የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መክብብ 7:1-29

መክብብ 7:1-29 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ከመ​ል​ካም ሽቱ መል​ካም ስም፥ ከመ​ወ​ለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻ​ላል። ወደ ግብዣ ቤትም ከመ​ሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻ​ላል፤ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያ​ውም የሆነ ይህን መል​ካም ነገር በልቡ ያኖ​ረ​ዋል። ከሣቅ ኀዘን ይሻ​ላል፥ ከፊት ኀዘን የተ​ነሣ ልብ ደስ ይሰ​ኛ​ልና። የጠ​ቢ​ባን ልብ በል​ቅሶ ቤት ነው፤ የሰ​ነ​ፎች ልብ ግን በደ​ስታ ቤት ነው። ለሰው የሰ​ነ​ፎ​ችን ዘፈን ከሚ​ሰማ ይልቅ የጠ​ቢ​ባ​ንን ተግ​ሣጽ መስ​ማት ይሻ​ለ​ዋል። ከድ​ስት በታች እን​ደ​ሚ​ቃ​ጠል እሾህ ድምፅ የሰ​ነፍ ሣቅ እን​ዲሁ ነው፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ግፍ ጠቢ​ብን ያሳ​ብ​ደ​ዋል፥ የል​ቡ​ንም ትዕ​ግ​ሥት ያጠ​ፋ​ዋል። የነ​ገር ፍጻሜ ከመ​ጀ​መ​ሪ​ያው ይሻ​ላል፤ ታጋ​ሽም ከልብ ትዕ​ቢ​ተኛ ይሻ​ላል። በመ​ን​ፈ​ስህ ለቍጣ ችኩል አት​ሁን፥ ቍጣ በሰ​ነ​ፎች ብብት ያር​ፋ​ልና። ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለ​ፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አት​ና​ገር፤ የዚ​ህን ነገር በጥ​በብ አት​ጠ​ይ​ቅ​ምና። ጥበብ ከር​ስት ጋር መል​ካም ነው፤ ፀሓ​ይ​ንም ለሚ​ያዩ ሰዎች ትር​ፍን ይሰ​ጣል። የጥ​በብ ጥላ ከብር ጥላ ይሻ​ላል፤ የጥ​በ​ብ​ንም ዕው​ቀት ማብ​ዛት ገን​ዘብ ላደ​ረ​ጋት ሕይ​ወ​ትን ትሰ​ጠ​ዋ​ለች። የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ሥራ ተመ​ል​ከት፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጠማማ ያደ​ረ​ገ​ውን ማን ሊያ​ቀ​ናው ይች​ላል? በመ​ል​ካም ቀን ደስ ይበ​ልህ ፤ በክ​ፉም ቀን ተመ​ል​ከት፤ ሰው ከእ​ርሱ በኋላ መር​ምሮ ምንም እን​ዳ​ያ​ገኝ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይህ​ንም ያንም እን​ደ​ዚያ ሠራ። ጻድቅ በጽ​ድቁ ሲጠፋ፥ ኃጥ​እም በክ​ፋቱ ሲኖር፥ ይህን ሁሉ በከ​ንቱ ዘመኔ አየሁ። እጅግ ጻድቅ አት​ሁን፥ እጅ​ግም ጠቢብ አት​ሁን፥ እን​ዳ​ት​በ​ድል። እጅግ ክፉ አት​ሁን፥ እል​ከ​ኛም አት​ሁን፥ ያለ ጊዜህ እን​ዳ​ት​ሞት። ይህን ብት​ይዝ ለአ​ንተ መል​ካም ነው፤ በዚ​ህም እጅ​ህን አታ​ር​ክስ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን የሚ​ፈራ ከሁሉ ይወ​ጣ​ልና። በከ​ተማ ከሚ​ኖሩ ዐሥር ገዢ​ዎች ይልቅ ጥበብ ጠቢ​ብን ትረ​ዳ​ዋ​ለች። በም​ድር ላይም መል​ካ​ምን የሚ​ሠራ ኀጢ​አ​ት​ንም የማ​ያ​ደ​ርግ ጻድቅ ሰው አይ​ገ​ኝ​ምና። አገ​ል​ጋ​ይህ ሲረ​ግ​ምህ እን​ዳ​ት​ሰማ በሚ​ጫ​ወ​ቱ​በት ቃል ሁሉ ልብ​ህን አት​ጣል። ብዙ ጊዜ ያበ​ሳ​ጭ​ሃ​ልና፤ በብዙ መን​ገ​ድም ልብ​ህን ያስ​ከ​ፋ​ታ​ልና፥ አንተ ደግሞ ሌሎ​ችን እንደ ረገ​ምህ ታው​ቃ​ለ​ህና። ይህን ሁሉ በጥ​በብ ፈተ​ንሁ፥ ጠቢ​ብም እሆ​ና​ለሁ አልሁ፥ እር​ስዋ ግን ከእኔ ራቀች። ርቃና እጅግ ጠልቃ ሳለች መር​ምሮ የሚ​ያ​ገ​ኛት ማን ነው? አው​ቅና እመ​ረ​ምር ዘንድ ጥበ​ብ​ንና የነ​ገ​ሩን ሁሉ መደ​ም​ደ​ሚያ እፈ​ልግ ዘንድ፥ የክ​ፉ​ዎ​ች​ንም ስን​ፍ​ናና ዕብ​ደት አውቅ ዘንድ እኔ በልቤ ዞርሁ። እኔም ከሞት ይልቅ የመ​ረ​ረች ነገ​ርን አገ​ኘሁ፤ እር​ስ​ዋም ልብዋ ወጥ​መ​ድና መረብ የሆነ፥ በእ​ጆ​ች​ዋም ማሰ​ሪያ ያላት ሴት ናት፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ፊት ደግ የሆነ ከእ​ርሷ ያመ​ል​ጣል። ኀጢ​አ​ተኛ ግን ይጠ​መ​ድ​ባ​ታል። እነሆ፥ ይህን ነገር አገ​ኘሁ ይላል ሰባ​ኪው፥ መደ​ም​ደ​ሚ​ያን ለማ​ግ​ኘት አን​ዲ​ቱን በአ​ን​ዲቱ ጨምሬ ወደ ነገሩ ሁሉ መደ​ም​ደ​ሚያ እደ​ርስ ዘንድ ብመ​ረ​ምር፥ ነፍሴ የፈ​ለ​ገ​ች​ውን አላ​ገ​ኘ​ሁም፤ ከሺህ ወን​ዶች አንድ አገ​ኘሁ፥ ከእ​ነ​ዚያ ሁሉ መካ​ከል ግን አን​ዲት ሴት አላ​ገ​ኘ​ሁም። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በጊ​ዜው ሰዎ​ችን ቅኖች አድ​ርጎ እንደ ሠራ​ቸው እነሆ፥ ይህን ብቻ አገ​ኘሁ፥ እነ​ርሱ ግን ብዙ ዕው​ቀ​ትን ይሻሉ።

መክብብ 7:1-29 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

መልካም ስም ከመልካም ሽቱ ይበልጣል፤ ከልደትም ቀን የሞት ቀን ይሻላል። ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ፣ ወደ ሐዘን ቤት መሄድ ይሻላል፤ ሞት የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፤ ሕያው የሆነም ይህን ልብ ማለት ይገባዋል። ሐዘን ከሣቅ ይሻላል፤ ያዘነ ፊት ለልብ መልካም ነውና። የጠቢባን ልብ በሐዘን ቤት ነው፤ የሞኞች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው። የሞኞችን መዝሙር ከመስማት፣ የጠቢባንን ሰዎች ተግሣጽ መስማት ይሻላል። የሰነፎች ሣቅ፣ ከድስት ሥር እንደሚንጣጣ የእሾኽ ማገዶ ነው፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ግፍ ጠቢብን ሞኝ ያደርጋል፤ ጕቦም ልብን ያበላሻል። የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል፤ ትዕግሥተኛም ከትዕቢተኛ ይሻላል። የሞኞች ቍጣ በዕቅፋቸው ውስጥ ስለሆነ፣ በመንፈስህ ለቍጣ አትቸኵል። አንተም፣ “ከእነዚህ ቀናት የቀድሞዎቹ ለምን ተሻሉ?” አትበል፤ እንዲህ ያሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ጠቢብነት አይደለምና። ጥበብ እንደ ርስት መልካም ነገር ነው፤ ጠቃሚነቱም ፀሓይን ለሚያዩ ሰዎች ነው። ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ጥበብም ጥላ ከለላ ነው፤ የዕውቀት ብልጫዋ ግን፣ ጥበብ የባለቤቷን ሕይወት መጠበቋ ነው። እግዚአብሔር ያደረገውን ተመልከት፤ እርሱ ያጣመመውን፣ ማን ሊያቃናው ይችላል? ጊዜው መልካም ሲሆን፣ ደስ ይበልህ፤ ጊዜው ክፉ ሲሆን ግን ይህን ዐስብ፤ እግዚአብሔር አንዱን እንዳደረገ፣ ሌላውንም አድርጓል፤ ስለዚህ ሰው ስለ ወደ ፊት ሁኔታው፣ ምንም ሊያውቅ አይችልም። በዚህ ከንቱ በሆነው ሕይወቴ እነዚህን ሁለቱን ነገሮች አይቻለሁ፤ ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ፣ ኀጥእም በክፋቱ ዕድሜው ሲረዝም። እጅግ ጻድቅ፣ እጅግም ጠቢብ አትሁን፤ ራስህን ለምን ታጠፋለህ? እጅግ ክፉ አትሁን፤ ሞኝም አትሁን፤ ለምንስ ያለ ቀንህ ትሞታለህ? አንዱን ይዞ ሌላውንም አለመልቀቅ መልካም ነው፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ጽንፈኝነትን ያስወግዳል። በአንድ ከተማ ካሉ ዐሥር ገዦች ይልቅ፣ ጥበብ ጠቢቡን ሰው ኀያል ታደርገዋለች። ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኀጢአት የማይሠራ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም። የሚነገረውን ቃል ሁሉ ለማዳመጥ አትሞክር፤ አለዚያ አገልጋይህ ሲረግምህ ትሰማ ይሆናል፤ ብዙ ጊዜ አንተ ራስህ፣ ሌሎችን እንደ ረገምህ ልብህ ያውቃልና። እኔም ይህን ሁሉ በጥበብ ፈትኜ፣ “ጠቢብ ለመሆን ቈርጫለሁ” አልሁ፤ ይህ ግን ከእኔ የራቀ ነበር። ጥበብ ምንም ይሁን ምን፣ እጅግ ጥልቅና ሩቅ ነው፤ ማንስ ሊደርስበት ይችላል? ስለዚህ ጥበብንና የነገሮችን አሠራር ለመመርመርና ለማጥናት፣ የክፋትን መጥፎነት፣ የሞኝነትንም እብደት ለማስተዋል፣ አእምሮዬን መለስሁ። ልቧ ወጥመድ፣ እጆቿም እግር ብረት የሆኑ፣ አሽክላ የሆነች፣ ከሞት የከፋችዋን ሴት አገኘሁ፤ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ከእጇ ያመልጣል፤ ኀጢአተኛውን ግን አጥምዳ ትይዘዋለች። ሰባኪው እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ መርምሬ ያገኘሁት ነገር ይህ ነው፤ “የነገሮችን ብልኀት መርምሮ ለማግኘት፣ አንዱን በአንዱ ላይ በመጨመር፣ ገና በመመርመር ላይ ሳለሁ፣ ግን ያላገኘሁት፣ ከሺሕ ወንዶች መካከል አንድ ቅን ሰው አገኘሁ፣ በእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ቅን ሴት አላገኘሁም። ይህን አንድ ነገር ብቻ አገኘሁ፤ እግዚአብሔር ሰውን ቅን አድርጎ መሥራቱን፣ ሰዎች ግን ውስብስብ ዘዴ ቀየሱ።”

መክብብ 7:1-29 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፥ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል። ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፥ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና። ከሳቅ ኀዘን ይሻላል፥ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና። የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት ነው፥ የሰነፎች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው። ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። ከድስት በታች እንደሚቃጠል እሾህ ድምፅ የሰነፍ ሳቅ እንዲሁ ነው፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል፥ ጉቦም ልቡን ያጠፋዋል። የነገር ፍጻሜ ከመጀመሪያው ይሻላል፥ ታጋሽም ከትዕቢተኛ ይሻላል። በነፍስህ ለቍጣ ችኩል አትሁን፥ ቍጣ በሰነፍ ብብት ያርፋልና። ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፥ የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና። ጥበብ ከርስት ጋር መልካም ነው፥ ፀሐይንም ለሚያዩ ሰዎች ትርፍን ይሰጣል። የጥበብ ጥላ እንደ ገንዘብ ጥላ ናትና፥ የእውቀትም ብልጫዋ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን እንድትሰጥ ነው። የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት፥ እርሱ ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል? በመልካም ቀን ደስ ይበልህ፥ በክፉም ቀን ተመልከት፥ ሰው ከእርሱ በኋላ መርምሮ ምንም እንዳያገኝ እግዚአብሔር ይህንም ያንም እንደዚያ ሠርቶአል። ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ ኀጥእም በክፋቱ እጅግ ዘመን ሲኖር፥ ይህን ሁሉ ከንቱ በሆነ ዘመኔ አየሁ። እጅግ ጻድቅ አትሁን፥ እጅግ ጠቢብም አትሁን፥ እንዳትጠፋ። እጅግ ክፉ አትሁን፥ እልከኛም አትሁን፥ ጊዜህ ሳይደርስ እንዳትሞት። እግዚአብሔርን የሚፈራ ከሁሉ ይወጣልና ይህን ብትይዝ ከዚያም ደግሞ እጅህን ባታርቅ መልካም ነው። በከተማ ከሚኖሩ ከአሥር ገዢዎች ይልቅ ጥበብ ጠቢብን ታበረታለች። በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ ኃጢአትንም የማያደርግ ጻድቅ አይገኝምና። ባሪያህ ሲረግምህ እንዳትሰማ በሚጫወቱበት ቃል ሁሉ ልብህን አትጣል፥ አንተ ደግሞ ሌሎችን እንደ ረገምህ ልብህ ያውቃልና። ይህን ሁሉ በጥበብ ፈተንሁ፥ ጠቢብ እሆናለሁ አልሁ፥ እርስዋ ግን ከእኔ ራቀች። የሆነው ራቀ እጅግም ጠለቀ፥ መርምሮ የሚያገኘውስ ማን ነው? አውቅና እመረምር ዘንድ፥ ጥበብንና የነገሩን ሁሉ መደምደሚያ እፈልግ ዘንድ፥ ኃጢአትም ስንፍና፥ ስንፍናም እብደት እንደ ሆነች አውቅ ዘንድ እኔ በልቤ ዞርሁ። እኔም ከሞት ይልቅ የመረረ ነገር መርምሬ አገኘሁ፥ እርስዋም ልብዋ ወጥመድና መርበብ የሆነ፥ እጆችዋም እግር ብረት የሆኑ ሴት ናት፥ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነ ከእርስዋ ያመልጣል፥ ኃጢአተኛ ግን ይጠመድባታል። አንዱን በአንዱ ላይ ጨምሬ ወደ ነገሩ ሁሉ መደምደሚያ እደርስ ዘንድ፥ እነሆ፥ ይህን ነገር አገኘሁ ይላል ሰባኪው፥ ነፍሴ እስከ ዛሬ ድረስ ትሻታለች፥ ነገር ግን አላገኘሁም፥ ከሺህ ወንዶች አንድ አገኘሁ፥ ከእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ሴት አላገኘሁም። እግዚአብሔር ሰዎችን ቅኖች አድርጎ እንደ ሠራቸው፥ እነሆ፥ ይህን ብቻ አገኘሁ፥ እነርሱ ግን ብዙ ብልሃትን ፈለጉ።

መክብብ 7:1-29 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ዋጋው ውድ ከሆነ ከመልካም ሽቶ መልካም ስም ይሻላል፤ ከልደትም ቀን የሞት ቀን ይሻላል። ሞት በሰው ሁሉ ላይ የሚደርስ መሆኑን እንዲገነዘቡ ስለሚያደርግ ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ይልቅ ወደ ለቅሶ ቤት መሄድ ይመረጣል። ፊትህን በሐዘን የሚያጠቁር ቢመስልም አእምሮህን የሚያበራ በመሆኑ ከሳቅ ይልቅ ሐዘን ይሻላል። ሁልጊዜ ስለ አስደሳች ነገር ብቻ የሚያስብ ሰው ሞኝ ነው፤ ብልኅ ግን የሞትንም ነገር ያስባል። የሞኞችን ዘፈን ከመስማት የጥበበኞችን ተግሣጽ መስማት ይሻላል። የሞኝ ሳቅ ከድስት ሥር እንደሚንጣጣ እሾኽ ስለ ሆነ ትርጒም የሌለው ከንቱ ነገር ነው። ግፍን መፈጸም ጥበበኛን ሰው እንደ ሞኝ ያደርገዋል፤ ጉቦ መቀበልም መልካም ጠባይን ያበላሻል። ማናቸውም ነገር ከመጀመሪያው ይልቅ ፍጻሜው የተሻለ ነው፤ በትዕቢት ከሚናገር ሰው ይልቅ ትዕግሥተኛ ሰው ይሻላል። ቊጣ የሰነፎች ቂም በቀል መወጫ ስለ ሆነ የቊጡነት ስሜትህን ተቈጣጠር። እንዲህ ዐይነቱ ጥያቄ ከብልኅ ሰው የሚመነጭ ስላልሆነ “ከአሁኑ ዘመን ይልቅ በጥንት ዘመን የተደረጉት ነገሮች ሁሉ እንዴት እጅግ የተሻሉ ናቸው?” ብለህ አትጠይቅ፤ ጥበብን ማግኘት ርስትን ከመውረስ የተሻለ ስለ ሆነ በዚህ ዓለም የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ጠቢባን መሆን ይገባቸዋል፤ ጥበብ እንደ ገንዘብ ከለላ ነች፤ ከዚያም በላይ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን ትጠብቃለች። እስቲ የእግዚአብሔርን አሠራር አስተውል፤ እግዚአብሔር ያላቃናውን ማን ሊያቃናው ይችላል? ጊዜው መልካም ሲሆን ደስ ይበልህ፤ ጊዜውም ክፉ ሲሆን አስተውል፤ ይህንንም ያንንም ያደረገ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ ሰው ማንኛውንም የወደፊት ሁናቴውን ሊያውቅ አይችልም። ከንቱ በሆነው ዘመኔ ክፉ ሰው በሚሠራው በደል እስከ ረጅም ዕድሜ ሲኖር፥ ደግ ሰው ግን በደግነቱ ሲጠፋ ብዙ ነገር አይቼበታለሁ፤ ስለዚህ እንዳትጠፋ እጅግም ጠቢብ፥ እጅግም ደግ አትሁን። ያለ ጊዜህም በሞት እንዳትቀጭ እጅግ ክፉ ወይም ሞኝ አትሁን። ወደ ክፋት ወይም ወደ ደግነት ከመጠን በላይ ርቀህ አትሂድ፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ግን በሁሉም ነገር ይሳካለታል። በአንዲት ከተማ ከሚኖሩ ከዐሥር ገዥዎች ይበልጥ ጥበብ ለአስተዋይ ሰው ብርታትን ትሰጠዋለች። ምንም ስሕተት ሳይፈጽም ሁልጊዜ መልካም ነገርን የሚሠራ ደግ ሰው በምድር ላይ አይገኝም። ሰዎች የሚናገሩትን ሁሉ አዘውትረህ ለማጤን አትሞክር፤ አዘውትረህ የምታዳምጥ ከሆነ ግን የገዛ አገልጋይህ ሲሰድብህ ትሰማለህ። አንተም ራስህ ብትሆን ሁልጊዜ ሌሎችን ስትነቅፍ መኖርህን አትዘንጋ። ያለኝን ጥበብ ይህን ሁሉ ለመመርመር ተጠቀምኩበት፤ እጅግ ጥበበኛ ለመሆንም ወስኜ ነበር፤ ይሁን እንጂ ከዐቅሜ በላይ ሆነብኝ። እጅግ የጠለቀና ከባድ ስለ ሆነ ጥበብን መርምሮ ማወቅ የሚችል ማን ነው? ጥበብንና የነገሮችን ሁናቴ ለመረዳት፥ ለማጥናትና ለመመርመር አሰብኩ፤ ይህም ክፋት ሞኝነት መሆኑን፥ ሞኝነትም እብደት መሆኑን ወደማወቅ አደረሰኝ። ከሞት ይልቅ የመረረ ሌላም ነገር አገኘሁ፤ ይኸውም የሴት ወጥመድነት ነው፤ ሴት እንደ መረብ በሆነ ፍቅርዋ ወንዶችን ታጠምዳለች፤ እንደ እግር ብረት በሆኑ ክንዶችዋም ተጠምጥማ ለመያዝ ትፈልጋለች፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ብቻ ከእርስዋ ሸሽቶ ማምለጥ ይችላል፤ ኃጢአተኛውን ግን አጥምዳ ትይዘዋለች። ጥበበኛው እንዲህ አለ፦ “እነሆ፦ በተከታታይ መርምሬ ያገኘሁት ሌላ ነገር ደግሞ ይህ ነው፤ ይኸውም ሌላ መልስ ለማግኘት ፈልጌ ማጣቴ ነው፤ ከሺህ ወንዶች መካከል ልበ ቅን ሊባል የሚገባ አንድ ወንድ ብቻ አገኘሁ፤ ከሴቶች መካከል ግን አንዲት እንኳ ማግኘት አልቻልኩም። መርምሬ የደረስኩበት ሌላው ነገር እግዚአብሔር ሰዎችን ልበ ቅኖች አድርጎ ፈጥሮአቸዋል፤ እነርሱ ግን ተንኰልን ሁሉ ፈለሰፉ።”

መክብብ 7:1-29 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፥ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል። ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፥ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና። ከሳቅ ኀዘን ይሻላል፥ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና። የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት ነው፥ የአላዋቂዎች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው። ሰው የአላዋቂዎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። ከድስት በታች እንደሚቀጣጠል እሾህ ድምፅ የአላዋቂ ሳቅ እንዲሁ ነው፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል፥ ጉቦም ልቡን ያጠፋዋል። የነገር ፍጻሜ ከመጀመሪያው ይሻላል፥ ታጋሽም ከትዕቢተኛ ይሻላል። በነፍስህ ለቁጣ ችኩል አትሁን፥ ቁጣ በአላዋቂ ብብት ያርፋልና። ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፥ ይህንን ነገር የመትጠይቀው ክጥበብ ተነሥተህ አይደለምና። ጥበብ ከርስት ጋር መልካም ነው፥ ፀሐይንም ለሚያዩ ሰዎች ትርፍን ይሰጣል። የጥበብ ጥላ እንደ ገንዘብ ጥላ ናትና፥ የእውቀትም ብልጫዋ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን መስጠትዋ ነው። የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት፥ እርሱ ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል? በመልካም ቀን ደስ ይበልህ፥ በክፉም ቀን ተመልከት፥ ሰው ከእርሱ በኋላ መርምሮ ምንም እንዳያገኝ እግዚአብሔር ይህንንም ያንንም እንዲሁ ሠርቶአል። ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ ክፉም በክፋቱ ረጅም ዘመን ሲኖር፥ ይህን ሁሉ ከንቱ በሆነ ዘመኔ አየሁ። እጅግ ጻድቅ አትሁን፥ እጅግ ጠቢብም አትሁን፥ ለምን ራስህን ታጠፋለህ? እጅግ ክፉ አትሁን፥ አላዋቂም አትሁን፥ ጊዜህ ሳይደርስ ለምን ትሞታለህ? እግዚአብሔርን የሚፈራ በሁሉም ይዋጣለታልና ይህን ብትይዝ፥ ከዚያም ደግሞ እጅህን ባታርቅ መልካም ነው። በከተማ ከሚኖሩ ከዐሥር ገዢዎች ይልቅ ጥበብ ጠቢብን ታበረታለች። በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ፥ ምንም ኃጢአት የማያደርግ ጻድቅ አይገኝምና። አገልጋይህ ሲረግምህ እንዳትሰማ በሚጫወቱበት ቃል ሁሉ ልብህን አትጣል፥ አንተ ደግሞ ሌሎችን የረገምክበትን ጊዜ ልብህ ያውቃልና። ይህን ሁሉ በጥበብ ፈተንሁ፥ ጠቢብ እሆናለሁ አልሁ፥ እርሷ ግን ከእኔ ራቀች። የሆነው ነገር ራቀ፥ እጅግም ጠለቀ፥ መርምሮ የሚያገኘውስ ማን ነው? አውቅና እመረምር ዘንድ፥ ጥበብንና የነገሩን ሁሉ ትርጒም እፈልግ ዘንድ፥ ክፋትም አላዋቂነት፥ አላዋቂነትም እብደት እንደሆነ አውቅ ዘንድ እኔ በልቤ ዞርሁ። እኔም ከሞት ይልቅ የመረረ ነገር መርምሬ አገኘሁ፤ እርሷም ልብዋ ወጥመድና መረብ የሆነ፥ እጆችዋም እግር ብረት የሆኑ ሴት ናት፥ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነ ከእርሷ ያመልጣል፥ ኃጢአተኛ ግን ይጠመድባታል። አንዱን በአንዱ ላይ ጨምሬ ወደ ነገሩ ሁሉ ትርጒም እደርስ ዘንድ፥ እነሆ፥ ይህን ነገር አገኘሁ ይላል ሰባኪው፥ ነፍሴ እስከ ዛሬ ድረስ ትሻታለች፥ ነገር ግን አላገኘሁም፥ ከሺህ ወንዶች አንድ አገኘሁ፥ ከእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ሴት አላገኘሁም። እግዚአብሔር ሰዎችን ቅኖች አድርጎ እንደ ሠራቸው፥ እነሆ፥ ይህን ብቻ አገኘሁ፥ እነርሱ ግን ብዙ ብልሃትን ፈለጉ።