ሙሴም ወደ ዐማቱ ወደ የትሮ ተመልሶ ሄደና “በግብጽ ወደሚኖሩት ወገኖቼ ተመልሼ ሄጄ በሕይወት መኖራቸውን እንዳይ ፍቀድልኝ” አለው። የትሮም ፈቅዶ “በሰላም ሂድ” አለው። ሙሴ ገና በምድያም ሳለ እግዚአብሔር “ሊገድሉህ የሚፈልጉት ሁሉ ስለ ሞቱ ወደ ግብጽ ተመልሰህ ሂድ” አለው። ስለዚህም ሙሴ ሚስቱንና ወንዶች ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ ወደ ግብጽ መጓዝ ጀመረ፤ ተአምራት የሚገለጥበት የእግዚአብሔርንም በትር በእጁ ይዞ ነበር። እንደገናም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ አሁን ወደ ግብጽ መመለስህ ስለ ሆነ፥ በሰጠሁህ ኀይል የምታደርጋቸውን ተአምራት በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ፤ ሆኖም እኔ የፈርዖንን ልብ ስለማደነድን ሕዝቡን በቀላሉ አይለቅም። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር ለፈርዖን የምለውን እንዲህ ብለህ ትነግረዋለህ፤ ‘እስራኤል የበኲር ልጄ ነው፤ እኔም ይህ ልጄ እኔን ያመልክ ዘንድ እንድትለቀው ነገርኩህ፤ አንተ ግን እምቢ አልክ፤ ስለዚህ አሁን የአንተን የበኲር ልጅ እገድላለሁ።’ ” ሙሴ ወደ ግብጽ በመጓዝ ላይ ሳለ ባረፈበት ሰፈር እግዚአብሔር አግኝቶት በሞት ሊቀጣው ፈለገ። ከዚያ በኋላ ሲፖራ ሮጣ ሄዳ ባልጩት አመጣችና የልጅዋን ሸለፈት ገረዘች፤ የሙሴንም እግር በሸለፈቱ ዳስሳ “በእርግጥ አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። እግዚአብሔርም ለሙሴ ምሕረት አደረገለት፤ እርስዋም “ከግዝረት ሥርዓት የተነሣ አንተ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። በዚያኑ ጊዜ እግዚአብሔር አሮንን “ከሙሴ ጋር ለመገናኘት ወደ በረሓው ሂድ” አለው። እርሱም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ሄደ፤ በዚያም ሙሴን አግኝቶ ሳመው። ሙሴም እግዚአብሔር ወደ ግብጽ እንዲመለስ ባዘዘው ጊዜ የነገረውን ቃልና እንዲፈጽማቸው ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ለአሮን አስረዳው። ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ግብጽ ወርደው የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በአንድነት ሰበሰቡ። አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የተናገረውን ሁሉ ገለጠላቸው፤ ሙሴም ተአምራትን ሁሉ በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፤ እግዚአብሔር ወደ እነርሱ መጥቶ እንደ ጐበኛቸውና የደረሰባቸውንም የግፍ ጭቈና ማየቱን በሰሙ ጊዜ ተንበርክከው ሰገዱ።
ኦሪት ዘጸአት 4 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘጸአት 4:18-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos