መጽሐፈ ዕዝራ 7
7
የዕዝራ መምጣትና የሠራው ሥራ
1ከነዚህም ነገሮች በኋላ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ መንግሥት ዕዝራ የሠራያ ልጅ፥ የዓዛርያ ልጅ፥ የሒልቂያ ልጅ፥ 2የሻሉም ልጅ፥ የጻዶቅ ልጅ፥ የአሒጡብ ልጅ፥ 3የአማርያ ልጅ፥ የዓዛርያ ልጅ፥ የመራዮት ልጅ፥ 4የዘራሕያ ልጅ፥ የዑዚ ልጅ፥ የቡቂ ልጅ፥ 5የአቢሹዓ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ፥ የኤልዓዛር ልጅ፥ የታላቁ ካህን የአሮን ልጅ፥ 6ይህ ዕዝራ ከባቢሎን መጣ፥ የእስራኤል አምላክ ጌታ ለሙሴ በሰጠው ሕግ ችሎታ ያለው ጸሐፊ ነበረ፤ የአምላኩ የጌታ እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች ንጉሡ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ሰጠው። 7በንጉሡ በአርጤክስስ በሰባተኛው ዓመት ከእስራኤል ልጆች አንዳንዶቹ፥ ከካህናቱም አንዳንዶቹ፥ ሌዋውያኑ፥ መዘምራኑ፥ በር ጠባቂዎቹና፥ የቤተ መቅደስ አገልጋዮቹ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ። 8በንጉሡ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛውም ወር ወደ ኢየሩሳሌም መጣ። 9በመጀመሪያው ወር በአንደኛው ቀን ከባቢሎን መውጣት ጀመረ፥ መልካሚቱም የአምላኩ እጅ በእርሱ ላይ ስለ ነበረች በአምስተኛ ወር በመጀመሪያው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ። 10ዕዝራም የጌታን ሕግ ሊፈልግና ሊያደርግው፥ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ሊያስተምር ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።
አርጤክስስ ለዕዝራ የሰጠው ደብዳቤ
11የጌታን ትእዛዝ ቃልና ለእስራኤል የሆነውን ሥርዓት ይጽፍ ለነበረው ለጸሐፊው ለካህኑ ለዕዝራ ንጉሡ አርጤክስስ የሰጠው የደብዳቤው ግልባጭ ይህ ነው፦ 12“ከንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ ለሰማያት አምላክ ሕግ ጸሐፊ ለካህኑ ዕዝራ፤ አሁንም 13በመንግሥቴ ውስጥ ካሉ ከእስራኤል ሕዝብ፥ ከካህናቱና ከሌዋውያኑም ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ የሚፈልግ ሁሉ ከአንተ ጋር እንዲሄድ አዝዣለሁ። 14በእጅህ እንዳለችው እንደ አምላክህ ሕግ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን እንድትመረምር በንጉሡና በሰባት አማካሪዎቹ ተልከሃል፤ 15ንጉሡና አማካሪዎቹ መኖሪያው በኢየሩሳሌም ለሆነው ለእስራኤል አምላክ በፈቃዳቸው የሰጡትን ብርና ወርቅ ይዘህ ሂድ፤ 16በባቢሎንም አውራጃ ሁሉ የምታገኘውን ብርና ወርቅ በሙሉ፥ ሕዝቡና ካህናቱም በኢየሩሳሌም ላለው ለአምላካቸው ቤት በፈቃዳቸው የሚሰጡትን ይዘህ ሂድ። 17ስለዚህ በዚህ ገንዘብ ወይፈኖችን፥ አውራ በጎችንና ጠቦቶችን ከእህል ቁርባኖቻቸውና ከመጠጥ ቁርባኖቻቸው ጋር ተግተህ ግዛ፥ በኢየሩሳሌምም ባለው በአምላካችሁ ቤት መሠዊያ ላይ አቅርባቸው። 18የሚቀረውን ብርና ወርቅ አንተና ወንድሞችህ እንደ አምላካችሁ ፈቃድ ለማድረግ ደስ የሚላችሁን ነገር አድርጉ። 19ለአምላክህ ቤት አገልግሎት የተሰጠህን ዕቃዎች በኢየሩሳሌም አምላክ ፊት አቅርብ። 20ከዚህ በላይ ለአምላክህ ቤት የሚያስፈልግህን ነገር ሁሉ ከንጉሡ ቤተ መዛግብት ውሰድ። 21እኔም ንጉሡ አርጤክስስ በወንዝ ማዶ ለምትገኙ ገንዘብ ያዦች ሁሉ፦ የሰማያት አምላክ ሕግ ጸሐፊ የሆነው ካህኑ ዕዝራ የሚጠይቃችሁን ሁሉ በትጋት እንድትሰጡት ይህን ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፤ 22እስከ መቶ መክሊት ብር፥ እስከ መቶ የቆሬስ መስፈሪያ ስንዴ፥ እስከ መቶ የባዶስ መስፈሪያ የወይን ጠጅ፥ እስከ መቶም የባዶስ መስፈሪያ ዘይት፥ ጨውም የሚፈልገውን ያህል ሳትጽፉ ስጡት። 23በንጉሡና በልጆቹ መንግሥት ላይ ቁጣ እንዳይሆን፥ የሰማያት አምላክ የሚያዘው ሁሉ ልክ እንዳዘዘው ለሰማያት አምላክ ቤት ይደረግ። 24ደግሞም በካህናቱ፥ በሌዋውያኑ፥ በመዘምራኑ፥ በበር ጠባቂዎቹና፥ በቤተ መቅደስ አገልጋዮቹ በዚህም በእግዚአብሔር ቤት በሚሠሩ አገልጋዮች ላይ ግብርና ቀረጥ መጥንም ለመጣል ሥልጣን እንደሌላችሁ እወቁ። 25አንተም ዕዝራ፥ በእጅህ እንዳለው እንደ አምላክህ ጥበብ መጠን በወንዝ ማዶ ለሚገኙ ሕዝቦች ሁሉ የአምላክህን ሕግ በሚያውቁ ሁሉ ላይ እንዲፈርዱ ዳኞችንና ፈራጆችን ሹምላቸው፥ የማያውቁትንም አስተምሩአቸው። 26የአምላክህን ሕግና የንጉሡን ትእዛዝ በማያደርግ በማንም ላይ ሞት ወይም ስደት ወይም ንብረት መወረስ ወይም ግዞት በፅኑ ይፈረድበት።”
27በኢየሩሳሌም ያለውን የጌታን ቤት እንዲያሳምር እንደዚህ ያለውን ነገር በንጉሡ ልብ ያኖረ፥ የአባቶቻችን አምላክ ጌታ ይባረክ። 28በንጉሡ፥ በአማካሪዎቹና በኃያላን ባለሥልጣኖቹም ሁሉ ፊት ፅኑ ፍቅሩን በእኔ ላይ ዘረጋ፤ እኔም በላዬ ባለችው በእግዚአብሔር እጅ ራሴን አበረታሁ፥ ከእኔም ጋር እንዲወጡ ከእስራኤል አለቆችን ሰበሰብሁ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ 7: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ