የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 3

3
የሙሴ መጠራት
1እነሆ፥ ሙሴ የምድያም ካህን የሆነውን የዐማቹን የየትሮንን በጎች ይጠብቅ ነበር፤ መንጋውንም እየነዳ ከበረሓው ማዶ ወዳለው የእግዚአብሔር ተራራ እየተባለ ወደሚጠራው ወደ ሲና መጣ። #3፥1 በሌላ ቦታ ኮሬብ ተብሎም ይጠራል። 2እዚያም የእግዚአብሔር መልአክ በቊጥቋጦ ውስጥ በተቀጣጠለ የእሳት ነበልባል መካከል ሆኖ ተገለጠለት፤ ሙሴም ቊጥቋጦው በእሳት ተያይዞ ሳለ ምንም አለመቃጠሉን ተመለከተና፥ 3“ይህ እንዴት አስገራሚ ሁኔታ ነው? ቊጥቋጦውስ እንዴት አይቃጠልም? ቀርቤ መመልከት አለብኝ” አለ። #ሐ.ሥ. 7፥30-34።
4ሙሴም ሁኔታውን ለማየት በቀረበ ጊዜ እግዚአብሔር ተመለከተው፤ በቊጥቋጦውም መካከል ሆኖ “ሙሴ! ሙሴ!” ብሎ ጠራው።
ሙሴም “እነሆ፥ አለሁ” አለ።
5እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ወደዚህ አትቅረብ፤ የቆምክባት ምድር የተቀደሰች ስለ ሆነች ጫማህን አውልቅ፤ 6እኔ የቀድሞ አባቶችህ የአብርሃም፥ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ነኝ፤” በዚህ ጊዜ ሙሴ እግዚአብሔርን ፊት ለፊት ማየት ስለ ፈራ ፊቱን ሸፈነ።
7ከዚያም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፤ “በግብጽ ያለውን የሕዝቤን ጭንቀት አይቻለሁ፤ በአስጨናቂዎቻቸው ምክንያት የሚጮኹትን ጩኸት ሰምቼአለሁ፤ ጭንቀታቸውንም ዐውቃለሁ። 8እነርሱንም ከግብጻውያን እጅ ለማዳን ወርጃለሁ፤ ከግብጽም አውጥቼ አሁን ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን፥ የሚኖሩባትን፥ በማርና በወተት የበለጸገችውን ሰፊና ለም የሆነችውን ምድር እሰጣቸዋለሁ። 9እነሆ፥ የሕዝቤ የእስራኤል ጩኸት ወደ እኔ ደርሶአል፤ ግብጻውያን በእነርሱ ላይ የሚያደርሱባቸውን የግፍ ጭቈና ተመልክቻለሁ፤ 10ስለዚህ አሁን ሕዝቤን ከግብጽ ምድር ታወጣ ዘንድ ወደ ግብጽ ንጉሥ እልክሃለሁ።” 11ሙሴ ግን እግዚአብሔርን “ወደ ፈርዖን ሄጄ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ለማውጣት እኔ ማን ነኝ?” አለ።
12እግዚአብሔርም መልሶ “አይዞህ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔ እንደ ላክኹህም ምልክት የሚሆንህ ይህ ነው፤ ሕዝቤን ከግብጽ በምታወጣበት ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ እኔን ታመልኩኛላችሁ” አለው። #ዘፀ. 6፥2-3።
13ሙሴም “እኔ ወደ እስራኤል ሕዝብ ሄጄ ‘የቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ በምላቸው ጊዜ እነርሱ ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን እመልስላቸዋለሁ?” አለ።
14እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እኔ ‘ያለሁና የምኖር ነኝ፤’ ስለዚህም ‘እኔ ነኝ’ ወደ እናንተ ልኮኛል” በላቸው፤ #ዮሐ. 8፥58፤ ዕብ. 13፥8፤ ራዕ. 1፥4፤8። 15እግዚአብሔርም እንደገና ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በላቸው፦ የአባቶቻችሁ የአብርሃም፥ የይስሐቅ፥ የያዕቆብ አምላክ እግዚአብሔር ወደ እናንተ ልኮኛል፤ ይህ የዘለዓለም ስሜ ነው፤ በዚህም ስም ከትውልድ እስከ ትውልድ እታወቃለሁ። 16እንግዲህ ሂድና የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች ሁሉ በአንድነት ሰብስብ፤ የቀድሞ አባቶቻቸው የአብርሃም የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ እኔ እግዚአብሔር የተገለጥኩልህ መሆኔንም ንገራቸው፤ ወደ እነርሱ ወርጄ ግብጻውያን በእነርሱ ላይ ያደረሱባቸውን ግፍና ጭቈና መመልከቴን ንገራቸው። 17በግፍ ጭቈና ከሚሠቃዩባት ከግብጽ ምድር አውጥቼ እነሆ ዛሬ፥ ከነዓናውያን፥ ሒታውያን፥ አሞራውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን የሚኖሩባትን፥ በማርና በወተት የበለጸገች ሰፊና ለም የሆነች ምድር ልሰጣቸው ቃል ገብቻለሁ።
18“ሕዝቤም አንተ የምትነግራቸውን ሁሉ ይሰማሉ፤ ከዚያም በኋላ ከእስራኤል ሕዝብ አለቆች ጋር ሆነህ ወደ ግብጽ ንጉሥ ሂድና ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር ተገልጦልናል፤ ስለዚህም ለአምላካችን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እናቀርብ ዘንድ የሦስት ቀን መንገድ ተጒዘን ወደ በረሓ እንድንሄድ ፍቀድልን’ ብላችሁ ንገሩት። 19እርግጥ ነው በታላቅ ክንድ ካልተገደደ በቀር የግብጽ ንጉሥ እንደማይለቃችሁ ዐውቃለሁ። 20ስለዚህም እጅግ አስፈሪ የሆኑ ድንቅ ተአምራትን በማድረግ የኀይል ክንዴን ዘርግቼ ግብጻውያንን እቀጣለሁ፤ ከዚያም በኋላ እንድትወጡ ይፈቅድላችኋል።
21“በምትወጡበት ጊዜ ሕዝቡ በግብጻውያን ዘንድ ሞገስ እንዲያገኙ ስለማደርግ ባዶ እጃችሁን አትወጡም። #ዘፀ. 12፥35-36። 22የዕብራውያን ሴቶች እያንዳንዳቸው ጐረቤት በመሆን አብረዋቸው የሚኖሩትን ግብጻውያን ሴቶች ወርቅ፥ ብርና፥ ጌጣጌጥና ልብስ እንዲሰጡአቸው ይጠይቃሉ፤ ይህንንም ሁሉ ወስዳችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን ታለብሳላችሁ፤ በዚህም ዐይነት ግብጻውያንን በዝብዛችሁ ትወጣላችሁ።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ