መጽሐፈ ዕዝራ 10
10
ከባዕዳን ጋር የተፈጸመውን ጋብቻ ለማስቀረት የተደረገ ጥረት
1ዕዝራም እያለቀሰና በእግዚአብሔር ቤት ፊት እየወደቀ በጸለየና በተናዘዘ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ የወንድና የሴት የሕፃናትም እጅግ ታላቅ ጉባኤ ወደ እርሱ ተሰበሰበ፤ ሕዝቡም እጅግ አለቀሱ። 2ከኤላም ልጆች ወገን የነበረ የይሒኤል ልጅ ሴኬንያ ዕዝራን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “አምላካችንን በድለናል፤ የምድርን አሕዛብ እንግዶች ሴቶችን አግብተናል፤ አሁን ግን ስለዚህ ነገር ገና ለእስራኤል ተስፋ አለ። 3አሁንም እንደ ጌታዬና የአምላካችንን ትእዛዝ እንደሚፈሩት ምክር፥ ሴቶችን ሁሉ ከእነርሱም የተወለዱትን እንሰድድ ዘንድ ከአምላካችን ጋር ቃል ኪዳን እናድርግ፤ እንደ ሕጉም ይደረግ። 4ይህም ነገር ለአንተ ይገባልና፥ እኛም ከአንተ ጋር ነንና ተነሣ! አይዞህ፤ አድርገው።”
5ዕዝራም ተነሣ፤ አለቆቹንና ካህናቱን፥ ሌዋውያኑንና እስራኤልን ሁሉ እንደዚህ ቃል ያደርጉ ዘንድ አማለ፤ እነርሱም ማሉ። 6ዕዝራም ከእግዚአብሔር ቤት ፊት ተነሥቶ ወደ ኤልያሴብ ልጅ ወደ ዮሐናን ጓዳ ገባ፤ ስለ ምርኮኞቹም ኃጢአት ያለቅስ ነበርና ገብቶ እንጀራ አልበላም፤ ውኃም አልጠጣም። 7-8ምርኮኞቹም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ፥ እንደ አለቆቹና እንደ ሽማግሌዎችም ምክር በሦስት ቀን ውስጥ ያልመጣ ሁሉ ንብረቱ ሁሉ እንዲወረስ፥ እርሱም ከምርኮው ጉባኤ እንዲለይ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አዋጅ ነገሩ።
9ሦስት ቀንም ሳያልፍ በዘጠነኛው ወር ከወሩም በሀያኛው ቀን የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሁሉ ስለዚህ ነገርና ስለ ታላቁ ዝናብ እየተንቀጠቀጡ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ባለው አደባባይ ተቀመጡ። 10ካህኑም ዕዝራ ተነሥቶ፦ “ተላልፋችኋል፤ የእስራኤልን በደል ታበዙ ዘንድ እንግዶችን ሴቶች አግብታችኋል። 11አሁንም ለአባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር ተናዘዙ፤ ደስ የሚያሰኘውንም አድርጉ፤ ከምድርም አሕዛብና ከእንግዶች ሴቶች ተለዩ” አላቸው። 12ጉባኤውም ሁሉ በታላቅ ድምፅ መልሰው እንዲህ አሉ፦ “እንደ ተናገርኸን እናደርግ ዘንድ ይገባናል። 13ነገር ግን የሕዝቡ ቍጥር ብዙ ነው፤ ጊዜውም የትልቅ ዝናብ ጊዜ ነው፤ በሜዳም ልንቆም አንችልም፤ በዚህም ነገር እጅግ በድለናልና ይህ ሥራ የአንድ ወይም የሁለት ቀን ሥራ አይደለም። 14አለቆቻችንም በጉባኤው ሁሉ ፋንታ ይቁሙ፤ ስለዚህም ነገር የአምላካችን ጽኑ ቍጣ ከእኛ ይመለስ ዘንድ እንግዶቹን ሴቶች ያገቡት በከተሞቻችን ያሉት ሁሉ በተቀጠረው ጊዜ ይምጡ፤ ከእነርሱም ጋር የከተማ ሁሉ ሽማግሌዎችና ፈራጆች ይምጡ።” 15ነገር ግን የአሣሄል ልጅ ዮናታንና የቴቁዋ ልጅ የሕዝያ ይህን ነገር ተቃወሙ፤ ሜሱላምና ሌዋዊዉ ሳባታይ ረዱአቸው።
16ምርኮኞቹም እንዲህ አደረጉ፤ ካህኑ ዕዝራም የአባቶችም ቤቶች አለቆች በየአባቶቻቸው ቤቶች ተለዩ፤ ሁሉም በየስማቸው ተጻፉ፤ በአሥረኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ነገሩን ይመረምሩ ዘንድ ተቀመጡ። 17እስከ መጀመሪያው ወር እስከ መጀመሪያው ቀን ድረስ ሠርተው፥ እንግዶቹን ሴቶች ያገቡትን ሰዎች ሁሉ መርምረው ጨረሱ።
ከባዕዳን ሰቶች የተጋቡ ሰዎች
18ከካህናቱም ወገን ልጆች እንግዶቹን ሴቶች ያገቡ ሰዎች ተገኙ፤ ከኢዮሴዴቅ ልጅ ከኢያሱ ልጆችና ከወንድሞቹ፥ መዕሤያ፥ አልዓዛር፥ ያሪብ፥ ጎዶልያስ። 19ሚስቶቻቸውን ይፈቱ ዘንድ እጃቸውን ሰጡ፤ ስለ በደላቸውም ከመንጋው አንድ አውራ በግ ለበደል መሥዋዕት አቀረቡ። 20ከኢሜር ልጆችም፤ አናኒና ዝባድያ። 21ከካሪም ልጆችም፤ መዕሤያ፥ ኤልያስ፥ ሸማያ፥ ይሒኤል፥ ዖዝያ። 22ከፋስኩር ልጆችም፤ ኤልዮዔናይ፥ መዕሤያ፥ ይስማኤል፥ ናትናኤል፥ ዮዛባት፥ ኤልዓሣ።
23ከሌዋውያንም፤ ዮዛባት፥ ሰሜኢ፥ ቆሊጣስ የሚባል ቆልያ፥ ፈታያ፥ ይሁዳ፥ አልዓዛር።
24ከመዘምራንም፤ ኤልያሴብ፤ ከበረኞችም፤ ሰሎም፥ ጤሌም፥ ኡሪ።
25ከእስራኤልም፤ ከፋሮስ ልጆች፤ ራምያ፥ ይዝያ፥ መልክያ፥ ሚያሚን፥ አልዓዛር፥ መልክያ፥ በናያስ። 26ከኤላም ልጆችም፤ መታንያ፥ ዘካርያስ፥ ይሒኤል፥ አብዲ፥ ይሬሞት፥ ኤልያ። 27ከዛቱዕ ልጆችም፤ ዔሊዮ ዔናይ፥ ኢልያሴብ፥ መታንያ፥ ይሬሞት፥ ዛባድ፥ ዓዚዛ። 28ከቤባይ ልጆችም፤ ይሆሐናን፥ ሐናንያ፥ ዘባይ፥ አጥላይ። 29ከባኒ ልጆችም፤ ሜሱላም፥ መሉክ፥ ዓዳያ፥ ያሱብ፥ ሸዓል፥ ራሞት። 30ከፈሐት ሞዓብ ልጆችም፤ ዓድና፥ ክላል፥ በናያስ፥ መዕሤያ፥ መታንያ፥ ባስልኤል፥ ቢንዊ፥ ምናሴ። 31ከካሪም ልጆችም፤ አልዓዛር፥ ይሺያ፥ መልክያ፥ 32ሸማያ፥ ስምዖን፥ ብንያም፥ መሉክ፥ ሰማራያ። 33ከሐሱም ልጆችም፤ መትናያ፥ መተታ፥ ዛባድ፥ ኤሊፋላት፥ ይሬማይ፥ ምናሴ፥ ሰሜኢ። 34ከባኒ ልጆችም፤ መዕዳይ፥ ዓምራም፥ 35ኡኤል፥ በናያስ፥ ቤድያ፥ ኬልቅያ 36-37ወንያ፥ ሜሪሞት፥ ኤልያሴብ፥ መታንያ፥ 38መትናይ፥ የዕሡ፥ ባኒ፥ ቢንዊ፥ ሰሜኢ፥ 39-40ሰሌምያ፥ ናታን፥ ዓዳያ፥ መክነድባይ፥ 41ሴሴይ፥ ሸራይ፥ ኤዝርኤል፥ ሰሌምያ፥ ሰማራያ፥ ሰሎም፥ አማርያ፥ ዮሴፍ። 42-43ከናባው ልጆችም፤ ይዒኤል፥ መቲትያ፥ ዛባድ፥ ዘቢና፥ ያዳይ፥ ኢዮኤል፥ በናያስ። 44እነዚህ ሁሉ እንግዶቹን ሚስቶች አግብተው ነበር፤ ከእነዚህም ሚስቶች አያሌዎቹ ልጆችን ወልደው ነበር።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ 10: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ