በምድርም ሁሉ እህል አልነበረም፤ ራብ እጅግ ጸንቶአልና፤ ከራብም የተነሣ የግብፅ ምድርና የከነዓን ምድር ተጐዳ። ዮሴፍም ከግብፅ ምድርና ከከነዓን ምድር በእህል ሸመታ የተገኘውን ብሩን ሁሉ አከማቸ፤ ዮሴፍም ብሩን ወደ ፈርዖን ቤት አስገባው። ብሩም በግብፅ ምድርና በከነዓን ምድር አለቀ፤ የግብፅ ሰዎችም ሁሉ ወደ ዮሴፍ መጡ፤ እንዲህ ሲሉ፥ “በፊትህ እንዳንሞት እህል ስጠን፤ ብሩ አልቆብናልና።” ዮሴፍም፥ “ከብቶቻችሁን አምጡልኝ፤ ብር ከአለቀባችሁ በከብቶቻችሁ ፈንታ እህል እሰጣችኋለሁ” አለ። ከብቶቻቸውንም ወደ ዮሴፍ አመጡ፤ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው፥ በበጎቻቸውም፥ በላሞቻቸውም፥ በአህዮቻቸውም ፈንታ እህልን ሰጣቸው፤ በዚያች ዓመትም ስለ ከብቶቻቸው ሁሉ ፈንታ እህልን መገባቸው። ያችም ዓመት ተፈጸመች፤ በሁለተኛዋም ዓመት ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ አሉት፥ “እኛ ለጌታችን ሞተን እንዳናልቅበት እህል ስጠን፤ ብሩ በፍጹም አለቀ፤ ንብረታችንና ከብታችንም በጌታችን ዘንድ ነው፤ ከሰውነታችንና ከምድራችን በቀር በጌታችን ፊት አንዳች የቀረን የለም፤ እንግዲህ እኛ በፊትህ እንዳንሞት፥ ምድራችንም እንዳትጠፋ፥ እኛንም፥ ምድራችንንም በእህል ግዛን፤ እኛም ለፈርዖን አገልጋዮች እንሁን፤ ምድራችንም ለእርሱ ትሁን፤ እኛ እንድንድን፥ እንዳንሞትም፥ ምድራችንም እንዳትጠፋ እንዘራ ዘንድ ዘር ስጠን።” ዮሴፍም የግብፅን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛ፤ የግብፅ ሰዎች ሁሉ ራብ ስለጸናባቸው ርስታቸውን ሸጠዋልና፤ ምድሪቱ ለፈርዖን ሆነች። ሕዝቡንም ሁሉ ከግብፅ ዳርቻ አንሥቶ እስከ ሌላው ዳርቻዋ ድረስ አገልጋዮች አደረጋቸው። ዮሴፍ የካህናትን ምድር ብቻ አልገዛም፤ ፈርዖን ለካህናቱ ድርጎ ይሰጣቸው ነበርና፥ ፈርዖንም የሰጣቸውን ድርጎ ይበሉ ነበር፤ ስለዚህም ምድራቸውን አልሸጡም። ዮሴፍም የግብፅን ሰዎች ሁሉ እንዲህ አላቸው፥ “እነሆ ዛሬ እናንተንና ምድራችሁን ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁ፤ ለእናንተ ዘር ውሰዱና ምድሪቱን ዝሩ፤ በመከርም ጊዜ ፍሬውን ከአምስት እጅ አንዱን እጅ ለፈርዖን ስጡ፤ አራቱም እጅ ለእናንተ ለራሳችሁ፥ ለእርሻው ዘርና ለእናንተ ምግብ፥ ለቤተ ሰባችሁም ሁሉ ሲሳይ ይሁን።” እነርሱም፥ “አንተ አዳንኸን፤ በጌታችንም ፊት ሞገስን አገኘን፤ ለፈርዖንም አገልጋዮች እንሆናለን” አሉት። ዮሴፍም ለፈርዖን ካልሆነችው ከካህናቱ ምድር በቀር አምስተኛው እጅ ለፈርዖን እንዲሆን በግብፅ ምድር እስከ ዛሬ ሕግ አደረጋት። እስራኤልም በግብፅ ምድር በጌሤም ሀገር ተቀመጠ፤ እርስዋም ርስታቸው ሆነች፤ በዙ፤ እጅግም ተባዙ።
ኦሪት ዘፍጥረት 47 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 47:13-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos