መጽሐፈ ዕዝራ 7
7
የዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም መምጣት
1ከብዙ ጊዜ በኋላ አርጤክስስ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት በሆነበት ዘመን፥ ዕዝራ ተብሎ የሚጠራ አንድ ሰው በዚያ ይኖር ነበር፤ የእርሱም የቀድሞ አባቶች የትውልድ ሐረግ እስከ ታላቁ ሊቀ ካህናት አሮን ድረስ ሲቈጠር እንደሚከተለው ነው፦ ዕዝራ የሠራያ ልጅ ሲሆን፥ ሠራያ የዐዛርያ ልጅ፥ ዐዛርያ የሒልቂያ ልጅ፥ ሒልቂያ የሻሉም ልጅ፥ 2ሻሉም የሳዶቅ ልጅ፥ ሳዶቅ የአሒጡብ ልጅ፥ አሒጦብ የአማርያ ልጅ፥ 3አማርያ የዓዛርያ ልጅ፥ ዓዛርያ የመራዮት ልጅ፥ መራዮት የዘራሕያ ልጅ፥ 4ዘራሕያ የዑዚ ልጅ፥ ዑዚ የቡቂ ልጅ፥ 5ቡቂ የአቢሹዓ ልጅ፥ አቢሹዓ የፊንሐስ ልጅ፥ ፊንሐስ የአልዓዛር ልጅ፥ አልዓዛር የሊቀ ካህናቱ የአሮን ልጅ ነው።
6ይህ ዕዝራ ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ እርሱም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ሕግ ሊቅ ነበር፤ የእግዚአብሔር ኀይል ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ ንጉሡ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ሰጠው። 7እንዲሁም ንጉሥ አርጤክስስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ከእስራኤል ልጆች መካከል ካህናት፥ ሌዋውያን፥ መዘምራን፥ በር ጠባቂዎችና የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ከዕዝራ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 8ዕዝራ ንጉሡ አርጤክስስ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት በአምስተኛው ወር ወደ ኢየሩሳሌም ደረሰ። 9የእግዚአብሔር ታላቅ ኀይል በእርሱ ላይ ስለ ነበረ ከባቢሎን በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ተነሥቶ ኢየሩሳሌም በአምስተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ደረሰ። 10ዕዝራ መላ ሕይወቱን የእግዚአብሔርን ሕግ በማጥናትና በተግባር በመተርጐም፥ እንዲሁም የእግዚአብሔርን ትእዛዞች፥ ሕጎችና ሥርዓቶች ለመላው የእስራኤል ሕዝብ በማስተማር ያውለው ነበር።
ንጉሠ ነገሥቱ አርጤክስስ ለዕዝራ የሰጠው የጽሑፍ ፈቃድ
11እግዚአብሔር ለእስራኤል የሰጣቸውን ሕግና ትእዛዞች ሁሉ የሚያውቅ ሊቅ ለነበረው ለካህኑ ዕዝራ፥ ንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ የሰጠው ደብዳቤ ከዚህ የሚከተለው ነው፦
12“ከንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ፥ የሰማይ አምላክ የእግዚአብሔርን ሕግ በማጥናት ረገድ ታላቅ ምሁር ለሆነው ለካህኑ ዕዝራ፦ ሰላም ላንተ ይሁን፤
13“እኔ በማስተዳድረው የንጉሠ ነገሥት መንግሥት ግዛት ውስጥ የሚገኙና ከአንተ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ የሚፈልጉ እስራኤላውያን፥ ካህናትና ሌዋውያን ሁሉ እንዲመለሱ ፈቅጃለሁ፤ 14ከዚህም ጋር እኔ ራሴ ከሰባቱ አማካሪዎቼ ጋር በአንድነት ያስተላለፍነውን ውሳኔ ለአንተ የተሰጠው የአምላክህ ሕግ በተግባር መፈጸሙን እየተመለከትህ፥ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያለውን ሁኔታ እንድትመረምር ልኬሃለሁ። 15በተጨማሪም በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ለተሠራለት ለእስራኤል አምላክ እኔና አማካሪዎቼ በበጎ ፈቃድ የሰጠነውን ብርና ወርቅ ይዘህ ሂድ። 16ከዚህም ሁሉ ጋር አንተ ራስህ ከባቢሎን ምድር የሰበሰብከውን ወርቅና ብር፥ የእስራኤል ሕዝብና ካህናታቸውም ጭምር በኢየሩሳሌም በተሠራው የአምላካቸው ቤተ መቅደስ እንዲቀርብላቸው የሚፈልጉትን መባ ሁሉ ይዘህ ሂድ። 17ይህም ገንዘብ በጥንቃቄ ሥራ ላይ እንዲውል አድርግ፤ ወይፈኖችን፥ የበግ አውራዎችንና ጠቦቶችን፥ ለመባ የሚሆነውን እህልና የወይን ጠጅ ጭምር በኢየሩሳሌም በተሠራው በአምላክህ ቤተ መቅደስ ውስጥ በሚገኘው መሠዊያ ላይ የሚቀርበውን መባ ሁሉ ግዛበት። 18ከዚያ የሚተርፈውንም ብርና ወርቅ እንደ አምላካችሁ ፈቃድ አንተና ወገኖችህ ለምትፈልጉት ነገር እንዲውል አድርግ። 19በአምላክህ ቤተ መቅደስ ውስጥ አገልግሎት እንዲከናወንባቸው የተሰጡህን ንዋያተ ቅድሳት በኢየሩሳሌም ለሚመለከው አምላክ አቅርብ። 20ለቤተ መቅደሱ መገልገያ የሚያስፈልግህንም ሌላውን ነገር ሁሉ ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ልትወስድ ትችላለህ።
21“እኔ ንጉሥ አርጤክስስ ከኤፍራጥስ ምዕራብ የምትገኙ በጅሮንዶች ሁሉ በሰማይ አምላክ ሕግ ምሁር የሆነው ካህኑ ዕዝራ የሚጠይቃችሁን ሁሉ ትሰጡት ዘንድ አዝዣለሁ። 22እስከ ሦስት ሺህ አራት መቶ ኪሎ ያኽል የሚመዝን ብር፥ እስከ ዐሥር ሺህ ኪሎ ስንዴ፥ እስከ ሁለት ሺህ ሊትር የወይን ጠጅ፥ እስከ ሁለት ሺህ ሊትር የወይራ ዘይትና የሚያስፈልገውንም ያኽል ጨው ስጡት። 23በንጉሡና በልጆቹ ላይ ቊጣ እንዳይመጣ የሰማይ አምላክ ለቤተ መቅደሱ የሚያዘው ሁሉ በጥንቃቄ መፈጸም አለበት። 24እንዲሁም ከካህናት፥ ከሌዋውያን፥ ከመዘምራን፥ ከዘብ ጠባቂዎች፥ በአጠቃላይም ቤተ መቅደሱን የሚመለከት ማናቸውንም ሥራ ከሚያከናውኑት ወገኖች ሁሉ ላይ ቀረጥ፥ ግብርና ግዴታ የመጣል ሥልጣን የሌላችሁ መሆኑን እንድታውቁ።
25“አንተም ዕዝራ፥ አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህ ጥበብና ዕውቀት እየተመራህ፥ በአምላክህ በእግዚአብሔር ሕግ የሚመሩትን፥ በኤፍራጥስ ማዶ የሚገኙትን ሰዎች የሚመሩ አስተዳዳሪዎችንና ዳኞችን ሹምላቸው፤ ለማያውቁትም ሁሉ የአምላክህን ሕግ አስተምራቸው፤ 26ለእግዚአብሔር ሕግ ወይም ለመንግሥት ሕግ ሁሉ የማይታዘዝ ማንም ሰው ቢኖር በጥንቃቄ እየተመረመረ በሞት ወይም ከሀገር በመባረር ወይም ሀብት ንብረቱን በመወረስ ወይም በእስራት ይቀጣ።”
ዕዝራ እግዚአብሔርን ማመስገኑ
27ዕዝራ እንዲህ ሲል እግዚአብሔርን አመሰገነ፦ “የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን! በኢየሩሳሌም ለሚሠራው ለእግዚአብሔር ቤት ንጉሠ ነገሥቱ ክብር ለመስጠት እንዲፈቅድ ያደረገው እርሱ ነው፤ 28በእግዚአብሔርም ፈቃድ በንጉሠ ነገሥቱና በአማካሪዎቹ፥ በባለሥልጣኖቹም ሁሉ ዘንድ መወደድን አግኝቻለሁ፤ የአምላኬ የእግዚአብሔር ኀይል ከእኔ ጋር ስለ ሆነ ከእስራኤል የጐሣ መሪዎች ብዙዎቹ ከእኔ ጋር ተባብረው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ በማግባባት ለማስተማር አብቅቶኛል።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ 7: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997