የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፀአት 4:18-31

ኦሪት ዘፀአት 4:18-31 መቅካእኤ

ሙሴም ሄደ፥ ወደ አማቱ ወደ ይትሮ ተመለሰ፥ እርሱም፦ “እባክህን በግብጽ ወዳሉ ዘመዶቼ እንድመለስ እስካሁንም በሕይወት እንዳሉ ሄጄ እንዳይ ፍቀድልኝ” አለው። ይትሮም ሙሴን፦ “በሰላም ሂድ” አለው። ጌታም ሙሴን በምድያን፦ “ወደ ግብጽ ተመልሰህ ሂድ ነፍስህን የሚፈልጓት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና” አለው። ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፥ በአህያ ላይም አስቀመጣቸው፥ ወደ ግብጽም ምድር ተመለሰ፤ ሙሴም የእግዚአብሔርን በትር ይዞ ሄደ። ጌታም ሙሴን አለው፦ “ወደ ግብጽ ስትመለስ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራት ሁሉ ተመልከት በፈርዖንም ፊት ታደርጋቸዋለህ፤ እኔም ልቡን አጸናዋለሁ፥ ሕዝቡንም አይለቅቅም። ፈርዖንንም ትለዋለህ፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እስራኤል የበኩር ልጄ ነው፤ እንዲያገለግለኝ ልጄን ልቀቅ አልሁህ፤ አንተም ትለቅቀው ዘንድ እንቢ አልህ፤ እነሆ እኔ የበኩር ልጅህን እገድላለሁ።’” እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ በማደሪያው ስፍራ ጌታ ተገናኘው፥ ሊገድለውም ፈለገ። ፂፖራም ባልጩት ወሰደች፥ የልጇንም ሸለፈት ገረዘች፥ እግሩንም ነክታ፦ “አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ” አለች። ከእርሱም ፈቀቅ አለ። የዚያን ጊዜ፦ “ለግርዛቱ የደም ሙሽራ” አለች። ጌታም አሮንን፦ “ሙሴን ለመገናኘት ወደ ምድረ በዳ ሂድ” አለው፤ ሄዶም በእግዚአብሔር ተራራ ተገናኘው፥ ሳመውም። ሙሴም ለአሮን በእርሱ ዘንድ የላከውን የጌታን ቃል ሁሉ ያዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ነገረው። ሙሴና አሮንም ሄዱ የእስራኤልን ልጆች ሽማግሌዎችንም ሁሉ ሰበሰቡ። አሮንም ጌታ ለሙሴ የተናገረውን ቃላት ሁሉ ተናገረ፥ ተአምራቶቹንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፤ ጌታ የእስራኤልን ልጆች እንደተመለከተ ጭንቀታቸውንም እንዳየ በሰሙ ጊዜ፥ አጎነበሱ ሰገዱም።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}