የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ዕዝራ 9

9
ዕዝራ ከአይሁድ ዘር ውጪ የተደረገ ጋብቻ መኖሩን መገንዘቡ
1ይህም ሁሉ ከተፈጸመ በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ መሪዎች አንዳንዶቹ ወደ እኔ ቀርበው ከዚህ የሚከተለውን ቃል ነገሩኝ፦ “ሕዝቡና ካህናቱ ሌዋውያኑም ጭምር በጐረቤት ባሉት በዐሞን፥ በሞአብና በግብጽ ከሚኖሩትና እንዲሁም ከከነዓናውያን፥ ከሒታውያን፥ ከፈሪዛውያን፥ ከኢያቡሳውያንና ከአሞራውያን ርኲሰት ራሳቸውን አልጠበቁም፤ እነዚያ አሕዛብ ሲፈጽሙት የነበረውን አጸያፊ ነገር ሁሉ አድርገዋል። 2ለራሳቸውና ለልጆቻቸው ሚስቶች የሚሆኑ ከእነዚያ ወገኖች አግብተዋል፤ አጋብተዋልም፤ ቅዱሱን ዘር ከሌሎች ከአካባቢው አሕዛብ ጋር ቀላቅለዋል፤ በዚህ እምነተ ቢስ በሆነ ተግባር መሪዎቹና ባለ ሥልጣኖቹ ግንባር ቀደም ሆነዋል።” 3እኔም ይህን በሰማሁ ጊዜ በሐዘን መጐናጸፊያዬንና ካባዬን ቀደድሁ፤ የራስ ጠጒሬንና ጢሜን በመንጨት በብርቱ ሐዘን ላይ ሆኜ ተቀመጥሁ፤ 4የሠርክ መሥዋዕት እስከሚቀርብበትም ጊዜ ድረስ በድንጋጤና በሐዘን ቈየሁ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች ስለ ሠሩት ኃጢአት በተናገረው ቃል ከመፍራት የተነሣ ድንጋጤ አድሮባቸው የነበሩትም ሁሉ በዙሪያዬ ተሰበሰቡ።
5የምሽትም መሥዋዕት የሚቀርብበት ሰዓት በደረሰ ጊዜ በሐዘን ከተቀመጥኩበት ስፍራ ተነሣሁ፤ የቀደድኩትን ልብስ እንደ ለበስኩ፥ በጒልበቴም በመንበርከክ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጆቼን ዘርግቼ እንዲህ ስል ጸለይኩ፦ 6“አምላኬ ሆይ፥ ኃጢአታችን ከራሳችን በላይ ስለ ሆነና በደላችንም ወደ ሰማይ ስለ ደረሰ ፊቴን ወደ አምላኬ ወደ አንተ ለማቅናት ዐፍራለሁ እፈራለሁም። 7ከቀድሞ አባቶቻችን ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ እኛ ታላቅ በደል ሠርተናል፤ ከኃጢአታችንም ብዛት የተነሣ እኛ፥ ነገሥታቶችንና ካህናታችን በባዕዳን ነገሥታት እጅ ወድቀናል፤ ስለዚህም ለሰይፍ ተዳረግን፤ ሀብታችንንም ተዘረፍን፤ በመታሰር ተማርከን ተወሰድን፤ እነሆ፥ አሁንም እንዳለንበት ሁኔታ እስከ መጨረሻ ተዋርደናል። 8አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ ዐይናችንን አበራህ፤ እነሆ፥ አሁን ደግሞ ለጥቂት ጊዜ በፊትህ ሞገስን አግኝተን ከእኛ ጥቂቶቹ ከባርነት ቀንበር ነጻ ወጥተው በዚህች ቅድስት ምድር በሰላም ይኖሩ ዘንድ ፈቅደሃል፤ ምንም እንኳ በባርነት አገዛዝ ሥር ብንወድቅም እነሆ አዲስ ሕይወት ሰጥተኸናል። 9እኛ ባርያዎች ነበርን፤ አንተ ግን ባርያዎች ሆነን እንድንቀር አልተውከንም፤ አንተ የፋርስ ነገሥታት እንዲራሩልንና በሕይወት ነጻ ወጥተን ቀደም ሲል ፈርሶ የነበረውን ቤተ መቅደስህን እንደገና መልሰን እንድንሠራ፥ እዚህም በይሁዳና በኢየሩሳሌም በሰላም እንድንኖር ፈቀድክልን።
10“ነገር ግን አምላካችን ሆይ! እስከ አሁን ስለ ሆነው ነገር ሁሉ ምን ማለት እንችላለን? እነሆ፥ አሁንም እንደገና ትእዛዞችህ አላከበርንም፤ 11እነዚህም ትእዛዞች በአገልጋዮችህ በነቢያት አማካይነት የተሰጡ ነበሩ፤ ነቢያት አስቀድመው ‘የምትወርሱአት ምድር ከርኲሰት ሁሉ የነጻች አይደለችም፤ የሚኖሩባት ሕዝቦች ዳር እስከ ዳር በአጸያፊ ተግባር ሁሉ እንድትሞላ አድርገዋታል። 12ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁን በጋብቻ ለእነርሱ ወንዶች ልጆች አትስጡ፤ እናንተም ለወንዶች ልጆቻችሁ የእነርሱን ሴቶች ልጆች በጋብቻ አትውሰዱ፤ በማንኛውም ጊዜ ከምድሩ መልካም ነገር በልታችሁ ለልጆቻችሁ ዘላቂ ርስት አድርጋችሁ ለማስተላለፍ እንድትችሉ በማንኛውም ጊዜ ከእነርሱ ጋር የወዳጅነት ስምምነት አታድርጉ’ ሲሉ ነግረውን ነበር። #ዘፀ. 34፥11-16፤ ዘዳ. 7፥1-5። 13የደረሰብን ችግር የክፉ ሥራችንና የበደላችን ውጤት ነው፤ ሆኖም አምላካችን የቀጣኸን ልንቀጣ ከሚገባን ያነሰ ነው፤ ከዚህም በላይ ከሞት አምልጠን በሕይወት አትርፈኸናል። 14ታዲያ እንዴት እንደገና የአንተን ትእዛዞች ጥሰን ከእነዚህ ዐመፀኞች ሕዝቦች ጋር ጋብቻ እንፈጽማለን? በዚህስ ምክንያት ምንም ቅሬታ ሳታስቀርልን እኛን በቊጣህ አታጠፋንምን? 15የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ እውነተኛ ፈራጅ ነህ፤ ነገር ግን ከጥፋት አምልጠን በሕይወት እንድንኖር ፈቀድክልን፤ እነሆ እኛ፥ በደላችንን ተሸክመን በፊትህ ለመቅረብ የተገባን አይደለንም።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ