መጽሐፈ መክብብ 5
5
እግዚአብሔርን ስለ መፍራት
1ወደ እግዚአብሔር ቤት በምትሄድበት ጊዜ እግርህን ጠብቅ፤#ምዕ. 5 ቍ. 1 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 4 ቍ. 17 ነው። የጠቢባንንም ትምህርት ለመስማት ቅረብ፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ለመስማትም በቀረብህ ጊዜ መሥዋዕትህ ከሰነፎች ስጦታ የተሻለ ይሁን እነርሱ ክፉ እንደሚያደርጉ አያውቁምና” ይላል። ዳግመኛም ከሰነፎች ስጦታ መሥዋዕት አድርገህ ከመቀበል ተጠበቅ፤ እነርሱ መልካም ለመሥራት ዐዋቂዎች አይደሉምና። 2እግዚአብሔር በሰማይ፥ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኩል፤ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ይሁን። 3ሕልም በብዙ መከራ፥ እንዲሁም የሰነፍ ቃል በብዙ ነገር ይመጣልና። 4ፈቃዱ አይደለምና#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሰነፎች ደስ አያሰኙትምና” ይላል። ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘግይ፤ አንተ ግን እንደ ተሳልህ ስእለትህን ስጥ። 5ተስለህ የማትፈጽም ከሆነ ባትሳል ይሻላል። 6ለሥጋህ በደል አፍህን አትስጥ፥ በእግዚአብሔርም#ዕብ. “በመልአክ” ይላል። ፊት፥ “ባለማወቅ ነው” አትበል፤ እግዚአብሔር ስለ ቃልህ እንዳይቈጣ፥ የእጅህንም ሥራ እንዳያጠፋብህ፤ 7ብዙ ሕልም፥ እንዲሁ ደግሞ ብዙ ቃል ከንቱ ነውና፤ አንተ ግን እግዚአብሔርን ፈጽመህ ፍራ።
ስለ ኑሮ ከንቱነት
8ከፍ ካለው በላይ ከፍ ያለ ይጠብቅሃልና፥ ከእነርሱም በላይ ደግሞ ሌሎች ከፍ ይላሉና በሀገሩ ድሃ ሲበደል፥ ፍርድና ጽድቅም ሲነጠቅ ብታይ በሥራው አታድንቅ። 9የምድር ጥቅም ለሁሉ ነው፥ የንጉሥም ጥቅም በእርሻ ነው። 10ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፤ ብዙ እህልንም የሚወድድ እንዲሁ ነው፤ ይህም ከንቱ ነው። 11ሀብት ሲበዛ የሚበሉት ይበዛሉ፤ በዐይኑም ከማየት በቀር ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል? 12ብዙ ወይም ጥቂት ቢበላ የአገልጋይ እንቅልፉ ጣፋጭ ነው፤ ብልጽግናን ያበዛ ሰውን ግን ይተኛ ዘንድ የሚተወው የለም።
13ከፀሓይ በታች ያየሁት ክፉ ደዌ አለ፤ ለመከራው በባለቤቱ ዘንድ የተቈጠበች ባለጠግነት ናት። 14ያችም ባለጠግነት በክፉ ንጥቂያ ትጠፋለች፤ ልጅንም ቢወልድ በእጁ ምንም የለውም። 15ከእናቱ ሆድ ራቁቱን እንደ ወጣ እንዲሁ እንደ መጣው ይመለሳል፤ ከጥረቱም በእጁ ሊወስድ የሚችለው ምንም የለም። 16ይህም ደግሞ የሚያሳዝን ክፉ ደዌ ነው፥ እንደ መጣ እንዲሁ ይሄዳልና፥ ለሰውነቱ ለሚደክም ሰው ትርፉ ምንድን ነው? 17ዘመኑ ሁሉ በጨለማ በልቅሶና በብዙ ብስጭት በደዌና በኀዘን ነውና።
18እነሆ፥ እኔ ያየሁት መልካምና የተዋበ ነገር፦ ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፥ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው፤ ይህ ዕድል ፈንታው ነውና። 19እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ባለጠግነትንና ሀብትን መስጠቱ፥ ከእርስዋም ይበላና ዕድል ፈንታውን ይወስድ ዘንድ፥ በድካሙም ደስ ይለው ዘንድ ማሠልጠኑ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። 20እግዚአብሔር በልቡ ደስታ ስለሚያደክመው እርሱ የሕይወቱን ዘመን ሁሉ እጅግ አያስብም።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 5: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ