መጽሐፈ መክብብ 7
7
1ከመልካም ሽቱ መልካም ስም፥ ከመወለድ ቀንም የሞት ቀን ይሻላል። 2ወደ ግብዣ ቤትም ከመሄድ ወደ ልቅሶ ቤት መሄድ ይሻላል፤ እርሱ የሰው ሁሉ ፍጻሜ ነውና፥ ሕያውም የሆነ ይህን መልካም ነገር በልቡ ያኖረዋል። 3ከሣቅ ኀዘን ይሻላል፥ ከፊት ኀዘን የተነሣ ልብ ደስ ይሰኛልና። 4የጠቢባን ልብ በልቅሶ ቤት ነው፤ የሰነፎች ልብ ግን በደስታ ቤት ነው። 5ለሰው የሰነፎችን ዘፈን ከሚሰማ ይልቅ የጠቢባንን ተግሣጽ መስማት ይሻለዋል። 6ከድስት በታች እንደሚቃጠል እሾህ ድምፅ የሰነፍ ሣቅ እንዲሁ ነው፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 7ግፍ ጠቢብን ያሳብደዋል፥ የልቡንም ትዕግሥት ያጠፋዋል። 8የነገር ፍጻሜ ከመጀመሪያው ይሻላል፤ ታጋሽም ከልብ ትዕቢተኛ ይሻላል። 9በመንፈስህ ለቍጣ ችኩል አትሁን፥ ቍጣ በሰነፎች ብብት ያርፋልና።
10ከዚህ ዘመን ይልቅ ያለፈው ዘመን ለምን ተሻለ? ብለህ አትናገር፤ የዚህን ነገር በጥበብ አትጠይቅምና።
11ጥበብ ከርስት ጋር መልካም ነው፤ ፀሓይንም ለሚያዩ ሰዎች ትርፍን ይሰጣል። 12የጥበብ ጥላ ከብር ጥላ ይሻላል፤ የጥበብንም ዕውቀት ማብዛት ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን ትሰጠዋለች። 13የእግዚአብሔርን ሥራ ተመልከት፤ እግዚአብሔር ጠማማ ያደረገውን ማን ሊያቀናው ይችላል? 14በመልካም ቀን ደስ ይበልህ ፤ በክፉም ቀን ተመልከት፤ ሰው ከእርሱ በኋላ መርምሮ ምንም እንዳያገኝ እግዚአብሔር ይህንም ያንም እንደዚያ ሠራ።
15ጻድቅ በጽድቁ ሲጠፋ፥ ኃጥእም በክፋቱ ሲኖር፥ ይህን ሁሉ በከንቱ ዘመኔ አየሁ። 16እጅግ ጻድቅ አትሁን፥ እጅግም ጠቢብ አትሁን፥ እንዳትበድል። 17እጅግ ክፉ አትሁን፥ እልከኛም አትሁን፥ ያለ ጊዜህ እንዳትሞት። 18ይህን ብትይዝ ለአንተ መልካም ነው፤ በዚህም እጅህን አታርክስ፥ እግዚአብሔርን የሚፈራ ከሁሉ ይወጣልና።
19በከተማ ከሚኖሩ ዐሥር ገዢዎች ይልቅ ጥበብ ጠቢብን ትረዳዋለች። 20በምድር ላይም መልካምን የሚሠራ ኀጢአትንም የማያደርግ ጻድቅ ሰው አይገኝምና። 21አገልጋይህ ሲረግምህ እንዳትሰማ በሚጫወቱበት ቃል ሁሉ ልብህን አትጣል። 22ብዙ ጊዜ ያበሳጭሃልና፤ በብዙ መንገድም ልብህን ያስከፋታልና፥ አንተ ደግሞ ሌሎችን እንደ ረገምህ ታውቃለህና። 23ይህን ሁሉ በጥበብ ፈተንሁ፥ ጠቢብም እሆናለሁ አልሁ፥ እርስዋ ግን ከእኔ ራቀች። 24ርቃና እጅግ ጠልቃ ሳለች መርምሮ የሚያገኛት ማን ነው? 25አውቅና እመረምር ዘንድ ጥበብንና የነገሩን ሁሉ መደምደሚያ እፈልግ ዘንድ፥ የክፉዎችንም ስንፍናና ዕብደት አውቅ ዘንድ እኔ በልቤ ዞርሁ። 26እኔም ከሞት ይልቅ የመረረች ነገርን አገኘሁ፤ እርስዋም ልብዋ ወጥመድና መረብ የሆነ፥ በእጆችዋም ማሰሪያ ያላት ሴት ናት፤ በእግዚአብሔርም ፊት ደግ የሆነ ከእርሷ ያመልጣል። ኀጢአተኛ ግን ይጠመድባታል። 27እነሆ፥ ይህን ነገር አገኘሁ ይላል ሰባኪው፥ መደምደሚያን ለማግኘት አንዲቱን በአንዲቱ ጨምሬ ወደ ነገሩ ሁሉ መደምደሚያ እደርስ ዘንድ ብመረምር፥ 28ነፍሴ የፈለገችውን አላገኘሁም፤ ከሺህ ወንዶች አንድ አገኘሁ፥ ከእነዚያ ሁሉ መካከል ግን አንዲት ሴት አላገኘሁም። 29እግዚአብሔር በጊዜው ሰዎችን ቅኖች አድርጎ እንደ ሠራቸው እነሆ፥ ይህን ብቻ አገኘሁ፥ እነርሱ ግን ብዙ ዕውቀትን ይሻሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 7: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ