መጽሐፈ መክብብ 6
6
1ከፀሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ፥ እርሱም በሰው ላይ እጅግ የበዛ ነው። 2እግዚአብሔር ለሰው ሀብትንና ጥሪትን ክብርንም ሰጠው፥ ከወደደውም ሁሉ ለሰውነቱ የከለከላት የለም፤ ነገር ግን ሌላ ሰው ይበላዋል እንጂ ከእርሱ ይበላ ዘንድ እግዚአብሔር አላሠለጠነውም፤ ይህም ከንቱና ክፉ ደዌ ነው። 3ሰው መቶ ልጆች ቢወልድ፥ ብዙ ዘመንም በሕይወት ቢኖር፥ ዕድሜውም ብዙ ዓመት ቢሆን፥ ነገር ግን ነፍሱ መልካምን ባትጠግብ፥ መቃብርንም ባያገኝ፥ እኔ ስለ እርሱ፥ “ከእርሱ ይልቅ ጭንጋፍ ይሻላል” አልሁ። 4በከንቱ መጥቶአል፥ በጨለማም ይሄዳል፥ ስሙ በጨለማ ይሸፈናልና። 5ደግሞም ፀሐይን አላየም፥ አላወቀምም፤ ስለዚህ ከዚያ ይልቅ ለዚህ ዕረፍት አለው። 6ሺህ ዓመት ሁለት ጊዜ በሕይወት ቢኖር፥ መልካምንም ባያይ፥ ሁሉ ወደ አንድ ስፍራ የሚሄድ አይደለምን?
7የሰው ድካም ሁሉ በአፉ ነው፥ ነፍሱ ግን አትጠግብም። 8ከአላዋቂ ይልቅ ለጠቢብ ጥቅሙ ምንድር ነው? በሕያዋን ፊትስ መሄድን ለሚያውቅ ለድሃ ጥቅሙ ምንድር ነው? 9በዐይን ማየት በነፍስ ከመቅበዝበዝ ይሻላል፥ ይህ ደግሞ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
10የሆነው ሁሉ እነሆ፥ ስሙ አስቀድሞ ተጠራ፥ ሰውም እንደ ሆነ ታወቀ፤ ከእርሱም ከሚበረታው ጋር ይፋረድ ዘንድ አይችልም። 11ከንቱን የሚያበዛ ብዙ ነገር አለና፥ ለሰው ጥቅሙ ምንድር ነው? 12ሰው በከንቱ ወራቱ ቍጥርና እንደ ጥላ በሚያሳልፈው ዘመኑ በሕይወቱ ሳለ ለሰው የሚሻለውን የሚያውቅ ማን ነው? ወይስ ለሰው ከፀሓይ በታች ከእርሱ በኋላ የሚሆነውን ማን ይነግረዋል?
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 6: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ