መጽሐፈ ዕዝራ 10
10
ከአሕዛብ ጋር መጋባትን ለመከልከል የወጣ ሕግ
1ዕዝራ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ለጸሎት ተንበርክኮ እያለቀሰ የተፈጸመውን ኃጢአት ሁሉ ለእግዚአብሔር በሚናዘዝበት ጊዜ ወንዶችም፥ ሴቶችም፥ ሕፃናትም ጭምር ያሉበት ቊጥሩ የበዛ የእስራኤል ማኅበር መጥቶ በዙሪያው በመሰብሰብ በመረረ ሁኔታ ያለቅሱ ነበር። 2ከዚህም በኋላ ከዔላም ጐሣ የየሒኤል ልጅ ሸካንያ ዕዝራን እንዲህ አለው፦ “በእርግጥ እኛ በአካባቢአችን ካሉት አሕዛብ ባዕዳን ሴቶችን በማግባት በእግዚአብሔር ላይ የነበረንን እምነት አጓድለናል፤ ይህም ሁሉ ሆኖ አሁንም ለእስራኤል ተስፋ አለ። 3አሁን እንግዲህ እነዚህን ባዕዳን ሴቶች ከነልጆቻቸው ማሰናበት እንደሚገባን ለአምላካችን ቃል እንግባ፤ አንተ ጌታዬና የአምላካችንን ትእዛዝ የሚያከብሩ ሌሎችም የምትሰጡንን ምክር ሁሉ እንፈጽማለን፤ የእግዚአብሔር ሕግ የሚያዘውን ሁሉ እናደርጋለን፤ 4ይህንንም ሁሉ ለማስፈጸም ኀላፊነቱ የአንተ ስለ ሆነ ተነሥ፤ እኛም እንደግፍሃለን፤ አይዞህ በርታ።”
5ስለዚህም ዕዝራ የካህናት፥ የሌዋውያንና የቀሩት ሕዝብ መሪዎች ሸካንያ ባቀረበው ሐሳብ መስማማታቸውን በመሐላ እንዲያረጋግጡለት በማድረግ ሥራውን ጀመረ። 6ቀጥሎም ዕዝራ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ከነበረው ስፍራ በመነሣት የኤልያሺብ ልጅ ዮሐናን ወደሚኖርባቸው ክፍሎች ገባ፤ ምርኮኞቹ እምነት በማጓደል ስለ ፈጸሙትም በደል ሁሉ እያዘነ ሌሊቱን በዚያው አነጋ፤ እህልም ሆነ ውሃ አልቀመሰም።
7ከምርኮ የተመለሱትም ሁሉ በኢየሩሳሌም ይሰበሰቡ ዘንድ በመላው ኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምድር ሁሉ ታወጀ። 8ይህም ሁሉ በሕዝቡ መሪዎች ምክርና ትእዛዝ የተወሰነ ነበር፤ በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ ወደዚህ ስብሰባ መምጣት ያልቻለ ማንም ሰው ቢኖር ንብረቱ ሁሉ እንደሚወረስና ከምርኮ ከተመቱት ሰዎች ጉባኤ እንደሚወገድ ተነገረው። 9ይህም ጥሪ እንደ ተላለፈ በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ በይሁዳና በብንያም ግዛት የሚኖሩት ሁሉ ዘጠነኛው ወር በገባ በሃያኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው በቤተ መቅደሱ አደባባይ ተሰበሰቡ፤ ሰዎቹ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት በተሰበሰቡበት ጉዳይና በዝናቡ ምክንያት እየተንቀጠቀጡ ቆመው ነበር።
10ካህኑ ዕዝራም ቆሞ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “እነሆ እምነታችሁን አጓድላችሁ ተገኝታችኋል፤ ባዕዳን ሴቶችንም በማግባታችሁ ምክንያት በእስራኤል ላይ የበደልን ዕዳ አምጥታችኋል። 11ከአሁን በኋላ እንግዲህ በቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአታችሁን ሁሉ ተናዘዙ፤ እርሱም ደስ የሚሰኝበትን ነገር ሁሉ አድርጉ፤ በምድራችን ከሚኖሩት ባዕዳን ሁሉ ራቁ፤ ያገባችኋቸውንም ባዕዳን ሴቶች ወዲያ አስወግዱ።”
12የተሰበሰቡትም ሰዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “አንተ የምትለውን ሁሉ እናደርጋለን!” አሉ። 13ንግግራቸውንም በመቀጠል እንዲህ አሉት፦ “እነሆ እዚህ የተሰበሰበው ሕዝብ ብዙ ነው፤ ከዚህም ጋር በከባድ ሁኔታ እየዘነበ ነው፤ መጠለያ በሌለበት በዚህ ስፍራ መቆም አልቻልንም፤ በዚህ ኃጢአት የተበከልነውም ብዙዎች በመሆናችን ይህን ሁሉ ነገር በአንድ ወይም በሁለት ቀኖች ውስጥ መፈጸም አይቻልም። 14ስለዚህ አለቆቻችን በዚሁ በኢየሩሳሌም ጉዳዩን ያጥኑት፤ ከዚህም በኋላ ባዕድ ሴት ያገባ ሁሉ እያንዳንዱ በሚሰጠው የቀጠሮ ቀን ከሚኖርባት ከተማ መሪዎችና ዳኞች ጋር እየመጣ ውሳኔውን ይቀበል፤ እግዚአብሔር የተቈጣበትም ሁኔታ ሁሉ በዚሁ ዐይነት ይበርዳል።” 15ይህም በተነገረ ጊዜ መሹላምና ሻበታይ ተብሎ የሚጠራው አንድ ሌዋዊ ድጋፍ ከሰጡአቸው ከዐሣሔል ልጅ ዮናታንና የቲቅዋ ልጅ ከሆነው ከያሕዘያ በቀር ሌላ ተቃዋሚ አልነበረም።
16ከምርኮ የተመለሱት ሁሉ ይህንኑ ዕቅድ ለመቀበል ተስማሙ፤ ስለዚህም ካህኑ ዕዝራ ከጐሣ መሪዎች መካከል መርጦ አስፈጻሚዎችን በመሾም ስም ዝርዝራቸውን መዝግቦ አኖረ፤ እነርሱም ዐሥረኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን ጉዳዩን መመርመር ጀመሩ። 17በሚቀጥለው ዓመት በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ከባዕዳን ሴቶች ጋር የተጋቡትን ሰዎች ጉዳይ በሙሉ መርምረው ጨረሱ።
ከባዕዳን ሴቶች ጋር የተጋቡ ሰዎች ስም ዝርዝር
18ከባዕዳን ሴቶች ጋር የተጋቡ ሰዎች ስም ዝርዝር የሚከተለው ነው፦
በየጐሣቸው የተመዘገቡ ካህናት፥
የኢዮጼዴቅ ልጆች ከሆኑት ከኢያሱና ከወንድሞቹ ጐሣ የተገኙ፤ ማዕሤያ፥ ኤሊዔዘር፥ ያሪብና ገዳልያ፤ 19እነርሱም ሚስቶቻቸውን ፈተው ለማሰናበት ቃል ከገቡ በኋላ ለኃጢአታቸው ማስተስረያ የሚሆን አንድ የበግ አውራ ለሚቃጠል መሥዋዕት አቀረቡ።
20ከኢሜር ጐሣ፦ ሐናኒና ዘባድያ።
21ከሓሪም ጐሣ፦ ማዕሤያህ፥ ኤልያስ፥ ሸማዕያ፥ የሒኤልና ዑዚያ፤
22ከፓሽሑር ጐሣ፦ ኤልዮዔናይ፥ ማዕሤያ፥ እስማኤል፥ ናትናኤል፥ ዮዛባድና ኤልዓሳ፤
23ከሌዋውያን ወገን፦
ዮዛባድ፥ ሺምዒ፥ ቀሊጣ ተብሎ የሚጠራው ቄላያ፥ ፐታሕያ፥ ይሁዳና ኤሊዔዘር፤
24ከመዘምራን ወገን፦
ኤልያሺብ።
ከቤተ መቅደስ ዘብ ጠባቂዎች ወገን፦
ሻሉም፥ ጤሌምና ኡሪ፤
25ከሌሎች እስራኤላውያን፦
ከፓርዖሽ ጐሣ፦ ራምያ፥ ይዚያ፥ ማልኪያ፥ ሚያሚን፥ አልዓዛር ማልኪያና በናያ፤
26ከዔላም ጐሣ፦ ማታንያ፥ ዘካርያስ የሒኤል፥ ዐብዲ፥ የሬሞትና ኤልያ፤
27ከዛቱ ጐሣ፦ ኤልዮዔናይ፥ ኤልያሺብ፥ ማታንያ፥ የሬሞት፥ ዘባድና ዓዚዛ፤
28ከቤባይ ጐሣ፦ የሆሐናን፥ ሐናንያ፥ ዛባይና ዐትላይ፤
29ከባኒ ጐሣ፦ መሹላም፥ ማሉክ፥ ዐዳያ፥ ያሹብ፥ ሸአልና የራሞት፤
30ከፓሐትሞአብ ጐሣ፦ ዓድና፥ ከላል፥ በናያ፥ ማዕሴያ፥ ማታንያ፥ በጻልኤል፥ ቢኑይና ምናሴ፤
31-32ከሓሪም ጐሣ፦ ኤሊዔዘር፥ ይሺያ፥ ማልኪያ፥ ሸማዕያ፥ ስምዖን፥ ብንያም፥ ማሉክና ሸማርያ፤
33ከሐሹም ጐሣ፦ ማታናይ፥ ማታታ፥ ዛባድ፥ ኤሊፌሌጥ፥ የሬማይ፥ ምናሴና ሺምዒ፤
34-37ከባኒ ጐሣ፦ መዕዳይ፥ ዓምራም፥ ኡኤል፥ በናያ፥ ቤድያ፥ ከሉሂ፥ ዋንያ፥ መሬሞት፥ ኤልያሺብ፥ ማታንያ፥ ማትናይና ያዕሱ፤
38-42ከቢኑይ ጐሣ፦ ሺምዒ፥ ሼሌምያ፥ ናታን፥ ዓዳያ፥ ማክናደባይ፥ ሻሻይ፥ ሻራይ፥ ዐዛርኤል፥ ሼሌምያ፥ ሸማርያ፥ ሻሉም፥ አማርያና ዮሴፍ፤
43ከነቦ ጐሣ፦ የዒኤል፥ ማቲትያ፥ ዛባድ፥ ዘቢና፥ ያዳይ፥ ኢዩኤልና በናያ፤
44እነዚህ ሁሉ ሰዎች ባዕዳን ሴቶችን አግብተው የነበሩ ናቸው፤ እነርሱም ያገቡአቸውን ባዕዳን ሴቶች ሁሉ ፈተው ከነልጆቻቸው አባረሩ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ 10: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997