የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 4

4
እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ተአምራዊ ኀይል
1ሙሴም እግዚአብሔርን “እስራኤላውያን ‘እግዚአብሔር አልተገለጠልህም’ ብለው ባያምኑኝና ቃሌን ባይሰሙ ምን እላቸዋለሁ?” አለው።
2እግዚአብሔርም “በእጅህ የያዝከው ምንድን ነው?” አለው።
እርሱም “በትር ነው” አለ።
3እግዚአብሔርም “ወደ መሬት ጣለው” አለው፤ ሙሴም ወደ መሬት በጣለው ጊዜ በትሩ ተለውጦ እባብ ሆነ፤ ሙሴም ከእርሱ ሸሸ። 4እግዚአብሔር ግን ሙሴን “እጅህን ዘርጋና ጅራቱን ይዘህ አንሣው” አለው። ሙሴም እጁን ዘርግቶ ጅራቱን በመያዝ ባነሣው ጊዜ እንደገና በትር ሆነ። 5እግዚአብሔርም “የቀድሞ አባቶቻቸው የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተገለጥኩልህ ለእስራኤላውያን ማስረጃ ይሆን ዘንድ በዚህ ተጠቀም” አለው።
6እንደገናም እግዚአብሔር ሙሴን “እጅህን ወደ ብብትህ አስገባው” አለው፤ እርሱም እጁን ወደ ብብቱ አስገባ፤ እጁንም ከብብቱ ባወጣው ጊዜ እንደ በረዶ ነጭ ሆነ። 7እግዚአብሔርም “እጅህን እንደገና ወደ ብብትህ አስገባ” አለው። ሙሴም እጁን ወደ ብብቱ አስገባ፤ መልሶም ባወጣው ጊዜ ተመልሶ እነሆ፥ እንደ ሌላው ሰውነቱ ጤናማ ሆነ። 8እግዚአብሔርም እንዲህ አለ፤ “እንግዲህ በመጀመሪያው ተአምር ባያምኑና እውነት ነው ብለው ባይቀበሉህ፥ ሁለተኛውን ተአምር ያምናሉ። 9እነዚህን ሁለት ተአምራት አይተው ባያምኑና ቃልህንም ባይሰሙ፥ ከዐባይ ወንዝ ጥቂት ውሃ ወስደህ በመሬት ላይ አፍስሰው፤ ከአባይ ወንዝ የወሰድከውም ውሃ በደረቀ ምድር ላይ ወደ ደም ይለወጣል።”
10ሙሴ ግን እንዲህ አለ፤ “እባክህ ጌታ ሆይ፥ ወደዚያ አትላከኝ፤ ቀድሞም ሆነ ወይም አሁን አንተ ከእኔ ጋር መነጋገር ከጀመርክበት ጊዜ አንሥቶ የመናገር ችሎታ የለኝም፤ እኔ አንደበቴ የሚኮላተፍና አጥርቼ ለመናገር የማልችል ነኝ።”
11ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለሰው አፍን የፈጠረለት ማነው? ድዳ ወይም ደንቆሮ፥ ዐይኑ እንዲያይ ወይም እንዳያይ የሚያደርግስ ማነው? ይህን ሁሉ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አይደለሁምን? 12ስለዚህ አሁን ሂድ! እኔም ከአንተ ጋር ሆኜ መናገር እንድትችል አደርጋለሁ፤ ምን መናገር እንደሚገባህ እነግርሃለሁ።”
13ሙሴም “እባክህ ጌታ ሆይ፥ ሌላ ሰው ላክ” አለው።
14በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ሙሴን እጅግ ተቈጥቶ እንዲህ አለው፤ “ሌዋዊ የሆነው ወንድምህ አሮን አለ አይደለምን? እርሱ ጥሩ ተናጋሪ መሆኑን ዐውቃለሁ፤ እንዲያውም አሁን ወደ አንተ እየመጣ ነው፤ በሚያይህም ጊዜ ከልብ ደስ ይለዋል። 15ለእርሱ ትነግረዋለህ፤ የሚናገረውንም ቃል ታስረዳዋለህ፤ ሁለታችሁም እንዴት መናገር እንደምትችሉና ምን ማድረግ እንደሚገባችሁ አስተምራችኋለሁ፤ 16እርሱ አንተን ወክሎ ይናገራል፤ በአንተም ስም ቃሉን ለሕዝቡ ያስተላልፋል፤ አንተም ለእርሱ እንደ አምላክ ትሆናለህ። 17ተአምራት የምታሳይበትንም ይህን በትር ይዘህ ሂድ።”
የሙሴ ወደ ግብጽ መመለስ
18ሙሴም ወደ ዐማቱ ወደ የትሮ ተመልሶ ሄደና “በግብጽ ወደሚኖሩት ወገኖቼ ተመልሼ ሄጄ በሕይወት መኖራቸውን እንዳይ ፍቀድልኝ” አለው። የትሮም ፈቅዶ “በሰላም ሂድ” አለው።
19ሙሴ ገና በምድያም ሳለ እግዚአብሔር “ሊገድሉህ የሚፈልጉት ሁሉ ስለ ሞቱ ወደ ግብጽ ተመልሰህ ሂድ” አለው። 20ስለዚህም ሙሴ ሚስቱንና ወንዶች ልጆቹን በአህያ ላይ አስቀምጦ ወደ ግብጽ መጓዝ ጀመረ፤ ተአምራት የሚገለጥበት የእግዚአብሔርንም በትር በእጁ ይዞ ነበር።
21እንደገናም እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ አሁን ወደ ግብጽ መመለስህ ስለ ሆነ፥ በሰጠሁህ ኀይል የምታደርጋቸውን ተአምራት በፈርዖን ፊት መፈጸም እንዳለብህ አትዘንጋ፤ ሆኖም እኔ የፈርዖንን ልብ ስለማደነድን ሕዝቡን በቀላሉ አይለቅም። 22በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር ለፈርዖን የምለውን እንዲህ ብለህ ትነግረዋለህ፤ ‘እስራኤል የበኲር ልጄ ነው፤ 23እኔም ይህ ልጄ እኔን ያመልክ ዘንድ እንድትለቀው ነገርኩህ፤ አንተ ግን እምቢ አልክ፤ ስለዚህ አሁን የአንተን የበኲር ልጅ እገድላለሁ።’ ” #ዘፀ. 12፥29።
24ሙሴ ወደ ግብጽ በመጓዝ ላይ ሳለ ባረፈበት ሰፈር እግዚአብሔር አግኝቶት በሞት ሊቀጣው ፈለገ። 25ከዚያ በኋላ ሲፖራ ሮጣ ሄዳ ባልጩት አመጣችና የልጅዋን ሸለፈት ገረዘች፤ የሙሴንም እግር በሸለፈቱ ዳስሳ “በእርግጥ አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። 26እግዚአብሔርም ለሙሴ ምሕረት አደረገለት፤ እርስዋም “ከግዝረት ሥርዓት የተነሣ አንተ የደም ሙሽራ ነህ” አለች።
27በዚያኑ ጊዜ እግዚአብሔር አሮንን “ከሙሴ ጋር ለመገናኘት ወደ በረሓው ሂድ” አለው። እርሱም ወደ እግዚአብሔር ተራራ ሄደ፤ በዚያም ሙሴን አግኝቶ ሳመው። 28ሙሴም እግዚአብሔር ወደ ግብጽ እንዲመለስ ባዘዘው ጊዜ የነገረውን ቃልና እንዲፈጽማቸው ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ለአሮን አስረዳው። 29ከዚህም በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ግብጽ ወርደው የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በአንድነት ሰበሰቡ። 30አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የተናገረውን ሁሉ ገለጠላቸው፤ ሙሴም ተአምራትን ሁሉ በሕዝቡ ፊት አደረገ። 31ሕዝቡም አመኑ፤ እግዚአብሔር ወደ እነርሱ መጥቶ እንደ ጐበኛቸውና የደረሰባቸውንም የግፍ ጭቈና ማየቱን በሰሙ ጊዜ ተንበርክከው ሰገዱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ