መጽሐፈ ዕዝራ 5
5
የቤተ መቅደሱ ሥራ እንደገና መቀጠሉ
1በዚያን ጊዜ ሁለቱ ነቢያት፥ ሐጌና የዒዶ ልጅ ዘካርያስ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምድር ለሚኖሩ አይሁድ፥ ስለ ቤተ መቅደሱ ሥራ ጉዳይ በእስራኤል አምላክ ስም ትንቢት ተናገሩላቸው። #ሐጌ 1፥1፤ ዘካ. 1፥1። 2የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የኢዮጼዴቅ ልጅ ኢያሱም የነዚህን ነቢያት የትንቢት ቃል በሰሙ ጊዜ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ መሥራታቸውን እንደገና ቀጠሉ፤ ሁለቱ ነቢያትም ይረዱአቸው ነበር። #ሐጌ 1፥12፤ ዘካ. 4፥6-9።
3በዚያን ጊዜ የኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ገዢ የነበረው ታተናይና ሽታርቦዝናይ እንዲሁም ተባባሪዎቻቸው የሆኑ ባለሥልጣኖች ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፦ “ይህን ቤተ መቅደስ ለመሥራትና ቅጽሩንም ለማደስ ማን ፈቀደላችሁ?” ሲሉ ጠየቁአቸው። 4ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተባበሩአቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ለማወቅም ጠየቁ። 5ነገር ግን የአይሁድ መሪዎችን እግዚአብሔር ይጠብቃቸው ስለ ነበር ለፋርስ ባለ ሥልጣኖች ለዳርዮስ መልእክት ጽፈው መልስ እስከሚያገኙ ድረስ ሥራውን ከመቀጠል አልከለከሉአቸውም። 6የኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ገዢ የነበረው ታተናይና ሽታርቦዝናይ እንዲሁም ተባባሪዎቻቸው የሆኑ ለንጉሥ ዳርዮስ የጻፉት ደብዳቤ የሚከተለው ነው፦ 7“ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ዳርዮስ! ግዛትዎ ሰላም ይሁን፤ 8ወደ ይሁዳ ምድር ሄደን የታላቁ አምላክ ቤተ መቅደስ በድንጋይና በጠርብ እንጨት ሲሠራ ማየታችን ለግርማዊነትዎ የታወቀ ይሁን፤ ሥራውም በሽማግሌዎቹ መሪነት በጥንቃቄና በፍጥነት እየተሠራ ነው።
9“እኛም የሕዝቡን መሪዎች ‘ይህን ቤተ መቅደስ እንደገና መልሳችሁ ለመሥራትና ቅጽሮቹንም ለማደስ ማን ፈቀደላችሁ?’ ብለን ጠየቅናቸው፤ 10የዚህ ሥራ መሪዎችም እነማን እንደ ሆኑ እንገልጥልህ ዘንድ የስም ዝርዝራቸውን ጠይቀናል።
11“እነርሱም እንዲህ ሲሉ አስረድተውናል፤ ‘እኛ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ የታላቁ እግዚአብሔር አገልጋዮች ነን፤ ስለዚህም ለእርሱ ከብዙ ዘመን በፊት በአንድ ታላቅ የእስራኤል ንጉሥ ተሠርቶለት የነበረውን ቤተ መቅደስና ቅጽር እንደገና መልሰን በመሥራት ላይ እንገኛለን፤ 12ነገር ግን የቀድሞ አባቶቻችን ይህን የሰማይ አምላክ በማስቈጣታቸው ምክንያት በከለዳውያን ሥርወ መንግሥት የባቢሎን ንጉሠ ነገሥት በሆነው በናቡከደነፆር ጦር እንዲሸነፉ አደረገ፤ ቤተ መቅደሱ ፈራረሰ፤ ሕዝቡም ተማርኮ ወደ ባቢሎን ተወሰደ። #2ነገ. 25፥8-12፤ 2ዜ.መ. 36፥17-20፤ ኤር. 52፥12-15። 13ከዚህም በኋላ ቂሮስ የባቢሎን ንጉሠ ነገሥት በሆነ በመጀመሪያው ዓመት ይህን ቤተ መቅደስ መልሰን መሥራት እንድንችል በዐዋጅ የፈቀደልን ንጉሠ ነገሥቱ ቂሮስ ራሱ ነው። #ዕዝ. 1፥2-11። 14ናቡከደነፆር በዚሁ በኢየሩሳሌም ተሠርቶ ከነበረው ከቀድሞው ቤተ መቅደስ ማርኮ የወሰዳቸውንና በባቢሎን ማምለኪያ ስፍራው ውስጥ ያኖራቸውን ከወርቅና ከብር የተሠሩ ንዋያተ ቅድሳትም ሁሉ ቂሮስ መልሶ አስረክቦናል፤ ንዋያተ ቅድሳቱንም ያስረከበን የይሁዳ ገዢ አድርጎ በሾመው ሼሽባጻር ተብሎ በሚጠራው ሰው አማካይነት ነው። 15ይኸው አገረ ገዢው ሼሽባጻር እነዚህን ንዋያተ ቅድሳት መልሶ በማምጣት በኢየሩሳሌም ከነበረው ቤተ መቅደስ ውስጥ ያኖር ዘንድ፥ እንዲሁም ቤተ መቅደሱ ቀድሞ በነበረበት ስፍራ ላይ ተመልሶ እንዲሠራ ያደርግ ዘንድ፥ ንጉሠ ነገሥቱ ቂሮስ አዞታል። 16ስለዚህም ሼሽባጻር መጥቶ መሠረቱን ጣለ፤ ከዚያም በኋላ የሕንጻው ሥራ እንዲቀጥል ተደርጎ፥ ይኸው እስከ አሁን በመሠራት ላይ ነው፤ ነገር ግን የቤተ መቅደሱ ሕንጻ ገና አልተፈጸመም።’
17“ንጉሥ ሆይ! እንግዲህ በእርግጥ ይህ ቤተ መቅደስ በኢየሩሳሌም ይሠራ ዘንድ ንጉሥ ቂሮስ የሰጠው ትእዛዝ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ በባቢሎን ቤተ መንግሥት የጽሑፍ ማስረጃዎችን አስመርምረህ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ዐይነት ውሳኔ ቢሰጥ እንደምትፈቅድ ታስታውቀን ዘንድ እንለምናለን።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ 5: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997