መጽሐፈ መክብብ 7
7
ስለ ሕይወት ማሰብ
1ዋጋው ውድ ከሆነ ከመልካም ሽቶ መልካም ስም ይሻላል፤ ከልደትም ቀን የሞት ቀን ይሻላል። #ምሳ. 22፥1።
2ሞት በሰው ሁሉ ላይ የሚደርስ መሆኑን እንዲገነዘቡ ስለሚያደርግ ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ይልቅ ወደ ለቅሶ ቤት መሄድ ይመረጣል።
3ፊትህን በሐዘን የሚያጠቁር ቢመስልም አእምሮህን የሚያበራ በመሆኑ ከሳቅ ይልቅ ሐዘን ይሻላል።
4ሁልጊዜ ስለ አስደሳች ነገር ብቻ የሚያስብ ሰው ሞኝ ነው፤ ብልኅ ግን የሞትንም ነገር ያስባል።
5የሞኞችን ዘፈን ከመስማት የጥበበኞችን ተግሣጽ መስማት ይሻላል።
6የሞኝ ሳቅ ከድስት ሥር እንደሚንጣጣ እሾኽ ስለ ሆነ ትርጒም የሌለው ከንቱ ነገር ነው።
7ግፍን መፈጸም ጥበበኛን ሰው እንደ ሞኝ ያደርገዋል፤ ጉቦ መቀበልም መልካም ጠባይን ያበላሻል።
8ማናቸውም ነገር ከመጀመሪያው ይልቅ ፍጻሜው የተሻለ ነው፤ በትዕቢት ከሚናገር ሰው ይልቅ ትዕግሥተኛ ሰው ይሻላል።
9ቊጣ የሰነፎች ቂም በቀል መወጫ ስለ ሆነ የቊጡነት ስሜትህን ተቈጣጠር። #ያዕ. 1፥19።
10እንዲህ ዐይነቱ ጥያቄ ከብልኅ ሰው የሚመነጭ ስላልሆነ “ከአሁኑ ዘመን ይልቅ በጥንት ዘመን የተደረጉት ነገሮች ሁሉ እንዴት እጅግ የተሻሉ ናቸው?” ብለህ አትጠይቅ፤
11ጥበብን ማግኘት ርስትን ከመውረስ የተሻለ ስለ ሆነ በዚህ ዓለም የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ጠቢባን መሆን ይገባቸዋል፤ 12ጥበብ እንደ ገንዘብ ከለላ ነች፤ ከዚያም በላይ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን ትጠብቃለች።
13እስቲ የእግዚአብሔርን አሠራር አስተውል፤ እግዚአብሔር ያላቃናውን ማን ሊያቃናው ይችላል? 14ጊዜው መልካም ሲሆን ደስ ይበልህ፤ ጊዜውም ክፉ ሲሆን አስተውል፤ ይህንንም ያንንም ያደረገ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ ሰው ማንኛውንም የወደፊት ሁናቴውን ሊያውቅ አይችልም።
15ከንቱ በሆነው ዘመኔ ክፉ ሰው በሚሠራው በደል እስከ ረጅም ዕድሜ ሲኖር፥ ደግ ሰው ግን በደግነቱ ሲጠፋ ብዙ ነገር አይቼበታለሁ፤ 16ስለዚህ እንዳትጠፋ እጅግም ጠቢብ፥ እጅግም ደግ አትሁን። 17ያለ ጊዜህም በሞት እንዳትቀጭ እጅግ ክፉ ወይም ሞኝ አትሁን። 18ወደ ክፋት ወይም ወደ ደግነት ከመጠን በላይ ርቀህ አትሂድ፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ግን በሁሉም ነገር ይሳካለታል።
19በአንዲት ከተማ ከሚኖሩ ከዐሥር ገዥዎች ይበልጥ ጥበብ ለአስተዋይ ሰው ብርታትን ትሰጠዋለች።
20ምንም ስሕተት ሳይፈጽም ሁልጊዜ መልካም ነገርን የሚሠራ ደግ ሰው በምድር ላይ አይገኝም።
21ሰዎች የሚናገሩትን ሁሉ አዘውትረህ ለማጤን አትሞክር፤ አዘውትረህ የምታዳምጥ ከሆነ ግን የገዛ አገልጋይህ ሲሰድብህ ትሰማለህ። 22አንተም ራስህ ብትሆን ሁልጊዜ ሌሎችን ስትነቅፍ መኖርህን አትዘንጋ።
23ያለኝን ጥበብ ይህን ሁሉ ለመመርመር ተጠቀምኩበት፤ እጅግ ጥበበኛ ለመሆንም ወስኜ ነበር፤ ይሁን እንጂ ከዐቅሜ በላይ ሆነብኝ። 24እጅግ የጠለቀና ከባድ ስለ ሆነ ጥበብን መርምሮ ማወቅ የሚችል ማን ነው? 25ጥበብንና የነገሮችን ሁናቴ ለመረዳት፥ ለማጥናትና ለመመርመር አሰብኩ፤ ይህም ክፋት ሞኝነት መሆኑን፥ ሞኝነትም እብደት መሆኑን ወደማወቅ አደረሰኝ።
26ከሞት ይልቅ የመረረ ሌላም ነገር አገኘሁ፤ ይኸውም የሴት ወጥመድነት ነው፤ ሴት እንደ መረብ በሆነ ፍቅርዋ ወንዶችን ታጠምዳለች፤ እንደ እግር ብረት በሆኑ ክንዶችዋም ተጠምጥማ ለመያዝ ትፈልጋለች፤ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ብቻ ከእርስዋ ሸሽቶ ማምለጥ ይችላል፤ ኃጢአተኛውን ግን አጥምዳ ትይዘዋለች። 27ጥበበኛው እንዲህ አለ፦ “እነሆ፦ በተከታታይ መርምሬ ያገኘሁት ሌላ ነገር ደግሞ ይህ ነው፤ 28ይኸውም ሌላ መልስ ለማግኘት ፈልጌ ማጣቴ ነው፤ ከሺህ ወንዶች መካከል ልበ ቅን ሊባል የሚገባ አንድ ወንድ ብቻ አገኘሁ፤ ከሴቶች መካከል ግን አንዲት እንኳ ማግኘት አልቻልኩም። 29መርምሬ የደረስኩበት ሌላው ነገር እግዚአብሔር ሰዎችን ልበ ቅኖች አድርጎ ፈጥሮአቸዋል፤ እነርሱ ግን ተንኰልን ሁሉ ፈለሰፉ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 7: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997