የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መክብብ 7

7
1 # ምሳ. 22፥1። ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፥ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል። 2ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፥ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና። 3ከሳቅ ኀዘን ይሻላል፥ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና። 4የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት ነው፥ የአላዋቂዎች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው። 5ሰው የአላዋቂዎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። 6ከድስት በታች እንደሚቀጣጠል እሾህ ድምፅ የአላዋቂ ሳቅ እንዲሁ ነው፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 7ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል፥ ጉቦም ልቡን ያጠፋዋል። 8የነገር ፍጻሜ ከመጀመሪያው ይሻላል፥ ታጋሽም ከትዕቢተኛ ይሻላል። 9#ያዕ. 1፥19።በነፍስህ ለቁጣ ችኩል አትሁን፥ ቁጣ በአላዋቂ ብብት ያርፋልና።
10ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፥ ይህንን ነገር የመትጠይቀው ክጥበብ ተነሥተህ አይደለምና።
11ጥበብ ከርስት ጋር መልካም ነው፥ ፀሐይንም ለሚያዩ ሰዎች#7፥11 በሕይውት ለሚኖሩ ሰዎች። ትርፍን ይሰጣል። 12የጥበብ ጥላ እንደ ገንዘብ ጥላ ናትና፥ የእውቀትም ብልጫዋ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን መስጠትዋ ነው። 13የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት፥ እርሱ ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል? 14በመልካም ቀን ደስ ይበልህ፥ በክፉም ቀን ተመልከት፥ ሰው ከእርሱ በኋላ መርምሮ ምንም እንዳያገኝ እግዚአብሔር ይህንንም ያንንም እንዲሁ ሠርቶአል።
15ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ ክፉም በክፋቱ ረጅም ዘመን ሲኖር፥ ይህን ሁሉ ከንቱ በሆነ ዘመኔ አየሁ። 16እጅግ ጻድቅ አትሁን፥ እጅግ ጠቢብም አትሁን፥ ለምን ራስህን ታጠፋለህ? 17እጅግ ክፉ አትሁን፥ አላዋቂም አትሁን፥ ጊዜህ ሳይደርስ ለምን ትሞታለህ? 18እግዚአብሔርን የሚፈራ በሁሉም ይዋጣለታልና ይህን ብትይዝ፥ ከዚያም ደግሞ እጅህን ባታርቅ መልካም ነው።
19በከተማ ከሚኖሩ ከዐሥር ገዢዎች ይልቅ ጥበብ ጠቢብን ታበረታለች። 20በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ፥ ምንም ኃጢአት የማያደርግ ጻድቅ አይገኝምና። 21አገልጋይህ ሲረግምህ እንዳትሰማ በሚጫወቱበት ቃል ሁሉ ልብህን አትጣል፥ 22አንተ ደግሞ ሌሎችን የረገምክበትን ጊዜ ልብህ ያውቃልና።
23ይህን ሁሉ በጥበብ ፈተንሁ፥ ጠቢብ እሆናለሁ አልሁ፥ እርሷ ግን ከእኔ ራቀች። 24የሆነው ነገር ራቀ፥ እጅግም ጠለቀ፥ መርምሮ የሚያገኘውስ ማን ነው? 25አውቅና እመረምር ዘንድ፥ ጥበብንና የነገሩን ሁሉ ትርጒም እፈልግ ዘንድ፥ ክፋትም አላዋቂነት፥ አላዋቂነትም እብደት እንደሆነ አውቅ ዘንድ እኔ በልቤ ዞርሁ። 26እኔም ከሞት ይልቅ የመረረ ነገር መርምሬ አገኘሁ፤ እርሷም ልብዋ ወጥመድና መረብ የሆነ፥ እጆችዋም እግር ብረት የሆኑ ሴት ናት፥ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነ ከእርሷ ያመልጣል፥ ኃጢአተኛ ግን ይጠመድባታል። 27አንዱን በአንዱ ላይ ጨምሬ ወደ ነገሩ ሁሉ ትርጒም እደርስ ዘንድ፥ እነሆ፥ ይህን ነገር አገኘሁ ይላል ሰባኪው፥ 28ነፍሴ እስከ ዛሬ ድረስ ትሻታለች፥ ነገር ግን አላገኘሁም፥ ከሺህ ወንዶች#7፥28 ከብዙ። አንድ አገኘሁ፥ ከእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ሴት አላገኘሁም። 29እግዚአብሔር ሰዎችን ቅኖች አድርጎ እንደ ሠራቸው፥ እነሆ፥ ይህን ብቻ አገኘሁ፥ እነርሱ ግን ብዙ ብልሃትን ፈለጉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ