መጽሐፈ ዕዝራ 6
6
የዳርዮስ ትእዛዝ
1በዚን ጊዜ ንጉሡ ዳርዮስ ትእዛዝ አስተላለፈ። በባቢሎን መዛግብት ባሉበት ቤተ መጻሕፍት ምርመራ ተደረገ። 2በሜዶን አውራጃ ባለው አሕምታ በሚባል ከተማ በቤተ መንግሥት ውስጥ አንድ ጥቅል ተገኘ፥ በውስጡም እንዲህ የሚል ተጽፎ ነበር፤ “ማስታወሻ 3በንጉሡ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ በኢየሩሳሌም ስላለው ስለ እግዚአብሔር ቤት እንዲህ ብሎ አዘዘ፥ መሥዋዕት የሚሠዋበት ቦታ፥ ይህ ቤት ይሠራ፥ በጽኑም ይመሥረት፤ ርዝመቱ ስድሳ ክንድ ስፋቱም ስድሳ ክንድ ይሁን። 4በሦስት መደዳ ታላላቅ ድንጋይ፥ አንድ መደዳ እንጨት ይደረግ፤ ወጪውም ከንጉሡ ቤት ይሰጥ። 5ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ካለው መቅደስ ወስዶ ወደ ባቢሎን ያመጣው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃዎች ይመለስ፥ በኢየሩሳሌምም ወዳለው መቅደስ ወደ ስፍራው ይወሰድ፥ በእግዚአብሔር ቤት ይኑር።”
6“አሁንም በወንዝ ማዶ ያለውን አካባቢ ገዢ የሆንህ ታትናይ፥ ሽታርቦዝናይ በወንዝ ማዶም ያሉ ተባባሪዎቻቸው ባለ ሥልጣናት ከዚያ ራቁ፤ 7ይህም የእግዚአብሔር ቤት እንዲሠራ ተዉ፥ የአይሁድ አለቃና የአይሁድም ሽማግሌዎች ይህን የእግዚአብሔርን ቤት በስፍራው እንዲሠሩ ተዉአቸው። 8ይህን የእግዚአብሔርን ቤት እንዲሠሩ ለአይሁድ ሽማግሌዎች የምታደርጉትን አዝዣለሁ፥ በወንዝ ማዶ ካለው አገር ከሚመጣው ግብር ከንጉሡ ገንዘብ ለእነዚህ ሰዎች ወጪውን በትጋት ይሰጣቸው፥ ሥራም እንዳታስፈቱአቸው። 9ለሰማይ አምላክ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያስፈልገውን፥ ወይፈኖችና አውራ በጎች ጠቦቶችም፥ በኢየሩሳሌም እንዳሉ እንደ ካህናቱ ቃል ስንዴና ጨው የወይን ጠጅና ዘይት ዕለት ዕለት ያለማቋረጥ ስጡአቸው። 10ይህም ለሰማያት አምላክ መልካም መዓዛ እንዲያቀርቡ፥ ለንጉሥና ለልጆቹ ሕይወትም እንዲጸልዩ ነው። 11ይህንም ትእዛዝ የሚያደናቅፍ ሁሉ፥ ምሰሶ ከቤቱ ተነቅሎ እርሱ ይሰካበት፥ ቤቱም የጉድፍ መጣያ ይሁን ብዬ አዝዣለሁ። 12ይህን ሊለውጡ፥ በኢየሩሳሌም ያለውንም የእግዚአብሔርን ቤት ሊያፈርሱ እጃቸውን የሚዘረጉትን ነገሥታትና አሕዛብ ሁሉ፥ ስሙን በዚያ ያኖረው አምላክ ያጥፋው። እኔ ዳርዮስ ይህን አዝዣለሁ፥ በትጋት ይፈጸም።”
የቤተ መቅደሱ ግንባታ ፍጻሜና የምረቃ በዓል
13ከዚያ በኋላ በወንዝ ማዶ ያለ አካባቢ ገዢ ታትናይ፥ ሽታርቦዝናይና ተባባሪዎቻቸው ንጉሡ ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ እንዲሁ ተግተው አደረጉ። 14#ሐጌ 1፥1፤ ዘካ. 1፥1።የአይሁድም ሽማግሌዎች በነቢዩ ሐጌና በዒዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት እየተበረታቱ ሠሩ ተከናወነላቸውም። በእስራኤል አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ቂሮስ ትእዛዝ እንደ ዳርዮስ እንደ አርጤክስስ የፋርስ ንጉሥ ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ። 15ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ።
16የእስራኤል ልጆች፥ ካህናትና ሌዋውያን የቀሩትም ምርኮኞች፥ የዚህን የእግዚአብሔርን ቤት ምረቃ በደስታ አከበሩ። 17ለዚህ የእግዚአብሔር ቤት ምረቃ አንድ መቶ ወይፈኖች፥ ሁለት መቶ አውራ በጎች፥ አራት መቶ የበግ ጠቦቶችን፥ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት እንደ እስራኤል ነገዶች ቍጥር ለእስራኤል ሁሉ ዐሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ። 18በሙሴም መጽሐፍ በተጻፈው መሠረት በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ካህናቱን በየማዕረጋቸው ሌዋውያኑንም በየክፍላቸው መደቡአቸው።
የፋሲካ በዓል
19 #
ዘፀ. 12፥1-20። ምርኮኞቹም በመጀመሪያው ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አከበሩ። 20ካህናቱና ሌዋውያኑ እንደ አንድ ሰው ሆነው እራሳቸውን አነጹ፥ ሁሉም ንጹሐን ነበሩ፥ ከምርኮ ለተመለሱ ሕዝቦች ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸው ለካህናቱና ለራሳቸው ፋሲካውን አረዱ። 21ከምርኮ የተመለሱት የእስራኤል ልጆች፥ የእስራኤልን አምላክ ጌታን ለመፈለግ ራሳቸውን ከምድር አሕዛብ ርኩሰት ለይተው ወደ እነርሱ መጥተው የነበሩት ሁሉ በሉት። 22ጌታ ደስ አሰኝቶአቸዋልና፥ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ቤትም ለመሥራት እጃቸውን እንዲያጸኑ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አከበሩ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ 6: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ