ዕዝራ 10:1-3
ዕዝራ 10:1-3 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዕዝራም እያለቀሰና በእግዚአብሔር ፊት እየወደቀ በጸለየና በተናዘዘ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ የወንድና የሴት፥ የሕፃናትም እጅግ ታላቅ ጉባኤ ወደ እርሱ ተሰበሰበ፤ ሕዝቡም እጅግ አለቀሱ። ከኤላም ልጆች ወገን የነበረውም የኢያሔል ልጅ ሴኬንያ ዕዝራን እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ “አምላካችንን በድለናል፤ የምድርንም አሕዛብ እንግዶች ሴቶችን አግብተናል፤ አሁን ግን ስለዚህ ነገር ገና ለእስራኤል ተስፋ አለ። አሁንም እንደ ጌታዬና የአምላካችንን ትእዛዝ እንደሚፈሩት ምክር፥ ሴቶችን ሁሉ፥ ከእነርሱም የተወለዱትን እንሰድድ ዘንድ ከአምላካችን ጋር ቃል ኪዳን እናድርግ። ተነሥ እንደ አምላካችንም ትእዛዝ ገሥፃቸው፤ እንደ ሕጉም ያድርጉ፤
ዕዝራ 10:1-3 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዕዝራ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ወድቆ በሚጸልይበት፣ በሚናዘዝበትና በሚያለቅስበት ጊዜ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች የሚገኙበት እጅግ ብዙ የእስራኤል ማኅበር በዙሪያው ተሰበሰበ፤ እነርሱም እንደዚሁ አምርረው አለቀሱ። ከዚያም ከኤላም ዘሮች አንዱ የሆነው የይሒኤል ልጅ ሴኬንያ ዕዝራን እንዲህ አለው፤ “በዙሪያችን ካሉት አሕዛብ፣ ባዕዳን ሴቶችን በማግባታችን ለአምላካችን ታማኞች ሆነን አልተገኘንም፤ ይህም ሆኖ አሁንም ለእስራኤል ተስፋ አለ። አሁንም እንደ ጌታዬ ምክርና የአምላካችንን ትእዛዝ እንደሚፈሩ ሰዎች እነዚህን ሴቶችና ልጆቻቸውን ለመስደድ በአምላካችን ፊት ቃል ኪዳን እንግባ፤ በሕጉም መሠረት ይፈጸም።
ዕዝራ 10:1-3 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዕዝራም እያለቀሰና በእግዚአብሔር ቤት ፊት እየወደቀ በጸለየና በተናዘዘ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ የወንድና የሴት የሕፃናትም እጅግ ታላቅ ጉባኤ ወደ እርሱ ተሰበሰበ፤ ሕዝቡም እጅግ አለቀሱ። ከኤላም ልጆች ወገን የነበረ የይሒኤል ልጅ ሴኬንያ ዕዝራን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “አምላካችንን በድለናል፤ የምድርን አሕዛብ እንግዶች ሴቶችን አግብተናል፤ አሁን ግን ስለዚህ ነገር ገና ለእስራኤል ተስፋ አለ። አሁንም እንደ ጌታዬና የአምላካችንን ትእዛዝ እንደሚፈሩት ምክር፥ ሴቶችን ሁሉ ከእነርሱም የተወለዱትን እንሰድድ ዘንድ ከአምላካችን ጋር ቃል ኪዳን እናድርግ፤ እንደ ሕጉም ይደረግ።
ዕዝራ 10:1-3 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ዕዝራ በቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ለጸሎት ተንበርክኮ እያለቀሰ የተፈጸመውን ኃጢአት ሁሉ ለእግዚአብሔር በሚናዘዝበት ጊዜ ወንዶችም፥ ሴቶችም፥ ሕፃናትም ጭምር ያሉበት ቊጥሩ የበዛ የእስራኤል ማኅበር መጥቶ በዙሪያው በመሰብሰብ በመረረ ሁኔታ ያለቅሱ ነበር። ከዚህም በኋላ ከዔላም ጐሣ የየሒኤል ልጅ ሸካንያ ዕዝራን እንዲህ አለው፦ “በእርግጥ እኛ በአካባቢአችን ካሉት አሕዛብ ባዕዳን ሴቶችን በማግባት በእግዚአብሔር ላይ የነበረንን እምነት አጓድለናል፤ ይህም ሁሉ ሆኖ አሁንም ለእስራኤል ተስፋ አለ። አሁን እንግዲህ እነዚህን ባዕዳን ሴቶች ከነልጆቻቸው ማሰናበት እንደሚገባን ለአምላካችን ቃል እንግባ፤ አንተ ጌታዬና የአምላካችንን ትእዛዝ የሚያከብሩ ሌሎችም የምትሰጡንን ምክር ሁሉ እንፈጽማለን፤ የእግዚአብሔር ሕግ የሚያዘውን ሁሉ እናደርጋለን፤
ዕዝራ 10:1-3 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ዕዝራ በእግዚአብሔር ቤት ፊት በግንባሩ ወድቆ እያለቀሰ በሚጸልይበትና በሚናዘዝበት ጊዜ፤ ወንዶች፥ ሴቶችና ሕፃናት የሚገኙበት እጅግ ታላቅ ጉባኤ ወደ እርሱ ተሰበሰበ፥ ሕዝቡም እጅግ አለቀሱ። ከዔላም ልጆች ወገን የነበረ፥ የይሒኤል ልጅ ሽካንያ ዕዝራን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለአምላካችን ታማኞች አልሆንም፥ የምድሪቱን ሕዝቦች እንግዶች ሴቶችን አግብተናል፥ አሁንም ግን በዚህ ነገር ለእስራኤል ተስፋ አለ። ስለዚህ ከአምላካችን ጋር ቃል ኪዳን እናድርግ፥ ሚስቶችን ሁሉ ከእነርሱ የተወለዱትንም እንላካቸው፤ እንደ ጌታዬና በአምላካችን ትእዛዝ እንደሚንቀጠቀጡ ሕዝቦች ምክር፥ እንደ ሕጉም ይደረግ።