ የቀረው አራት አምስተኛው እጅ ግን ለመሬታችሁ ዘር፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ ለቤተሰባችሁም ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ።” ሕዝቡም “ጌታችን ሆይ፥ ሕይወታችንን ስላዳንክልንና መልካም ነገር ስላደረግህልን ሁላችንም የፈርዖን ባሪያዎች እንሆናለን” አሉት። በዚህ ዐይነት ዮሴፍ ከመከር ሁሉ አንድ አምስተኛው እጅ ለፈርዖን እንዲሰጥ የግብጽን መሬት ይዞታ በሚመለከት ሕግ አወጣ፤ ይህም ሕግ እስከ ዛሬ ድረስ ይሠራበታል፤ የፈርዖን ንብረት ያልሆነው የካህናት መሬት ብቻ ነው። እስራኤላውያን በግብጽ አገር ጌሴም በተባለ ምድር ይኖሩ ነበር፤ እዚያም ብዙ ሀብት አገኙ፤ ብዙ ልጆችም ወለዱ።
ኦሪት ዘፍጥረት 47 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 47:13-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos