የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መክብብ 9

9
1ጻድቃንና ጠቢባን፥ ሥራዎቻቸውም በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆኑ፥ ይህን ሁሉ እመረምር ዘንድ በልቤ አኖርሁ፥ ፍቅርም ሆነ ጥል ቢሆን ሰው አያውቅም፤ ሁሉም በፊታቸው ነው። 2የጻድቁና የበደለኛው፥ የመልካሙና የክፉው፥ የንጹሑና የርኩሱ፥ መሥዋዕትን የሚሠዋውና የማይሠዋው፥ የሰው ሁሉ ድርሻው አንድ ነው፤ መልካሙ ሰው እንደ ኃጢአተኛው፥ የሚምለው ሰው መሐላን እንደሚፈራው ነው። 3ለሁሉም አንድ ዓይነት ዕጣ ክፍል መኖሩ ከፀሐይ በታች በሚደረገው ነገር በሙሉ ይህ ክፉ ነው፥ ደግሞም የሰው ልጆች ልብ በክፋት ተሞልታለች፥ በሕይወታቸውም ሳሉ እብደት በልባቸው ውስጥ ይኖራል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሙታን ይወርዳሉ። 4ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና ሰው ከሕያዋን ሁሉ ጋር በአንድነት ቢኖር ተስፋ አለው። 5ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፥ ሙታን ግን አንዳችም ነገር አያውቁም፥ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። 6ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ከወዲሁ ጠፍቶአል፥ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘለዓለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም።
7እግዚአብሔር ሥራህን ተቀብሎታልና ሂድ፥ እንጀራህን በደስታ ብላ፥ የወይን ጠጅህንም በተድላ ጠጣ። 8ሁልጊዜ ልብስህ ነጭ ይሁን፥ ቅባትም ከራስህ ላይ አይታጣ። 9በሕይወትህ፥ አንተም ከፀሐይ በታች በምትደክምበት ድካም ይህ እድል ፈንታህ ነውና ከንቱ በሆነ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፥ ከፀሐይ በታች በሰጠህ፥ በከንቱ ዘመንህ ሁሉ፥ ከምትወድዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ። 10አንተ በምትሄድበት በሲኦል ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ አይገኙምና እጅህ ለማድረግ የምታገኘውን ሁሉ እንደ ኃይልህ አድርግ።
11እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ሩጫ ለፈጣኖች፥ ፍልምያ ለኃያላን፥ እንጀራም ለጠቢባን፥ ሀብትም ለአስተዋዮች፥ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ፥ ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል። 12ሰውም ጊዜውን አያውቅም፥ በክፉ መረብ እንደ ተጠመዱ ዓሣዎች፥ በወጥመድም እንደ ተያዙ ወፎች፥ እንዲሁ የሰው ልጆች በክፉ ጊዜ በድንገት ሲወድቅባቸው ይጠመዳሉ።
13ከፀሐይ በታችም ይህን ጥበብ አየሁ፥ እርሷም በእኔ ዘንድ ታላቅ መሰለችኝ። 14ታናሽ ከተማ ነበረች፥ ጥቂቶች ሰዎችም ነበሩባት፥ ታላቅ ንጉሥም መጣባት ከበባትም፥ ታላቅ ግንብም ሠራባት። 15ጠቢብ ድሀ ሰውም ተገኘባት፥ ያችንም ከተማ በጥበቡ አዳናት፥ ያን ድሀ ሰው ግን ማንም አላሰበውም። 16እኔም፦ ከኃይል ይልቅ ጥበብ ትበልጣለች፥ የድሀው ጥበብ ግን ተናቀች ቃሉም አልተሰማችም አልሁ።
17በሰነፎች መካከል ከሚጮኽ ከገዢው ጩኸት ይልቅ የጠቢባን ቃል በጸጥታ ትሰማለች። 18ከጦር መሣሪያዎች ይልቅ ጥበብ ትሻላለች፥ አንድ ኃጢአተኛ ግን ብዙ መልካምን ያጠፋል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ