ሙሴም ወደ ዐማቱ ወደ ዮቶር ተመልሶ ሄደና፣ “ወገኖቼ እስካሁን በሕይወት መኖራቸውን አይ ዘንድ ወደ ግብፅ ተመልሼ እንድሄድ እባክህ ፍቀድልኝ” አለው። ዮቶርም፣ “ሂድ፤ በሰላም ያግባህ” አለው። ሙሴ በምድያም ሳለ እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “አንተን ሊገድሉህ የሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ” አለው። ስለዚህ ሙሴ ሚስቱንና ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ፣ ወደ ግብፅ አገር መመለስ ጀመረ፤ የእግዚአብሔርንም (ኤሎሂም) በትር በእጁ ይዞ ነበር። እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፣ “ወደ ግብፅ በምትመለስበት ጊዜ በሰጠሁህ ኀይል የምትሠራቸውን ታምራት ሁሉ በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ። እኔ ግን ሕዝቡን እንዳይለቅ ልቡን አደነድነዋለሁ። ስለዚህ ለፈርዖን እንዲህ በለው፣ ‘እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲህ ይላል፤ “እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ ያመልከኝ ዘንድ ልጄን ልቀቀው” ብዬህ ነበር፤ አንተ ግን እንዳይሄድ ከለከልኸው፤ ስለዚህ የበኵር ልጅህን እገድላለሁ።’ ” ሙሴ በጕዞ ላይ በእንግዳ ማረፊያ ስፍራ ውስጥ ሳለ እግዚአብሔር (ያህዌ) አግኝቶት ሊገድለው ፈልጎ ነበር። ሚስቱ ሲፓራ ግን ስለታም ባልጩት ወስዳ ልጇን ገረዘችው፤ በሸለፈቱ የሙሴን እግር በመንካትም “አንተ ለእኔ የደም ሙሽራዬ ነህ” አለችው። ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ) ተወው፤ “አንተ የደም ሙሽራ ነህ” ያለችው በግርዛቱ ምክንያት ነው። እግዚአብሔር (ያህዌ) አሮንን፣ “ሙሴን እንድታገኘው ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው። እርሱም ሙሴን በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተራራ አገኘው፤ ሳመውም። ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) እንዲናገር የላከውን ቃል በሙሉና እንዲፈጽማቸው ስላዘዘው ታምራዊ ምልክቶች ሁሉ ለአሮን ነገረው። ሙሴና አሮን ሄዱና የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በአንድነት ሰበሰቡ፤ አሮንም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ የነገረውን ቃል በሙሉ ነገራቸው፤ ታምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፣ እግዚአብሔር (ያህዌ) ስለ እነርሱ የሚገድደው መሆኑንና መከራቸውን ማየቱን በሰሙ ጊዜ ተንበረከኩ፤ በስግደትም አመለኩት።
ዘፀአት 4 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፀአት 4
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፀአት 4:18-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos