መጽሐፈ ዕዝራ 8
8
ከዕዝራ ጋር ከስደት የተመለሰው ሕዝብ
1በንጉሡ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት ከእኔ ጋር ከባቢሎን የተመለሱት የቤተሰብ አለቆች በየትውልዳቸው እንደሚከተለው ነው፦
2-14ከፊንሐስ ጐሣ ጌርሾም፥ ከኢታማር ጐሣ ዳንኤል፥
ከዳዊት ጐሣ የሸካንያ ልጅ ሐጡሽ፥
ከፓርዖሽ ጐሣ ዘካርያስ ሲሆን፥ ከእርሱ ቤተሰብ ወገን የሆኑ አንድ መቶ ኀምሳ ወንዶች ተመዝግበዋል፤
ከፓሐትሞአብ ጐሣ የዘራሕያ ልጅ ኤልየሆዔናይ ከሁለት መቶ ወንዶች ጋር፥
ከዛቱ ጐሣ የያሐዚኤል ልጅ ሸካንያ ከሦስት መቶ ወንዶች ጋር፥
ከዓዲን ጐሣ የዮናታን ልጅ ዔቤድ ከኀምሳ ወንዶች ጋር፥
ከዔላም ጐሣ የዐታልያ ልጅ የሻዕያ ከሰባ ወንዶች ጋር፥
ከሸፋጥያ ጐሣ የሚካኤል ልጅ ዘባድያ ከሰማንያ ወንዶች ጋር፥
ከኢዮአብ ጐሣ የየሒኤል ልጅ አብድዩ ከሁለት መቶ ዐሥራ ስምንት ወንዶች ጋር፥
ከባኒ ጐሣ የዮሲፍያ ልጅ ሸሎሚት ከአንድ መቶ ሥልሳ ወንዶች ጋር፥
ከቤባይ ጐሣ የቤባይ ልጅ ዘካርያስ ከኻያ ስምንት ወንዶች ጋር፥
ከዓዝጋድ ጐሣ የሃቃጣን ልጅ ዮሐናን ከአንድ መቶ ዐሥር ወንዶች ጋር፥
ከአዶኒቃም ጐሣ ኤሊፌሌጥ፥ ይዒኤልና ሸማዕያ ከስድሳ ወንዶች ጋር፥
እነርሱም ዘግየት ብለው ተመልሰዋል፤
ከቢግዋይ ጐሣ ዑታይና ዛኩር ከሰባ ወንዶች ጋር።
ዕዝራ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች የሚሆኑ ሌዋውያንን ማግኘቱ
15እኔ ዕዝራ ወደ አሀዋ በሚፈሰው ወንዝ አጠገብ መላውን ጉባኤ ሰበሰብኩ፤ በዚያም ሰፍረን ለሦስት ቀኖች ቈየን፤ በዚያም ጉባኤ ውስጥ ከካህናት በቀር ሌዋውያን አለመኖራቸውን ተገነዘብኩ፤ 16ስለዚህም ኤሊዔዘር፥ አሪኤል፥ ሸማዕያ፥ ኤልናታን፥ ያሪብ፥ ኤልናታን፥ ናታን፥ ዘካርያስና መሹላም ተብለው ወደሚጠሩ ዘጠኝ መሪዎች፥ እንዲሁም ዮያሪብና ኤልናታን ተብለው ወደሚጠሩ ሁለት መምህራን ላክሁባቸው፤ 17እነርሱንም በካሲፍያ ለሚኖር ሕዝብ መሪ ወደ ሆነው ወደ ኢዶ በመላክ ኢዶና የቤተ መቅደስ ሠራተኞች የሆኑት ረዳቶቹ በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉ ሰዎችን ይልኩልን ዘንድ እንዲነግሩአቸው አደረግሁ። 18የእግዚአብሔር ታላቅ ኀይል ከእኛ ጋር ስለ ነበረ እነርሱ በቂ ችሎታ ያለውን፥ የማሕሊ ጐሣ የሆነውን ሼሬብያ ተብሎ የሚጠራውን ሌዋዊ ላኩልን፤ እርሱም ዐሥራ ስምንቱን ወንዶች ልጆቹንና ወንድሞቹን አስከትሎ ወደ እኛ መጣ። 19እንዲሁም ከመራሪ ጐሣ የሆኑትን ሐሻብያና የሻዕያ ተብለው የሚጠሩትን ሰዎች ቊጥራቸው ኻያ ከሆነ ዘመዶቻቸው ጋር ላኩልን። 20በተጨማሪም የቀድሞ አባቶቻቸው ሌዋውያንን ይረዱ ዘንድ በንጉሥ ዳዊትና በባለሟሎቹ ተሹመው የነበሩ ብዛታቸው ሁለት መቶ ኻያ የሆነ የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ነበሩ፤ እነርሱም በየስማቸው ተመዝግበዋል።
ሕዝቡ ጾምና ጸሎት እንዲያደርግ ዕዝራ ማዘዙ
21እግዚአብሔር ጒዞአችንን እንዲያቃናልን፥ እኛንና ልጆቻችንን፥ እንዲሁም ንብረታችንን ሁሉ እንዲጠብቅልን በእርሱ ፊት ራሳችንን ዝቅ አድርገን እንለምነው ዘንድ በዚያው በአሀዋ ወንዝ አጠገብ ጾም ዐወጅኩ። 22ከዚህ በፊት ለንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ ባስረዳሁት ጊዜ “አምላካችን እግዚአብሔር በእርሱ የሚታመኑትን ሁሉ ይባርካል፤ እርሱን የሚተዉትን ግን በብርቱ ይቀጣቸዋል” በማለት ገልጬለት ስለ ነበረ በመንገድ ከሚገጥሙን ጠላቶቻችን እንዲጠብቁን ወታደሮችንና ፈረሰኞችን ይሰጠን ዘንድ ንጉሡን ጠይቄው ቢሆን ኖሮ ባፈርኩ ነበር። 23ስለዚህም እግዚአብሔር ራሱ እንዲጠብቀን በጾምና በጸሎት ተማጠንነው፤ እርሱም ጸሎታችንን ሰማ።
ለቤተ መቅደስ የቀረበ ስጦታ
24መሪዎች ከሆኑት ካህናት መካከል ሼሬብያን፥ ሐሻብያንና ሌሎችንም ዐሥር ሰዎች መረጥሁ፤ 25ከዚህ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ፥ አማካሪዎቹ፥ ባለሟሎቹና በዚያ የተገኙት እስራኤላውያን ለቤተ መቅደስ መገልገያ ይሆን ዘንድ የሰጡትን ብር፥ ወርቅና ሌሎቹንም ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ በሚዛን መዝኜ ለእነዚህ ካህናት አስረከብኳቸው።
26-27ያስረከብኳቸውም የቤተ መቅደስ ንብረት ከዚህ የሚከተለው ነው፦
22000 ኪሎ የሚመዝን ብር፥
70 ኪሎ የሚመዝኑ አንድ መቶ ከብር የተሠሩ ዕቃዎች፥
3400 ኪሎ የሚመዝን ወርቅ፥
8 ኪሎ ከ 400 ግራም የሚመዝኑ ኻያ ከወርቅ የተሠሩ ወጭቶች፥
ከወርቅ ከተሠሩት ወጭቶች ጋር እኩል ዋጋ ያላቸው ከንጹሕ ነሐስ የተሠሩ ሁለት ወጭቶች።
28እኔም እንዲህ አልኳቸው፦ “እነሆ እናንተ ለቀድሞ አባቶቻችን አምላክ ለእግዚአብሔር የተለያችሁ ናችሁ፤ እንዲሁም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ሆነው የቀረቡት ከብርና ከወርቅ የተሠሩት ዕቃዎች ሁሉ ለቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር የበጎ ፈቃድ መባ ናቸው። 29ወደ ቤተ መቅደስ መግባት እስኪችሉ ድረስ በጥንቃቄ ጠብቁአቸው፤ እዚያም ለካህናቱ በተመደበው ክፍል ውስጥ እነዚህን ሁሉ ንዋያተ ቅድሳት መዝናችሁ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ መሪዎች እንዲሁም በኢየሩሳሌም ለሚገኙት የሕዝቡ መሪዎች አስረክቡአቸው።” 30ስለዚህም ካህናቱና ሌዋውያኑ ብሩንና ወርቁን፥ ጠቅላላውንም ንዋያተ ቅድሳት ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ለመውሰድ ኀላፊነትን ተረከቡ።
የሕዝቡ ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ
31ከአሀዋ ወንዝ ተነሥተን ወደ ኢየሩሳሌም ጒዞ የጀመርነውም የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ነበር፤ በምንጓዝበትም ጊዜ አምላካችን ከእኛ ጋር ስለ ነበር ከጠላት አደጋና ከደፈጣ ተዋጊዎች ሽመቃ ጠበቀን። 32ኢየሩሳሌም በደረስንም ጊዜ በዚያ የሦስት ቀኖች ዕረፍት አደረግን፤ 33ከዚህም በኋላ በአራተኛው ቀን ወደ ቤተ መቅደስ ሄድን፤ ብሩን፥ ወርቁንና ንዋያተ ቅድሳቱንም ሁሉ መዝነን ለኡሪያ ልጅ ለካህኑ ለመሬሞት አስረከብነው፤ የፊንሐስ ልጅ አልዓዛርና እንዲሁም ሌዋውያኑ ዮዛባድ ተብሎ የሚጠራው የኢያሱ ልጅና ኖዓዲያ ተብሎ የሚጠራው የቢኑይ ልጅ ከእርሱ ጋር አብረው ነበሩ። 34ሁሉም ነገር በዚያኑ ሰዓት ተቈጥሮና ተመዝኖ በትክክል ተመዘገበ።
35ከዚያም ቀጥሎ እነዚያ ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች ሁሉ ለእስራኤል አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበውን መባ ሁሉ አመጡ፤ በዚህ ዐይነት በመላው እስራኤል ሕዝብ ስም ዐሥራ ሁለት ኰርማዎችን፥ ዘጠና ስድስት የበግ አውራዎችንና ሰባ ሰባት የበግ ጠቦቶችን አቀረቡ፤ እንዲሁም ስለ ኃጢአታቸው ስርየት ዐሥራ ሁለት አውራ ፍየሎችን አቀረቡ፤ እነዚህ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነበሩ። 36ንጉሠ ነገሥቱ የሰጣቸውንም ሰነድ በኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ላሉት ገዢዎችና ባለሥልጣኖች ሰጡ፤ እነርሱም ሕዝቡንና የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ በማገዝ ድጋፋቸውን ሰጡ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ 8: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997