የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፍጥረት 46

46
ያዕቆብ ከነቤተሰቡ ወደ ግብጽ መሄዱ
1ያዕቆብ ጓዙን ሁሉ ይዞ ተነሣ፤ ቤርሳቤህም በደረሰ ጊዜ ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ መሥዋዕት አቀረበ።
2እግዚአብሔር፥ ሌሊት በራእይ ተገለጠለትና “ያዕቆብ! ያዕቆብ!” ብሎ ጠራው።
እርሱም “አቤት ጌታ ሆይ፥ እነሆ አለሁ” አለ።
3እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “እኔ የአባትህ አምላክ፥ እግዚአብሔር ነኝ፤ ወደ ግብጽ ለመሄድ አትፍራ፤ እኔ ዘርህን በግብጽ አገር ታላቅ ሕዝብ አደርገዋለሁ፤ 4እኔ ወደ ግብጽ አብሬህ እሄዳለሁ፤ ወደዚህ ምድርም ትውልድህን መልሼ አመጣለሁ፤ በምትሞትበትም ጊዜ ዮሴፍ በአጠገብህ ይገኛል።”
5ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሥቶ ወደ ግብጽ ጒዞ ጀመረ፤ ልጆቹም አባታቸውን ያዕቆብን፥ ሕፃናት ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን የግብጽ ንጉሥ በላካቸው ሠረገሎች አሳፍረው፥ 6ከብቶቻቸውንና በከነዓን ያፈሩትን ሀብት ሁሉ ይዘው ወደ ግብጽ ሄዱ፤ በዚህ ዐይነት ያዕቆብ ቤተሰቡን ሁሉ ይዞ ወደ ግብጽ ሄደ፤ #ሐ.ሥ. 7፥15። 7አብረው የሄዱትም ወንዶች ልጆቹ፥ ሴቶች ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ናቸው።
8ከእስራኤል ጋር ወደ ግብጽ የወረዱት የእስራኤላውያን ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው፦
የያዕቆብ የበኲር ልጅ ሮቤል፥
9የሮቤል ልጆች፦ ሔኖክ፥ ፋሉ፥ ሔጽሮንና ካርሚ ናቸው።
10የስምዖን ልጆች፦ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ጾሐርና ከከነዓናዊቷ ሴት የተወለደው ሻኡል ናቸው።
11የሌዊ ልጆች፦ ጌርሾን፥ ቀዓትና መራሪ ናቸው።
12የይሁዳ ልጆች፦ ዔር፥ ኦናን፥ ሴላ፥ ፋሬስና ዛራሕ ናቸው፤ ዔርና ኦናን ግን በከነዓን ምድር ሞተዋል።
የፋሬስ ልጆች ሔጽሮንና ሐሙል ናቸው።
13የይሳኮር ልጆች፦ ቶላዕ፥ ፉዋ፥ ያሹብና ሺምሮን ናቸው።
14የዛብሎን ልጆች፦ ሴሬድ፥ ኤሎንና ያሕለኤል ናቸው።
15እነዚህ ወንዶች ልጆችና ሴቷም ልጅ ዲና በመስጴጦምያ ሳሉ ልያ ለያዕቆብ የወለደችለት ናቸው። ያዕቆብ ከልያ ያፈራቸው ልጆችና የልጅ ልጆች ሠላሳ ሦስት ናቸው።
16የጋድ ልጆች፦ ጸፎን፥ ሐጊ፥ ሹኒ፥ ኤጽቦን፥ ዔሪ፥ አሮድና አርኤሊ ናቸው።
17የአሴር ልጆች፦ ይምና፥ ይሽዋ፥ ይሽዊና በሪዓ ናቸው። እኅታቸው ሤራሕ ትባላለች።
የበሪዓ ልጆች ደግሞ ሔቤርና ማልኪኤል ናቸው።
18እነዚህ ዐሥራ ስድስቱ ላባ ለልጁ ለልያ በሞግዚትነት ከሰጣት ከዚልፋ የተወለዱ የያዕቆብ ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው።
19ያዕቆብ ከራሔል የወለዳቸው ዮሴፍና ብንያም ናቸው።
20የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ናቸው፤ እነርሱም ዮሴፍ በግብጽ ምድር ከኦን
ከተማ ካህን ከጶጢፌራ ሴት ልጅ ከአስናት የወለዳቸው ናቸው። #ዘፍ. 41፥50-52።
21የብንያም ልጆች፦ ቤላዕ፥ ቤኬር፥ አሽቤል፥ ጌራ፥ ናዕማን፥ ኤሒ፥ ሮሽ፥ ሙፊም፥
ሑፊምና አረድ ናቸው።
22እነዚህ ዐሥራ አራቱ ያዕቆብ ከራሔል የወለዳቸው ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው።
23የዳን ልጅ ሑሺም ነው።
24የንፍታሌም ልጆች፦ ያሕጽኤል፥ ጉኒ፥ ዬጼርና ሺሌም ናቸው።
25እነዚህ ሰባቱ ላባ ለልጁ ለራሔል ከሰጣት ከባላ የተወለዱ የያዕቆብ ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው።
26ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብጽ የሄዱት የያዕቆብ ቤተሰቦች ሥልሳ ስድስት ናቸው፤
ይህም የልጆቹን ሚስቶች ቊጥር ሳይጨምር ነው።
27ለዮሴፍ በግብጽ ከተወለዱት ከሁለቱ ወንዶች ልጆች ጋር፥ ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብጽ የገቡት የያዕቆብ ልጆችና የልጅ ልጆች ቊጥር በአጠቃላይ ሰባ ነበር። #ሐ.ሥ. 7፥14።
ያዕቆብና ቤተሰቡ በግብጽ አገር
28በጌሴም ምድር እንዲቀበለው ያዕቆብ ይሁዳን ወደ ዮሴፍ አስቀድሞ ላከው፤ እነርሱ ጌሴም በደረሱ ጊዜ፥ 29ዮሴፍ አባቱን ለመገናኘት በሠረገላው ተቀምጦ ወደዚያ ሄደ፤ በተገናኙም ጊዜ ዮሴፍ በአባቱ አንገት ላይ ተጠምጥሞ ለብዙ ጊዜ አለቀሰ።
30ያዕቆብ ዮሴፍን “እንግዲህ በሕይወት መኖርህን በዐይኔ አይቼ አረጋገጥኩ፤ ብሞት እንኳ ግድ የለኝም” አለው።
31ከዚህ በኋላ ዮሴፍ ወንድሞቹንና የቀረውን የአባቱን ቤተሰብ እንዲህ አላቸው፤ “ወደ ፈርዖን ልሂድና ‘በከነዓን ምድር ይኖሩ የነበሩት ወንድሞቼና የቀሩትም የአባቴ ቤተሰቦች ወደ እኔ መጥተዋል፤ 32እነርሱ እንስሶችን የማርባት ችሎታ ያላቸው ከብት ጠባቂዎች ናቸው፤ በጎቻቸውንና ፍየሎቻቸውን፥ ከብቶቻቸውን ያላቸውን ንብረት ሁሉ ይዘው መጥተዋል’ ብዬ ልንገረው። 33እናንተም ፈርዖን አስጠርቶ ‘ሥራችሁ ምንድን ነው?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፥ 34‘እኛ ልክ እንደ ቀድሞ አባቶቻችን ከልጅነታችን ጀምሮ የምንተዳደረው በግ በማርባት ነው’ ብላችሁ መልሱለት። በግ አርቢዎች በግብጻውያን ዘንድ የተናቁ ስለ ሆኑ ይህን በመናገር በጌሴም ምድር ለመኖር ፈቃድ ታገኛላችሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ