የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘጸአት 5

5
ሙሴና አሮን ወደ ግብጽ ንጉሥ ፊት መቅረባቸው
1ከዚያም በኋላ ሙሴና አሮን ወደ ግብጽ ንጉሥ ሄደው “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ‘በበረሓ ለእኔ በዓል ለማድረግ እንዲሄዱ ሕዝቤን ልቀቅ’ ይልሃል” አሉት።
2ንጉሡም “ለመሆኑ እግዚአብሔር ማን ነው? የእርሱንስ ትእዛዝ ሰምቼ እስራኤልን የምለቀው ለምንድን ነው? እኔ እግዚአብሔርን አላውቅም፤ እስራኤልንም አለቅም” አለ።
3ሙሴና አሮንም “የዕብራውያን አምላክ ለእኛ ተገልጦልናል፤ የሦስት ቀን መንገድ ወደ በረሓ ተጒዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እናቀርብ ዘንድ ፍቀድልን፤ እኛ ይህን ባናደርግ በበሽታ ወይም በጦርነት እንድናልቅ ያደርጋል” ሲሉ መለሱለት።
4ንጉሡም እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ሙሴና አሮን ለምን ሕዝቡን ሥራ ታስፈታላችሁ? በሉ ወደ ሥራችሁ ተመለሱ!” 5ከዚያም ንጉሡ እንዲህ አለ፤ “እነሆ፥ አሁን እናንተ ከአገሬው ሕዝብ በዝታችኋል፤ እናንተ ሙሴና አሮን ደግሞ ሥራ ታስፈቱአቸዋላችሁ።”
6በዚያኑ ቀን ንጉሡ ፈርዖን ጨካኞች የሆኑትን ግብጻውያን አሠሪዎችንና የእስራኤላውያን ሠራተኞች አለቆችን እንዲህ ብሎ አዘዘ፥ 7“ለጡብ ሥራ የሚሆን ገለባ ለሕዝቡ እንደ ወትሮው አትስጡ፤ እነርሱ ራሳቸው ገለባውን ፈልገው ያምጡ፤ 8ነገር ግን ቀድሞ ይሠሩት የነበረውን ያኽል አንድ ጡብ እንኳ ሳይጐድል እንዲያስረክቡ አድርጉ፤ ‘ለአምላካችን መሥዋዕት እናቀርብ ዘንድ ልቀቀን!’ እያሉ የሚነዘንዙኝ ብዙ የሚሠሩት ነገር ስለሌለ ነው፤ 9ሐሰተኛ ወሬ የሚሰሙበት ጊዜ እንዳይኖራቸው፥ እነዚህ ሰዎች ከምንጊዜውም ይልቅ በሥራ እንዲጠመዱና በብርቱ እንዲሠሩ አድርጉአቸው።”
10ጨካኞች የሆኑት ግብጻውያን አሠሪዎችና የእስራኤላውያን ሠራተኞች አለቆች ሄደው ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ አሉ፤ “ንጉሡ ከእንግዲህ ወዲህ ገለባ እንዳይሰጣችሁ አዞአል፤ 11ራሳችሁ ሄዳችሁ ከየትም ስፍራ ፈልጋችሁ ማምጣት ይኖርባችኋል፤ ነገር ግን የምትሠሩት ጡብ ቊጥር ማነስ የለበትም።” 12ስለዚህ ሕዝቡ ገለባ ፈልገው ለማግኘት በመላይቱ የግብጽ ምድር ተሰማሩ። 13ጨካኞች የሆኑትም አሠሪዎች ቀድሞ ገለባ እየሰጡአቸው ይሠሩት የነበረውን ያኽል ጡብ ቈጥረው እንዲያስረክቡ ያስገድዱአቸው ጀመር። 14እነዚህም ጨካኞች የሆኑት ግብጻውያን አሠሪዎች፥ የእስራኤላውያን ሠራተኞችን አለቆች “ቀድሞ ትሠሩት የነበረውን ያኽል ጡብ ሠርታችሁ የማታስረክቡት ስለምንድነው?” እያሉ ይገርፉአቸው ነበር።
15የእስራኤላውያን ሠራተኞች አለቆችም ወደ ንጉሡ ቀርበው “ንጉሥ ሆይ፥ በእኛ በአገልጋዮችህ ላይ እንዴት ይህን ሁሉ ነገር አደረግህብን? 16ምንም ገለባ ሳይሰጠን ጡብ እንድንሠራ ታዘናል፤ ከዚህም ጋር እነሆ፥ እየተገረፍን ነው፤ ስሕተቱ ግን የገዛ ሕዝብህ ነው እንጂ የእኛ አይደለም” ሲሉ አቤቱታቸውን አቀረቡ።
17ንጉሡም መልሶ “እናንተ ሥራ የማትወዱ ሰነፎች ናችሁ፤ በፍጹም ሰነፎች ናችሁ፤ ‘ሄደን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት እንድናቀርብ ልቀቀን’ እያላችሁ የምትጠይቁበትም ምክንያት ይኸው ነው፤ 18በሉ አሁንም ወደ ሥራችሁ ተመለሱ! ከቶ ገለባ አይሰጣችሁም፤ ነገር ግን ቀድሞ የምትሠሩትን ያኽል ጡብ እየሠራችሁ ማስረከብ ይኖርባችኋል!” አላቸው። 19የእስራኤላውያን ሠራተኞች አለቆች ቀድሞ የሚሠሩትን ያኽል ጡብ በየቀኑ መሥራት እንዳለባቸው በተረዱ ጊዜ በመከራ ላይ መውደቃቸውን ተገነዘቡ።
20ከንጉሡም ፊት እንደ ወጡ፥ እነርሱን በመጠባበቅ ላይ የነበሩትን ሙሴንና አሮንን አገኙአቸው፤ 21ሙሴንና አሮንንም “በንጉሡ በፈርዖንና በመኳንንቱ ዘንድ እጅግ እንድንጠላ በማድረጋችሁና በሰይፍ ይገድሉንም ዘንድ ምክንያት በመሆናችሁ፥ እግዚአብሔር ይይላችሁ፤ እርሱም ይፍረድባችሁ፤” አሉአቸው።
ሙሴ ወደ እግዚአብሔር ያቀረበው አቤቱታ
22ሙሴም እንደገና ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ እንዲህ አለ፤ “አምላክ ሆይ! በዚህ ሕዝብ ላይ ይህን ያኽል መከራ የምታደርስበት ስለምንድነው? እንዲህ ከሆነ እኔንስ ወደዚህ ስለምን ላክኸኝ? 23እኔ በአንተ ስም ለመናገር ወደ ንጉሡ መቅረብ ከጀመርኩበት ጊዜ አንሥቶ እርሱ በዚህ ሕዝብ ላይ የባሰ መከራ አምጥቶበታል፤ አንተም ይህን ሕዝብ ለመታደግ ከቶ አልፈቀድክም።”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ