ኦሪት ዘፍጥረት 47
47
1ዮሴፍም ወደ ፈርዖን ሄዶ “አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውንና ፍየሎቻቸውን ከብቶቻቸውንና ሌላም ያላቸውን ነገር ሁሉ ይዘው ከከነዓን ወደዚህ መጥተዋል፤ አሁንም በጌሴም ምድር ይገኛሉ” አለው። 2ከወንድሞቹ መካከል መርጦ ያመጣቸውንም አምስቱን ወንድሞቹን ወደ ፈርዖን አቀረባቸው።
3ፈርዖንም የዮሴፍን ወንድሞች፦ “የምትተዳደሩበት ሥራ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው።
እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱለት፥ “እኛ አገልጋዮችህ በግ አርቢዎች ነን፤ አባቶቻቸንም ይተዳደሩበት የነበረ ሥራ ይኸው ነበር። 4በከነዓን ምድር ራብ እጅግ ከመበርታቱ የተነሣ ለእንስሶቻችን ግጦሽ ስላጣን ለጊዜው በዚህች አገር ለመኖር መጥተናል፤ ስለዚህ አገልጋዮችህ በጌሴም ምድር እንድንኖር ፍቀድልን።”
5ፈርዖንም ዮሴፍን እንዲህ አለው፥
“አባትህና ወንድሞችህ ከመጡልህ፤ 6እነሆ፥ መላው የግብጽ ምድር የአንተ ነው፤ ስለዚህ አባትህና ወንድሞችህ ምርጥ በሆነችው በጌሴም ምድር እንዲኖሩ አድርግ። ከእነርሱ መካከል ልዩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ካሉ፥ በእኔ እንስሶች ላይ የበላይ ኀላፊዎች አድርገህ ሹማቸው።”
7ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አባቱን ያዕቆብን ወደ ፈርዖን አቀረበው፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው፤ 8ፈርዖንም “ዕድሜህ ስንት ነው?” በማለት ያዕቆብን ጠየቀው።
9ያዕቆብም “በመንከራተት ያሳለፍኳቸው ዘመናት መቶ ሠላሳ ናቸው። እነርሱም የቀድሞ አባቶቼ በመንከራተት ካሳለፉአቸው ዘመናት እጅግ ያነሡና ችግር የበዛባቸው ናቸው” አለ። 10ያዕቆብ ፈርዖንን ባረከውና ተሰናብቶት ወጣ።
11ከዚህ በኋላ ዮሴፍ አባቱና ወንድሞቹ በግብጽ ምድር እንዲቀመጡ አደረገ፤ ፈርዖን ባዘዘው መሠረት በግብጽ ምድር ምርጥ የሆነውን፥ በራምሴ ከተማ አጠገብ ያለውን ቦታ በይዞታ ሰጣቸው። 12ዮሴፍ ለአባቱና ለወንድሞቹ በልጆቻቸው ቊጥር ልክ እህል ይሰጣቸው ነበር።
የራቡ ጽናትና የዮሴፍ አመራር
13ይሁን እንጂ ራቡ እየጸና ስለ ሄደ፥ ከየትም አገር እህል ለማግኘት አልተቻለም ነበር፤ የግብጽና የከነዓን ሕዝቦችም በረሀቡ እጅግ ተጐድተው ነበር። 14ስለዚህ የግብጽና የከነዓን ሕዝቦች ወደ ዮሴፍ እየመጡ እህል ሲሸምቱ፥ ዮሴፍ ገንዘቡን ሰብስቦ ወደ ፈርዖን ግምጃ ቤት ያስገባው ነበር። 15በዚህ ሁኔታ የግብጽና የከነዓን ሕዝቦች ገንዘባቸውን በእህል ሸመታ ስለ ጨረሱ፥ ግብጻውያን ወደ ዮሴፍ ተሰብስበው መጥተው “የምንመገበው እህል ስጠን! ገንዘባችንን ስለ ጨረስን በራብ ማለቃችን ነው!” አሉት።
16ዮሴፍም “ገንዘባችሁ ካለቀ ከብቶቻችሁን አምጡና በእነርሱ ለውጥ እህል እሰጣችኋለሁ” አለ። 17እነርሱም ከብቶቻቸውን ወደ ዮሴፍ አመጡ፤ እርሱም በፈረሶቻቸውና በአህዮቻቸው፥ በበጎቻቸውና በፍየሎቻቸው በከብቶቻቸውም ለውጥ እህል ሰጣቸው፤ ያንንም ዓመት በሙሉ በከብቶቻቸው ልዋጭ እህል ሰጣቸው።
18በሚቀጥለውም ዓመት ወደ እርሱ መጡና እንዲህ አሉት፤ “ጌታችን ሆይ! ከአንተ የምንሰውረው ነገር የለም፤ ገንዘባችን ሁሉ አልቆአል፤ ከብቶቻችንንም ለአንተ አስረክበናል፤ እንግዲህ ለጌታችን የምንሰጠው ከሰውነታችንና ከመሬታችን በቀር ሌላ ምንም ነገር የለንም። 19እኛና ምድራችን በፊትህ እንጥፋን? እኛንና መሬታችንን ገዝተህ እህል ስጠን፤ እኛ የንጉሡ ባሪያዎች እንሆናለን፤ መሬታችንም የእርሱ ይሁን፤ በልተን በሕይወት እንድንኖር እህል ስጠን፤ በመሬታችን ላይ የምንዘራውም ዘር ስጠን።”
20ዮሴፍ በግብጽ ያለውን መሬት ሁሉ ለንጉሡ ገዛ፤ ከራቡ ጽናት የተነሣ ግብጻውያን ሁሉ መሬታቸውን መሸጥ ግድ ሆነባቸው፤ በዚህ ዐይነት መሬት ሁሉ የንጉሡ ንብረት ሆነ። 21ዮሴፍ በግብጽ አገር ዳር እስከ ዳር ያሉት ሰዎች ሁሉ የንጉሡ ባሪያዎች እንዲሆኑ አደረገ። 22ዮሴፍ ያልገዛው የካህናቱን መሬት ብቻ ነው፤ ካህናት ከፈርዖን በየጊዜው ድርጎ ይቀበሉ ስለ ነበር መሬታቸውን ለመሸጥ አልተገደዱም።
23ዮሴፍ ለሕዝቡ እንዲህ አላቸው፤ “እነሆ፥ እንግዲህ እናንተንና መሬታችሁን ለፈርዖን ስለ ገዛሁ ዘር ውሰዱና በመሬታችሁ ላይ ዝሩ። 24ነገር ግን በመከር ጊዜ ከምታመርቱት ከአምስት አንዱን እጅ ለፈርዖን መስጠት አለባችሁ፤ የቀረው አራት አምስተኛው እጅ ግን ለመሬታችሁ ዘር፥ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ ለቤተሰባችሁም ሁሉ ምግብ ይሁናችሁ።”
25ሕዝቡም “ጌታችን ሆይ፥ ሕይወታችንን ስላዳንክልንና መልካም ነገር ስላደረግህልን ሁላችንም የፈርዖን ባሪያዎች እንሆናለን” አሉት። 26በዚህ ዐይነት ዮሴፍ ከመከር ሁሉ አንድ አምስተኛው እጅ ለፈርዖን እንዲሰጥ የግብጽን መሬት ይዞታ በሚመለከት ሕግ አወጣ፤ ይህም ሕግ እስከ ዛሬ ድረስ ይሠራበታል፤ የፈርዖን ንብረት ያልሆነው የካህናት መሬት ብቻ ነው።
የያዕቆብ የመጨረሻ ማሳሰቢያ
27እስራኤላውያን በግብጽ አገር ጌሴም በተባለ ምድር ይኖሩ ነበር፤ እዚያም ብዙ ሀብት አገኙ፤ ብዙ ልጆችም ወለዱ።
28ያዕቆብ ዐሥራ ሰባት ዓመት በግብጽ አገር ኖረ፤ ዕድሜውም መቶ አርባ ሰባት ዓመት ሆኖት ነበር። 29ያዕቆብ የሚሞትበት ቀን በተቃረበ ጊዜ ልጁን ዮሴፍን አስጠርቶ እንዲህ አለው፤ “በፊትህ ሞገስን አግኝቼ ከሆነ፥ በምሞትበት ጊዜ በግብጽ ምድር እንዳትቀብረኝ፥ እጅህን በጒልበቴ ላይ አኑረህ በመሐላ ቃል ግባልኝ። 30አባቶቼ በተቀበሩበት መቃብር መቀበር ስለምፈልግ በምሞትበት ጊዜ ከግብጽ አገር ወስደህ፥ እነርሱ በተቀበሩበት ስፍራ ቅበረኝ።” #ዘፍ. 49፥29-32፤ 50፥6።
ዮሴፍም “እሺ እንዳልከኝ አደርጋለሁ” አለው።
31ያዕቆብም “ይህን እንደምታደርግ በመሐላ ቃል ግባልኝ” አለው። ዮሴፍ ይህንኑ በመሐላ አረጋገጠለት፤ ያዕቆብም በመኝታው ላይ እንዳለ በመስገድ እግዚአብሔርን አመሰገነ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘፍጥረት 47: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997