የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መክብብ 8

8
1ጠቢብን የሚመስለው? የነገሮችንስ ትርጒም የሚያውቅ ማን ነው? የሰው ጥበብ ፊቱን ታበራለች፥ የፊቱንም ድንዳኔ ትለውጣለች። 2እኔ፦ በመለኮታዊ መሐላ መሠረት የንጉሥን ትእዛዝ ጠብቅ እልሃለሁ። 3የወደደውን ሁሉ ያደርጋልና ከፊቱ ለመራቅ አትቸኩል፥ ክፉንም በማድረግ አትጽና። 4የንጉሥ ቃል ኃይለኛ ነውና፥ “ይህንስ ለምን ታደርጋለህ?” ማን ይለዋል? 5ትእዛዝን የሚጠብቅ ክፉ ነገር አይገጥመውም፥ የጠቢብም ልብ ጊዜንና ፍርድን ያውቃል። 6የሰው መከራ በእርሱ ላይ እጅግ ስለ ሆነ ለነገር ሁሉ ጊዜና ፍርድ አለውና። 7የሚሆነውንም አያውቅም፥ እንዴትስ እንደሚሆን የሚነግረው ማን ነው? 8መንፈስን ለማገድ በመንፈስ ላይ ሥልጣን ያለው ሰው የለም፥ በሞቱም ቀን ላይ ሥልጣን የለውም፥ በጦርነትም ውስጥ መሰናበቻ የለም፥ ክፋትም ሠሪውን አያድነውም። 9ይህን ሁሉ አየሁ፥ ከፀሐይም በታች ወደ ለተደረገው ሥራ ሁሉ ልቤን ሰጠሁ፥ ሰው ሰውን ለመጉዳት ገዢ የሚሆንበት ጊዜ አለ።
10እንዲሁም ክፉዎች ተቀብረው አየሁ፥ ነገር ግን ቅን አድራጊዎች ከቅድስት ስፍራ ወጡ፥ በከተማይቱም ውስጥ ተረሱ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 11በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይበየንምና በሰው ልጆች ልብ ውስጥ ክፉን መሥራት ጠነከረ። 12ኃጢአተኛ መቶ ጊዜ ክፉን ቢሠራ ዘመኑም ረጅም ቢሆን፥ እግዚአብሔርን ለሚፈሩት በፊቱም ለሚፈሩት መልካም እንደሚሆን አውቃለሁ፥ 13ለክፉ መልካም አይሆንም፤ በእግዚአብሔርም ፊት አይፈራምና ዘመኑ እንደ ጥላ አትረዝምም።
14በምድር የሚደረግ ከንቱ ነገር አለ፥ በክፉዎች ላይ የሚደረገው የሚደርስባቸው ጻድቃን አሉ፥ ለጻድቃንም የሚደረገው የሚደርስላቸው ክፉዎችም አሉ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። 15ከመብላትና ከመጠጣት፥ ደስም ከመሰኘት በቀር ለሰው ልጅ ከፀሐይ በታች ሌላ ምንም መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፥ ይህም እግዚአብሔር ከፀሐይም በታች በሰጠው በሕይወቱ ዘመን በድካሙ ከእርሱ ጋር ይኖራል።
16ጥበብን አውቅ ዘንድ፥ በምድር የሚሆነውንም ድካም አይ ዘንድ ልቤን በሰጠሁ ጊዜ፥ በቀንና በሌሊት እንቅልፍን በዓይኑ የማያይ አለና፥ 17የእግዚአብሔርንም ሥራ ሁሉ አየሁ፤ እርሱም ከፀሐይም በታች የተደረገውን ሥራ መርምሮ ሰው ማግኘት አለመቻሉን፥ ሰውም በመፈለግ እጅግ ቢደክምም መርምሮ አለማግኘቱን ነው፥ ደግሞም ጠቢብ ሰው አውቀዋለሁ ቢልም እንኳን ይህንን ለማግኘት አይችልም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ