ዕዝራ 7:6-10
ዕዝራ 7:6-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ይህ ዕዝራ ከባቢሎን መጣ፤ እርሱም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን ሕግ በሚገባ የሚያውቅ የሕግ መምህር ነበር። የአምላኩ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች፣ የጠየቀውን ሁሉ ንጉሡ ፈቀደለት። እንደዚሁም አንዳንድ እስራኤላውያን፣ ከካህናት፣ ከሌዋውያን፣ ከመዘምራን፣ ከበር ጠባቂዎችና ከቤተ መቅደሱ አገልጋዮች ጋር በመሆን በንጉሡ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት በሰባተኛው ዓመት ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። ዕዝራ በንጉሡ ሰባተኛ ዓመት በአምስተኛው ወር ኢየሩሳሌም ደረሰ። መልካሚቱ የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች፣ ከባቢሎን በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ተነሥቶ በአምስተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ኢየሩሳሌም ደረሰ። ዕዝራ የእግዚአብሔርን ሕግ በማጥናትና በማድረግ፣ ለእስራኤልም ሥርዐቱንና ሕጉን በማስተማር ራሱን ፈጽሞ ሰጥቶ ነበር።
ዕዝራ 7:6-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይህ ዕዝራ ከባቢሎን ወጣ፤ የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር በሰጠው በሙሴ ሕግ ፈጣን ጸሐፊ ነበረ፤ የአምላኩም የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና ንጉሡ ያሻውን ሁሉ ሰጠው። ከእስራኤልም ልጆች ከካህናቱ፥ ከሌዋውያኑ፥ ከመዘምራኑ፥ ከበረኞቹና ከናታኒም በንጉሡ በአርጤክስስ በሰባተኛው ዓመት አያሌዎች ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። በንጉሡም በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ። ዕዝራ በመጀመሪያውም ወር በአንደኛው ቀን ከባቢሎን ሊወጣ ጀመረ፤ መልካሚቱም የአምላኩ እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና በአምስተኛ ወር በመጀመሪያው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ። ዕዝራም የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፥ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።
ዕዝራ 7:6-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ይህም ዕዝራ ከባቢሎን ወጣ፤ እርሱም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠውን ሕግ ዐዋቂ ነበረ፤ የአምላኩም የእግዚአብሔር እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና ንጉሡ ያሻውን ሁሉ ሰጠው። ከእስራኤልም ልጆች ከካህናቱም፥ ከሌዋውያኑም፥ ከመዘምራኑም፥ ከበረኞቹም፥ ከናታኒምም በንጉሡ በአርተሰስታ በሰባተኛው ዓመት ዐያሌዎች ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። በንጉሡም በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ። በመጀመሪያውም ወር በአንደኛው ቀን ከባቢሎን ሊወጡ ጀመሩ፤ መልካሚቱም የአምላኩ እጅ በእርሱ ላይ ነበረችና በአምስተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ደረሱ። ዕዝራም የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፥ ለእስራኤልም ሥርዐትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።
ዕዝራ 7:6-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ይህ ዕዝራ ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ እርሱም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ሕግ ሊቅ ነበር፤ የእግዚአብሔር ኀይል ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ ንጉሡ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ሰጠው። እንዲሁም ንጉሥ አርጤክስስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ከእስራኤል ልጆች መካከል ካህናት፥ ሌዋውያን፥ መዘምራን፥ በር ጠባቂዎችና የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ከዕዝራ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። ዕዝራ ንጉሡ አርጤክስስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ። የእግዚአብሔር ታላቅ ኀይል በእርሱ ላይ ስለ ነበረ ከባቢሎን በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ተነሥቶ ኢየሩሳሌም በአምስተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ደረሰ። ዕዝራ መላ ሕይወቱን የእግዚአብሔርን ሕግ በማጥናትና በተግባር በመተርጐም፥ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ትእዛዞች፥ ሕጎችና ሥርዓቶች ለመላው የእስራኤል ሕዝብ በማስተማር ያውለው ነበር።
ዕዝራ 7:6-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ይህ ዕዝራ ከባቢሎን መጣ፥ የእስራኤል አምላክ ጌታ ለሙሴ በሰጠው ሕግ ችሎታ ያለው ጸሐፊ ነበረ፤ የአምላኩ የጌታ እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች ንጉሡ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ሰጠው። በንጉሡ በአርጤክስስ በሰባተኛው ዓመት ከእስራኤል ልጆች አንዳንዶቹ፥ ከካህናቱም አንዳንዶቹ፥ ሌዋውያኑ፥ መዘምራኑ፥ በር ጠባቂዎቹና፥ የቤተ መቅደስ አገልጋዮቹ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። በንጉሡ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛውም ወር ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። በመጀመሪያው ወር በአንደኛው ቀን ከባቢሎን መውጣት ጀመረ፥ መልካሚቱም የአምላኩ እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች በአምስተኛ ወር በመጀመሪያው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ። ዕዝራም የጌታን ሕግ ሊፈልግና ሊያደርግው፥ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ሊያስተምር ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።