መጽሐፈ መክብብ 6
6
1በዚህ ዓለም በሰው ሁሉ ላይ የሚደርስ እጅግ የከፋ ነገር ተመለከትኩ። 2እግዚአብሔር ለሰው ምድራዊ ሀብትንና ብልጽግናን ክብርንም ሁሉ ይሰጠዋል፤ ከሚያስፈልገውም ነገር ሁሉ ምንም አያጐድልበትም፤ ይሁን እንጂ በሚሰጠው ሀብት ሁሉ አይደሰትበትም፤ ይልቁንም እርሱ ደክሞ ያፈራውን ሌላ ሰው ይደሰትበታል። ይህም ከንቱና እጅግ የከፋ በደል ነው። 3እንግዲህ፥ አንድ ሰው መቶ ልጆች ቢወልድ፥ ረጅም ዕድሜ አግኝቶ ብዙ ዘመን በሕይወት ቢኖርም፥ እንዲደሰትበት ከሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ድርሻውን ሳያገኝ ቀርቶ በመጨረሻም በክብር ለመቀበር ሳይበቃ ቢቀር፥ እኔ ስለ እርሱ አዝናለሁ፤ ከእንደዚህ ያለውም ሰው ይልቅ በእናቱ ማሕፀን ሞቶ የተወለደ ጭንጋፍ ይሻላል አልኩ። 4ያ ጭንጋፍ ተረስቶ ወደሚቀርበት ጨለማ ስለሚወሰድ ቀድሞውኑ ሳይወለድ ቢቀር በተሻለው ነበር። 5እርሱ የፀሐይን ብርሃን ሳያይ የሕይወትንም ምንነት ሳያውቅ አንድ ጊዜ ዐርፎአል። 6ስለዚህ ሁለት ሺህ ዓመት ያለ ደስታ ቢኖር ጥቅሙ ምንድን ነው? ዞሮ ዞሮ ሁለቱም የሚሄዱት ወደ አንድ ተመሳሳይ ስፍራ ነው።
7ሰው በሥራ መድከሙ የሚበላውን ነገር ለማግኘት ነበር፤ ይሁን እንጂ “በቃኝ!” ማለት አያውቅም። 8ታዲያ፥ ጥበበኛ ሰው ከሞኝ የሚሻልበት ምን ነገር አለ? ለድኻስ ሕይወትን ለመምራት መቻሉ የሚያተርፍለት ጥቅም ምንድን ነው? 9ለምኞት ከመገዛት ይልቅ ባለ ነገር መርካት ይሻላል፤ ይህም ደግሞ ከንቱና ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነው።
10ያለ ነገር ሁሉ ስም ተሰጥቶታል፤ የሰዎችም ማንነት ታውቆአል፤ ከእነርሱ በላይ ብርቱ ከሆነው ጋር መቋቋም አይችሉም። 11ብዙ በተናገርን መጠን ቁምነገሩ ያነሰ ነው፤ ስለዚህ የመናገር ጥቅሙ ምንድን ነው? 12ከንቱ ሆኖ እንደ ጥላ በሚያልፍ ዘመኑ ለሰው የሚበጀውን ነገር የሚያውቅ ማን ነው? ወይስ ከሞተ በኋላ በዚህ ዓለም ምን እንደሚሆን ለሰው ማን ሊነግረው ይችላል?
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 6: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997