የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፀአት 4:18-31

ዘፀአት 4:18-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ሙሴም ሄደ፤ ወደ አማቱ ወደ ዮቶ​ርም ተመ​ለሰ፥ “እስከ ዛሬ በሕ​ይ​ወት እንደ አሉ አይ ዘንድ ተመ​ልሼ ወደ ግብፅ ወደ ወን​ድ​ሞች እሄ​ዳ​ለሁ” አለው። ዮቶ​ርም ሙሴን፥ “በደ​ኅና ሂድ” አለው። ከብዙ ዘመ​ንም በኋላ የግ​ብፅ ንጉሥ ሞተ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሙሴን በም​ድ​ያም፥ “ነፍ​ስ​ህን የሚ​ሹ​አት ሰዎች ሁሉ ሞተ​ዋ​ልና ተመ​ል​ሰህ ወደ ግብፅ ሂድ” አለው። ሙሴም ሚስ​ቱ​ንና ልጆ​ቹን ወሰደ፤ በአ​ህ​ዮች ላይም አስ​ቀ​መ​ጣ​ቸው፤ ወደ ግብ​ፅም ሀገር ተመ​ለሰ፤ ሙሴም ያችን የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን በትር በእጁ ይዞ ሄደ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሙሴን አለው፥ “ወደ ግብፅ ተመ​ል​ሰህ ስት​ሄድ በእ​ጅህ ያደ​ረ​ግ​ሁ​ትን ተአ​ም​ራ​ቴን ሁሉ በፈ​ር​ዖን ፊት ታደ​ር​ገው ዘንድ ተመ​ል​ከት፤ እኔ ግን ልቡን አጸ​ና​ዋ​ለሁ፤ ሕዝ​ቡ​ንም አይ​ለ​ቅ​ቅም። አንተ ግን ፈር​ዖ​ንን እን​ዲህ ትለ​ዋ​ለህ፦ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር እን​ዲህ ይላል፥ “እስ​ራ​ኤል የበ​ኵር ልጄ ነው፤ ያመ​ል​ኩኝ ዘንድ ሕዝ​ቤን ልቀቅ አል​ሁህ፤ አን​ተም ልት​ለ​ቅ​ቃ​ቸው ባት​ፈ​ቅድ፤ እኔ የበ​ኵር ልጅ​ህን እን​ደ​ም​ገ​ድል ዕወቅ።” እን​ዲ​ህም ሆነ፤ በመ​ን​ገድ ላይ በአ​ደ​ረ​በት ስፍራ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መል​አክ ተገ​ና​ኘው፤ ሊገ​ድ​ለ​ውም ፈለገ። ሚስቱ ሲፓ​ራም ባል​ጩት ወሰ​ደች፤ የል​ጅ​ዋ​ንም ሸለ​ፈት ገረ​ዘች፤ “ይህ የልጄ የግ​ር​ዛቱ ደም ስለ እርሱ ፈንታ ይሁን” ብላ ከእ​ግሩ በታች ወደ​ቀች። ከእ​ር​ሱም ሄደ፤ የዚያ ጊዜ፥ “ይህ የልጄ የግ​ር​ዛቱ ደም ስለ እርሱ ፈንታ ይሁን” ብላ​ለ​ችና። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም አሮ​ንን አለው፥ “ሄደህ በም​ድረ በዳ ሙሴን ተገ​ና​ኘው፤” ሄዶም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ተራራ ተገ​ና​ኘው፤ እርስ በር​ሳ​ቸ​ውም ተሳ​ሳሙ። ሙሴም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የላ​ከ​ውን ቃል ሁሉ፥ የአ​ዘ​ዘ​ው​ንም ተአ​ም​ራት ሁሉ ለአ​ሮን ነገ​ረው። ሙሴና አሮ​ንም ሄዱ፤ የእ​ስ​ራ​ኤ​ል​ንም ልጆች ሽማ​ግ​ሌ​ዎች ሁሉ ሰበ​ሰቡ። አሮ​ንም እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ለሙሴ የነ​ገ​ረ​ውን ቃል ሁሉ ተና​ገረ፤ ተአ​ም​ራ​ቱ​ንም በሕ​ዝቡ ፊት አደ​ረገ። ሕዝ​ቡም አመኑ፤ ደስም አላ​ቸው፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የእ​ስ​ራ​ኤ​ልን ልጆች ጐብ​ኝ​ቶ​አ​ልና፤ ጭን​ቀ​ታ​ቸ​ው​ንም አይ​ቶ​አ​ልና፤ ሕዝ​ቡም ራሳ​ቸ​ውን ዝቅ አድ​ር​ገው ሰገዱ።

ዘፀአት 4:18-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ሙሴም ወደ ዐማቱ ወደ ዮቶር ተመልሶ ሄደና፣ “ወገኖቼ እስካሁን በሕይወት መኖራቸውን አይ ዘንድ ወደ ግብፅ ተመልሼ እንድሄድ እባክህ ፍቀድልኝ” አለው። ዮቶርም፣ “ሂድ፤ በሰላም ያግባህ” አለው። ሙሴ በምድያም ሳለ እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “አንተን ሊገድሉህ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ” አለው። ስለዚህ ሙሴ ሚስቱንና ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ፣ ወደ ግብፅ አገር መመለስ ጀመረ፤ የእግዚአብሔርንም (ኤሎሂም) በትር በእጁ ይዞ ነበር። እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፣ “ወደ ግብፅ በምትመለስበት ጊዜ በሰጠሁህ ኀይል የምትሠራቸውን ታምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ። እኔ ግን ሕዝቡን እንዳይለቅ ልቡን አደነድነዋለሁ። ስለዚህ ለፈርዖን እንዲህ በለው፣ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ ይላል፤ “እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ ያመልከኝ ዘንድ ልጄን ልቀቀው” ብዬህ ነበር፤ አንተ ግን እንዳይሄድ ከለከልኸው፤ ስለዚህ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ።’ ” ሙሴ በጕዞ ላይ በእንግዳ ማረፊያ ስፍራ ውስጥ ሳለ እግዚአብሔር (ያህዌ) አግኝቶት ሊገድለው ፈልጎ ነበር። ሚስቱ ሲፓራ ግን ስለታም ባልጩት ወስዳ ልጇን ገረዘችው፤ በሸለፈቱ የሙሴን እግር በመንካትም “አንተ ለእኔ የደም ሙሽራዬ ነህ” አለችው። ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ተወው፤ “አንተ የደም ሙሽራ ነህ” ያለችው በግርዛቱ ምክንያት ነው። እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን፣ “ሙሴን እንድታገኘው ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው። እርሱም ሙሴን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተራራ አገኘው፤ ሳመውም። ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲናገር የላከውን ቃል በሙሉና እንዲፈጽማቸው ስላዘዘው ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ ለአሮን ነገረው። ሙሴና አሮን ሄዱና የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በአንድነት ሰበሰቡ፤ አሮንም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ የነገረውን ቃል በሙሉ ነገራቸው፤ ታምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እነርሱ የሚገድደው መሆኑንና መከራቸውን ማየቱን በሰሙ ጊዜ ተንበረከኩ፤ በስግደትም አመለኩት።

ዘፀአት 4:18-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ሙሴም ሄደ፤ ወደ አማቱ ወደ ዮቶር ተመለሰ፤ “እስከ ዛሬ በሕይወት እንዳሉ አይ ዘንድ ተመልሼ ወደ ግብፅ ወደ ወንድሞቼ ልሂድ፤” አለው። ዮቶርም ሙሴን፦ “በሰላም ሂድ” አለው። እግዚአብሔርም ሙሴን በምድያም፥ “ነፍስህን የሚሹአት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ፤” አለው። ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፤ በአህያ ላይም አስቀመጣቸው፤ ወደ ግብፅም አገር ተመለሰ፤ ሙሴም የእግዚአብሔርን በትር ይዞ ሄደ። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “ወደ ግብፅ ስትመለስ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት ታደርገው ዘንድ ተመልከት፤ እኔ ግን ልቡን አጸናዋለሁ፤ ሕዝቡንም አይለቅቅም። ፈርዖንንም፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘እስራኤል የበኩር ልጄ ነው፤ ይገዛልኝ ዘንድ ልጄን ልቀቅ’ አልሁህ፤ አንተም ትለቅቀው ዘንድ እንቢ አልህ፤ እነሆ እኔ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ”’ ትለዋለህ። እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ ባደረበት ስፍራ እግዚአብሔር ተገናኘው፤ ሊገድለውም ፈለገ። ሲፓራም ሚስቱ ባልጩት ወሰደች፤ የልጅዋንም ሸለፈት ገረዘች፤ ወደ እግሩም ጣለችው፤ አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ፤” አለች። ከእርሱም ፈቀቅ አለ። የዚያን ጊዜ ስለ ግርዛቱ “አንተ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። እግዚአብሔርም አሮንን፦ “ሄደህ በምድረ በዳ ሙሴን ተገናኘው፤” አለው፤ ሄዶም በእግዚአብሔር ተራራ ተገናኘው፤ ሳመውም። ሙሴም እግዚአብሔር በእርሱ ዘንድ የላከውን ቃል ሁሉ ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ለአሮን ነገረው። ሙሴና አሮንም ሄዱ የእስራኤልንም ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰቡ። አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን ቃል ሁሉ ተናገረ፤ ተአምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ልጆች እንደ ጎበኘ ጭንቀታቸውንም እንዳየ በሰሙ ጊዜ፥ አጎነበሱ፤ ሰገዱም።

ዘፀአት 4:18-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሙሴም ወደ ዐማቱ ወደ የትሮ ተመልሶ ሄደና “በግብጽ ወደሚኖሩት ወገኖቼ ተመልሼ ሄጄ በሕይወት መኖራቸውን እንዳይ ፍቀድልኝ” አለው። የትሮም ፈቅዶ “በሰላም ሂድ” አለው። ሙሴ ገና በምድያም ሳለ እግዚአብሔር “ሊገድሉህ የሚፈልጉት ሁሉ ስለ ሞቱ ወደ ግብጽ ተመልሰህ ሂድ” አለው። ስለዚህም ሙሴ ሚስቱንና ወንዶች ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ ወደ ግብጽ መጓዝ ጀመረ፤ ተአምራት የሚገለጥበት የእግዚአብሔርንም በትር በእጁ ይዞ ነበር። እንደገናም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ አሁን ወደ ግብጽ መመለስህ ስለ ሆነ፥ በሰጠሁህ ኀይል የምታደርጋቸውን ተአምራት በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ፤ ሆኖም እኔ የፈርዖንን ልብ ስለማደነድን ሕዝቡን በቀላሉ አይለቅም። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር ለፈርዖን የምለውን እንዲህ ብለህ ትነግረዋለህ፤ ‘እስራኤል የበኲር ልጄ ነው፤ እኔም ይህ ልጄ እኔን ያመልክ ዘንድ እንድትለቀው ነገርኩህ፤ አንተ ግን እምቢ አልክ፤ ስለዚህ አሁን የአንተን የበኲር ልጅ እገድላለሁ።’ ” ሙሴ ወደ ግብጽ በመጓዝ ላይ ሳለ ባረፈበት ሰፈር እግዚአብሔር አግኝቶት በሞት ሊቀጣው ፈለገ። ከዚያ በኋላ ሲፖራ ሮጣ ሄዳ ባልጩት አመጣችና የልጅዋን ሸለፈት ገረዘች፤ የሙሴንም እግር በሸለፈቱ ዳስሳ “በእርግጥ አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። እግዚአብሔርም ለሙሴ ምሕረት አደረገለት፤ እርስዋም “ከግዝረት ሥርዓት የተነሣ አንተ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። በዚያኑ ጊዜ እግዚአብሔር አሮንን “ከሙሴ ጋር ለመገናኘት ወደ በረሓው ሂድ” አለው። እርሱም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ሄደ፤ በዚያም ሙሴን አግኝቶ ሳመው። ሙሴም እግዚአብሔር ወደ ግብጽ እንዲመለስ ባዘዘው ጊዜ የነገረውን ቃልና እንዲፈጽማቸው ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ለአሮን አስረዳው። ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ግብጽ ወርደው የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በአንድነት ሰበሰቡ። አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የተናገረውን ሁሉ ገለጠላቸው፤ ሙሴም ተአምራትን ሁሉ በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፤ እግዚአብሔር ወደ እነርሱ መጥቶ እንደ ጐበኛቸውና የደረሰባቸውንም የግፍ ጭቈና ማየቱን በሰሙ ጊዜ ተንበርክከው ሰገዱ።

ዘፀአት 4:18-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ሙሴም ሄደ፥ ወደ አማቱ ወደ ይትሮ ተመለሰ፥ እርሱም፦ “እባክህን በግብጽ ወዳሉ ዘመዶቼ እንድመለስ እስካሁንም በሕይወት እንዳሉ ሄጄ እንዳይ ፍቀድልኝ” አለው። ይትሮም ሙሴን፦ “በሰላም ሂድ” አለው። ጌታም ሙሴን በምድያን፦ “ወደ ግብጽ ተመልሰህ ሂድ ነፍስህን የሚፈልጓት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና” አለው። ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፥ በአህያ ላይም አስቀመጣቸው፥ ወደ ግብጽም ምድር ተመለሰ፤ ሙሴም የእግዚአብሔርን በትር ይዞ ሄደ። ጌታም ሙሴን አለው፦ “ወደ ግብጽ ስትመለስ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራት ሁሉ ተመልከት በፈርዖንም ፊት ታደርጋቸዋለህ፤ እኔም ልቡን አጸናዋለሁ፥ ሕዝቡንም አይለቅቅም። ፈርዖንንም ትለዋለህ፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እስራኤል የበኩር ልጄ ነው፤ እንዲያገለግለኝ ልጄን ልቀቅ አልሁህ፤ አንተም ትለቅቀው ዘንድ እንቢ አልህ፤ እነሆ እኔ የበኩር ልጅህን እገድላለሁ።’” እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ በማደሪያው ስፍራ ጌታ ተገናኘው፥ ሊገድለውም ፈለገ። ፂፖራም ባልጩት ወሰደች፥ የልጇንም ሸለፈት ገረዘች፥ እግሩንም ነክታ፦ “አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። ከእርሱም ፈቀቅ አለ። የዚያን ጊዜ፦ “ለግርዛቱ የደም ሙሽራ” አለች። ጌታም አሮንን፦ “ሙሴን ለመገናኘት ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው፤ ሄዶም በእግዚአብሔር ተራራ ተገናኘው፥ ሳመውም። ሙሴም ለአሮን በእርሱ ዘንድ የላከውን የጌታን ቃል ሁሉ ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ነገረው። ሙሴና አሮንም ሄዱ የእስራኤልን ልጆች ሽማግሌዎችንም ሁሉ ሰበሰቡ። አሮንም ጌታ ለሙሴ የተናገረውን ቃላት ሁሉ ተናገረ፥ ተአምራቶቹንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፤ ጌታ የእስራኤልን ልጆች እንደተመለከተ ጭንቀታቸውንም እንዳየ በሰሙ ጊዜ፥ አጎነበሱ ሰገዱም።