መጽሐፈ ዕዝራ 6
6
ቂሮስ የሰጠው ትእዛዝ ተፈልጎ መገኘቱ
1በባቢሎን ቤተ መንግሥት የሚገኙ መዛግብት ሁሉ ይመረመሩ ዘንድ ንጉሠ ነገሥት ዳርዮስ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ 2ነገር ግን በባቢሎን ከተማ ሳይሆን በሜዶን ክፍለ ሀገር በተለይ “አሕምታ” ተብላ በምትጠራው ከተማ ውስጥ አንድ የብራና ጥቅል ተገኘ፤ በውስጡም የተጻፈበት ቃል እንዲህ የሚል ነበር፦
3“ቂሮስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በመጀመሪያው ዓመት በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ የሚቃጠለውና ሌላውም ልዩ ልዩ መሥዋዕት ይቀርብበት ዘንድ እንደገና እንዲሠራ በመፍቀድ ትእዛዝ ሰጥቶአል፤ የቤተ መቅደሱም ርዝመት ኻያ ሰባት ሜትር፥ ስፋቱም ኻያ ሰባት ሜትር መሆን አለበት። 4ቅጽሮቹም ከድንጋይ በተሠሩት በሦስቱም ዙር ግንቦች አናት ላይ አንዳንድ ዙር ከእንጨት የተሠራ ድምድማት ይኑራቸው፤ ለዚህም ሁሉ ሥራ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከቤተ መንግሥቱ ግምጃ ቤት ወጪ ሆኖ ይሰጥ። 5እንዲሁም ከዚህ በፊት ንጉሥ ናቡከደነፆር በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ ማርኮ ያወጣቸው ከወርቅና ከብር የተሠሩትም ንዋያተ ቅድሳት ወደዚያው ተመልሰው በኢየሩሳሌም በሚሠራው ቤተ መቅደስ በተገቢ ቦታቸው ይቀመጡ።”
የቤተ መቅደሱ ሥራ እንዲቀጥል ዳርዮስ ትእዛዝ መስጠቱ
6ከዚህ በኋላ ዳርዮስ የሚከተለውን መልእክት አስተላለፈ፦ “የኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ገዢ ለሆንከው ለታተናይ፥ ለሸታርቦዝናይና በኤፍራጥስ ምዕራብ ለሚገኙ ተባባሪዎቻችሁ ሁሉ፦ ከቤተ መቅደሱ ራቁ፤ 7ሥራውን ከማደናቀፍ ተቈጠቡ፤ የይሁዳ ክፍለ ሀገር ገዢና የአይሁድ መሪዎች ቀድሞ በነበረበት ስፍራ ላይ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መልሰው ይሥሩ። 8በዚሁ አጋጣሚ ይልቁንም የቤተ መቅደሱን ሥራ እንድታግዙአቸው አዝዣችኋለሁ። ስለዚህም አስፈላጊው የማሠሪያ ገንዘብ ሁሉ ከኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ከተሰበሰበው የመንግሥት ግብር ሳይዘገይ ወጪ እየሆነ ይሰጣቸው፤ ሥራውም መሰናከል አይገባውም። 9ከዚህም ሁሉ ጋር በኢየሩሳሌም የሚገኙት ካህናት በሚነግሩአችሁ መሠረት በየዕለቱ በሰማይ ለሚኖረው አምላክ ለሚያቀርቡት መሥዋዕት የሚፈልጓቸውን ኰርማዎች፥ በጎችን ወይም ጠቦቶችን፥ እንዲሁም ለመባ የሚሆነውን ስንዴ፥ ጨው፥ የወይን ጠጅና የወይራ ዘይት ሁሉ ስጡአቸው። 10ይህም ሁሉ የሚሆንበት ምክንያት የሰማይ አምላክ በደስታ የሚቀበለውን መሥዋዕት ሁሉ በማቅረብ ለእኔና ለልጆቼ ሕይወት እንዲጸልዩልን ነው፤ 11ከዚህም ሌላ ማስታወቅ የምፈልገው ነገር ይህን መመሪያ የማይቀበልና የማይታዘዝ ማንም ሰው ቢኖር ከቤቱ የእንጨት ምሰሶዎች አንዱ ተነቅሎ በአንዱ ጫፍ በኩል እንዲሾል ከተደረገ በኋላ በሰውነቱ ላይ ይሰካበት፤ ቤቱም ፈራርሶ የጉድፍ መጣያ ይሁን። 12ይህን ትእዛዝ ባለመቀበል በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ለማፍረስ የሚሞክረውን ማንኛውንም ንጉሥ ወይም ሕዝብ የስሙ መጠሪያ ይሆን ዘንድ የመረጠ አምላክ ያስወግደው፤ ይህን ትእዛዝ ያስተላለፍኩ እኔ ዳርዮስ ስለ ሆንኩ በሙሉ መፈጸም አለበት።”
የቤተ መቅደሱ የምረቃ በዓል
13ከዚህ በኋላ አገረ ገዢው ታተናይ፥ ሸታርቦዝናይና የእነርሱም ተባባሪዎች የሆኑ ባለሥልጣኖች ንጉሠ ነገሥቱ እንዳዘዛቸው ሁሉንም ነገር ፈጸሙ። 14የአይሁድ መሪዎች፥ ነቢያቱ ሐጌና ዘካርያስ እያበረታቱአቸው የቤተ መቅደሱን ሥራ አፋጠኑት፤ በእስራኤል አምላክ ፈቃድ የፋርስ ነገሥታት ቂሮስ፥ ዳርዮስና አርጤክስስ ባዘዙትም መሠረት የቤተ መቅደሱን ሥራ ፈጸሙ፤ #ሐጌ 1፥1፤ ዘካ. 1፥1። 15የቤተ መቅደሱን ሥራ የፈጸሙትም ዳርዮስ ንጉሠ ነገሥት በሆነ በስድስተኛው ዓመት አዳር ተብሎ የሚጠራው ወር በገባ በሦስተኛው ቀን ነበር። 16ከዚህም ቀጥሎ የእስራኤል ሕዝብ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ እንዲሁም ከምርኮ የተመለሱት ሌሎችም ሰዎች ሁሉ፥ የቤተ መቅደሱን ምረቃ በዓል በደስታ አከበሩ። 17እነርሱም ሁሉ ለበዓሉ የሚሆኑትን አንድ መቶ ወይፈኖችን፥ ሁለት መቶ በጎችንና አራት መቶ ጠቦቶችን ለመሥዋዕት አቀረቡ፤ ለኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚሆኑም ዐሥራ ሁለት ፍየሎችን በእያንዳንዱ ነገድ ስም አቀረቡ። 18በሙሴ መጽሐፍ በተጻፈውም መመሪያ መሠረት በኢየሩሳሌም ለተሠራው ቤተ መቅደስ አገልግሎት፥ ካህናቱን በየክፍላቸው፥ ሌዋውያኑን በየቡድናቸው አደራጁ።
የፋሲካ በዓል
19ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል አከበሩ። #ዘፀ. 12፥1-20። 20ካህናቱና ሌዋውያኑም ሁሉ በሥርዓቱ መሠረት ራሳቸውን አነጹ፤ ሌዋውያኑም በፋሲካው በዓል አከባበር ላይ ከምርኮ ለተመለሱት ሕዝብና ለካህናቱ፥ እንዲሁም ለራሳቸው የቀረቡትን እንስሶች ዐረዱ። 21መሥዋዕቱንም ሁሉ ከምርኮ የተመለሱት እስራኤላውያን እንዲሁም በዚያች ምድር የሚኖሩትን የአሕዛብን ሥርዓት ትተው የነበረውን ልማድ ትተው የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሁሉ እንዲመገቡት ተደረገ። 22እግዚአብሔር ራሱ በአሦር ንጉሠ ነገሥት ዘንድ መወደድን አግኝተው የእስራኤል አምላክ የሚመሰገንበትን ቤተ መቅደስ እንደገና መሥራት ይችሉ ዘንድ በሥራቸው ሁሉ እንዲረዳቸው ስላደረገላቸው የቂጣን በዓል ሰባት ቀን ሙሉ በታላቅ ደስታ አከበሩ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ 6: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997