የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መክብብ 7

7
1ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፥ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል። 2ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፥ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ በልቡ ያኖረዋልና። 3ከሳቅ ኀዘን ይሻላል፥ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና። 4የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት ነው፥ የሰነፎች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው። 5ሰው የሰነፎችን ዜማ ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። 6ከድስት በታች እንደሚቃጠል እሾህ ድምፅ የሰነፍ ሳቅ እንዲሁ ነው፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 7ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል፥ ጉቦም ልቡን ያጠፋዋል። 8የነገር ፍጻሜ ከመጀመሪያው ይሻላል፥ ታጋሽም ከትዕቢተኛ ይሻላል። 9በነፍስህ ለቍጣ ችኩል አትሁን፥ ቍጣ በሰነፍ ብብት ያርፋልና።
10ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፥ የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና።
11ጥበብ ከርስት ጋር መልካም ነው፥ ፀሐይንም ለሚያዩ ሰዎች ትርፍን ይሰጣል። 12የጥበብ ጥላ እንደ ገንዘብ ጥላ ናትና፥ የእውቀትም ብልጫዋ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን እንድትሰጥ ነው። 13የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት፥ እርሱ ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል? 14በመልካም ቀን ደስ ይበልህ፥ በክፉም ቀን ተመልከት፥ ሰው ከእርሱ በኋላ መርምሮ ምንም እንዳያገኝ እግዚአብሔር ይህንም ያንም እንደዚያ ሠርቶአል።
15ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ ኀጥእም በክፋቱ እጅግ ዘመን ሲኖር፥ ይህን ሁሉ ከንቱ በሆነ ዘመኔ አየሁ። 16እጅግ ጻድቅ አትሁን፥ እጅግ ጠቢብም አትሁን፥ እንዳትጠፋ። 17እጅግ ክፉ አትሁን፥ እልከኛም አትሁን፥ ጊዜህ ሳይደርስ እንዳትሞት። 18እግዚአብሔርን የሚፈራ ከሁሉ ይወጣልና ይህን ብትይዝ ከዚያም ደግሞ እጅህን ባታርቅ መልካም ነው።
19በከተማ ከሚኖሩ ከአሥር ገዢዎች ይልቅ ጥበብ ጠቢብን ታበረታለች። 20በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ ኃጢአትንም የማያደርግ ጻድቅ አይገኝምና። 21ባሪያህ ሲረግምህ እንዳትሰማ በሚጫወቱበት ቃል ሁሉ ልብህን አትጣል፥ 22አንተ ደግሞ ሌሎችን እንደ ረገምህ ልብህ ያውቃልና።
23ይህን ሁሉ በጥበብ ፈተንሁ፥ ጠቢብ እሆናለሁ አልሁ፥ እርስዋ ግን ከእኔ ራቀች። 24የሆነው ራቀ እጅግም ጠለቀ፥ መርምሮ የሚያገኘውስ ማን ነው? 25አውቅና እመረምር ዘንድ፥ ጥበብንና የነገሩን ሁሉ መደምደሚያ እፈልግ ዘንድ፥ ኃጢአትም ስንፍና፥ ስንፍናም እብደት እንደ ሆነች አውቅ ዘንድ እኔ በልቤ ዞርሁ። 26እኔም ከሞት ይልቅ የመረረ ነገር መርምሬ አገኘሁ፥ እርስዋም ልብዋ ወጥመድና መርበብ የሆነ፥ እጆችዋም እግር ብረት የሆኑ ሴት ናት፥ በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነ ከእርስዋ ያመልጣል፥ ኃጢአተኛ ግን ይጠመድባታል። 27አንዱን በአንዱ ላይ ጨምሬ ወደ ነገሩ ሁሉ መደምደሚያ እደርስ ዘንድ፥ እነሆ፥ ይህን ነገር አገኘሁ ይላል ሰባኪው፥ 28ነፍሴ እስከ ዛሬ ድረስ ትሻታለች፥ ነገር ግን አላገኘሁም፥ ከሺህ ወንዶች አንድ አገኘሁ፥ ከእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ሴት አላገኘሁም። 29እግዚአብሔር ሰዎችን ቅኖች አድርጎ እንደ ሠራቸው፥ እነሆ፥ ይህን ብቻ አገኘሁ፥ እነርሱ ግን ብዙ ብልሃትን ፈለጉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ