መጽሐፈ ዕዝራ 4

4
ቤተ መቅደሱ እንደገና እንዳይሠራ የተደረገ ተቃውሞ
1የይሁዳና የብንያም ሕዝብ ጠላቶች የሆኑ ነዋሪዎች ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ሰሙ። 2ወደ ዘሩባቤልና ወደ ጐሣ መሪዎችም ቀርበው “ቤተ መቅደሱን ከእናንተ ጋር አብረን እንሥራ፤ ይህንኑ እናንተ የምታመልኩትን እግዚአብሔር እኛም እናመልከዋለን፤ የአሦር ንጉሠ ነገሥት አስራዶን ወደዚህ አገር ከላከንም ጊዜ ጀምሮ መሥዋዕት ስናቀርብለት ቈይተናል” አሉአቸው። #2ነገ. 17፥24-41።
3ነገር ግን ዘሩባቤል፥ ኢያሱና የጐሣ መሪዎች ሁሉ እነዚህን ሰዎች፦ “ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ስለምንሠራው ቤተ መቅደስ የእናንተ ርዳታ አያስፈልገንም፤ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ቂሮስ ባዘዘን መሠረት እኛው ራሳችን እንሠራዋለን” ሲሉ መለሱላቸው።
4ከዚህም በኋላ የምድሪቱ ነዋሪዎች የሆኑት ሕዝቦች አይሁድን በማስፈራራትና ተስፋ ለማስቈረጥ በመሞከር ቤተ መቅደሱን እንዳይሠሩ ሊከለክሉአቸው ተነሣሡ። 5ለፋርስ መንግሥት ባለሥልጣኖች ጉቦ በመስጠትም በእነርሱ ላይ ተጽዕኖ ሊያደርጉባቸው ሞከሩ፤ ከቂሮስ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ዳርዮስ እስከ ተነሣበት ዘመን ድረስ ይህን ከማድረግ አልተቈጠቡም ነበር።
ኢየሩሳሌም እንደገና እንዳትሠራ የተደረገ ሌላ ተቃውሞ
6ይልቁንም አርጤክስስ ንጉሠ ነገሥት በሆነበት ዘመን መጀመሪያ ላይ፥ ጠላቶቻቸው በይሁዳና በኢየሩሳሌም ይኖሩ በነበሩት እስራኤላውያን ላይ በጽሑፍ የተቀናበረ ክስ መሠረቱባቸው። #አስ. 1፥1።
7አርጤክስስ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በተነሣበትም ዘመን፥ እንደገና ቢሽላም፥ ሚትረዳት፥ ጣብኤልና ሌሎቹ የእነርሱ ግብረ አበሮች የክስ ደብዳቤ ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ጻፉባቸው፤ ይህም ደብዳቤ የተጻፈው በሶርያ ፊደልና ቋንቋ ሲሆን ተተርጒሞ በንባብ እንዲሰማ የተላከ ነበር።
8እንዲሁም አገረ ገዢው ረሑምና የአውራጃው ጸሐፊ ሺምሻይ፥ ስለ ኢየሩሳሌም ጉዳይ ከዚህ የሚከተለውን ደብዳቤ ወደ ንጉሥ አርጤክስስ ጻፉ፤
9ከአገረገዢ ረሑምና ከአውራጃው ጸሐፊ ሺምሻይ፥ እንዲሁም ተባባሪዎቻቸው ከሆኑት ዳኞችና ቀድሞ በዔላም ምድር በኤሬክ፥ በባቢሎንና በሱሳ ይኖሩ ከነበሩት ሌሎችም ባለ ሥልጣኖች ሁሉ፥ 10ታላቁና ኀያሉ ንጉሠ ነገሥት አሰናፈር ከየተወለዱበት አገር በማዛወር በሰማርያ ከተማና ከኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል በየአውራጃው እንዲሰፍሩ ካደረጋቸው ከሌሎችም ሕዝቦች ጋር በመተባበር የተጻፈ ሲሆን።
11የደብዳቤውም ፍሬ ነገር ይህ ነው፤ በኤፍራጥስ ምዕራባዊ ክፍል ከሚኖሩ አገልጋዮቹ ለንጉሠ ነገሥት አርጤክስስ የተላከ።
12“ከግርማዊነትዎ ዘንድ የመጡት አይሁድ እዚህ ኢየሩሳሌም የደረሱ መሆናቸው በግርማዊነትዎ ዘንድ የታወቀ ይሁን። ያቺን ዐመፀኛና ክፉ ከተማ እንደገና በመሥራት ላይ ናቸው፤ ቅጽሮቹን በመጠገንና የቤተ መቅደስዋንም መሠረት በመጣል ላይ ናቸው። 13ስለዚህም ንጉሥ ሆይ! ይህች ከተማ እንደገና ከተሠራችና የቅጽሮችዋም ሥራ ከተጠናቀቀ፥ ሕዝቡ ግብር መክፈላቸውን ያቆማሉ፤ ለግርማዊነትዎ የሚቀርበውም የንጉሣዊ ቤተ መንግሥት ገቢ ሊቀነስ የሚችል መሆኑን ይታወቅ፤ 14እኛም የቤተ መንግሥቱ ጥቅም ተካፋዮች በመሆናችን አለመከበርዎን እያየን ዝም ማለትን ስላልወደድን ይህን ሐሳብ እናቀርባለን፤ 15ስለዚህ የቀድሞ አባቶችዎ ታሪክ ያለባቸው መዛግብት እንዲመረመሩ ትእዛዝ ይሰጡ ዘንድ እናሳስባለን፤ ይህ በሚደረግበት ጊዜ ይህች ከተማ ዘወትር ዐመፀኛ እንደ ነበረችና ከጥንት ጀምሮ ለነገሥታትና በየክፍላተ ሀገሩ ለሚገኙ አገረ ገዢዎች ምን ያኽል አስቸጋሪ እንደ ነበረች ማስረጃ ያገኛሉ፤ ከጥንት ጀምሮ ሕዝቦችዋ ዐመፀኞች ነበሩ፤ ከዚህ በፊት ከተማይቱ እንድትደመሰስ የተደረገበትም ምክንያት ይኸው ነበር። 16ከዚህም የተነሣ፥ ይህች ከተማ እንደገና ከተሠራችና የቅጽሮችዋም ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ግርማዊነትዎ ከኤፍራጥስ ማዶ በሚገኙት ክፍላተ ሀገሮች ላይ ምንም ይዞታ እንደማይኖርዎ እንገልጻለን።”
17ንጉሠ ነገሥቱም ለዚህ ደብዳቤ ከዚህ የሚከተለውን መልስ ላከ፦ “ለአገረ ገዢው ረሑም፥ ለአውራጃ ጸሐፊው ሺምሻይ፥ እንዲሁም በሰማርያና ከኤፍራጥስ በስተ ምዕራብ ለሚኖሩ ተባባሪዎችህ ሁሉ፥ ሰላም ለእናንተ ይሁን።
18“የላካችሁልኝ ደብዳቤ ተተርጒሞ በንባብ ሰምቼዋለሁ፤ 19በእርሱም መነሻነት ጥብቅ ምርምርና ጥናት እንዲደረግ ትእዛዝ ሰጥቻለሁ፤ ከጥናቱም የተገኘው ውጤት ኢየሩሳሌም ከጥንት ጀምሮ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ስታምፅ የኖረች ዐመፀኞችና አስቸጋሪዎች ሰዎች የሞሉባት ከተማ እንደ ነበረች ያስረዳል፤ 20ይህም ሁሉ ሆኖ፥ ኢየሩሳሌም ከኤፍራጥስ በስተ ምዕራብ ያሉትን አገሮች ሁሉ በማስገበር ቀረጥና ግብር የሚያስከፍሉ ኀያላን ነገሥታት ነግሠውባት ነበር። 21ስለዚህ እኔ ሌላ ትእዛዝ እስካስተላልፍ ድረስ እነዚያ ሰዎች ከተማይቱን እንደገና መሥራታቸውን ያቆሙ ዘንድ እዘዙ። 22በመንግሥታችን ላይ ምንም ችግር እንዳይደርስ ኀላፊነታችሁን ቸል እንዳትሉ ተጠንቀቁ።”
23ንጉሠ ነገሥቱ አርጤክስስ የላከው የመልስ ደብዳቤም መጥቶ ለረሑም፥ ለሺምሻይና ለተባባሪዎቻቸው ሁሉ እንደ ተነበበላቸው፥ ወዲያውኑ ወደ ኢየሩሳሌም ገሥግሠው በመምጣት ሕዝቡን በማስገደድ የኢየሩሳሌምን ከተማ እንደገና ከመሥራት አገዱአቸው፤ 24ስለዚህ ዳርዮስ በፋርስ እስከ ነገሠበት እስከ ሁለተኛው ዓመት ድረስ የቤተ መቅደሱ ሥራ በመቋረጡ በጅምር ቀርቶ ነበር።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ