መክብብ 4:4-8
መክብብ 4:4-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንዲሁም ጥረትና የሥራ መከናወን ሁሉ ሰው በባልንጀራው ላይ ካለው ቅናት እንደሚመነጭ ተመለከትሁ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። ሰነፍ እጁን አጣጥፎ ይቀመጣል፤ የገዛ ራሱንም ሥጋ ይበላል። በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት ዕፍኝ ይልቅ፣ በርጋታ የሚገኝ አንድ ዕፍኝ ይሻላል። ደግሞም ከፀሓይ በታች ከንቱ የሆነን ነገር አየሁ፤ ልጅም ሆነ ወንድም የሌለው፣ ብቸኛ ሰው አለ፤ ጥረቱ ማለቂያ የለውም፤ ዐይኑም ባለው ሀብት ገና አልረካም፤ እርሱም፣ “ለማን ብዬ ነው የምደክመው? ራሴን ከማስደሰትስ የምቈጠበው ለምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ፣ የጭንቅ ኑሮ ነው።
መክብብ 4:4-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ደግሞም የሰውን ድካምና የብልሃት ሥራውን ሁሉ ተመለከትሁ፥ በባልንጀራውም ዘንድ ቅንዓት እንዲያስነሣ አየሁ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። ሰነፍ እጆቹን ኮርትሞ ይቀመጣል፥ የገዛ ሥጋውንም ይበላል። በድካምና ነፋስን በመከተል ከሁለት እጅ ሙሉ ይልቅ አንድ እጅ ሙሉ በዕረፍት ይሻላል። እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ከንቱ ነገር አየሁ። አንድ ሰው ብቻውን አለ፥ ሁለተኛም የለውም፥ ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፥ ለድካሙ ግን መጨረሻ የለውም፥ ዓይኖቹም ከባለጠግነት አይጠግቡም። ለማን እደክማለሁ፥ ሰውነቴንስ መልካሙን ነገር ለምን እነፍጋታለሁ? ይላል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነገር ክፉም ጥረት ነው።
መክብብ 4:4-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እኔ ድካምን ሁሉና የብልሃት ሥራውን ተመለከትሁ፥ ለሰውም በባልንጀራው ዘንድ ቅንአትን እንዲያስነሣ አየሁ፤ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። ሰነፍ እጆቹን ኰርትሞ ይቀመጣል፥ የገዛ ሥጋውንም ይበላል። በድካምና ነፋስን በመከተል ከሁለት እጅ ሙሉ ይልቅ አንድ እጅ ሙሉ በዕረፍት ይሻላል። እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሓይ በታችም ከንቱ ነገርን አየሁ። አንድ ሰው ብቻውን አለ፥ ሁለተኛም የለውም፥ ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፤ ለድካሙ ግን መጨረሻ የለውም፥ ዐይኖቹም ከባለጠግነት አይጠግቡም። ለማን እደክማለሁ? ሰውነቴንስ ከደስታ ለምን እነፍጋታለሁ? ይላል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነገር፥ ክፉም ጥረት ነው።
መክብብ 4:4-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ደግሞም ሰዎች የተመኙትን ለማግኘት ተግተው በመሥራት ምን ያኽል እንደሚደክሙ ተመለከትኩ፤ ይህንንም የሚያደርጉት በባልንጀሮቻቸው ላይ በመቅናት መሆኑን ተረዳሁ፤ ይህም ሁሉ ከንቱ ስለ ሆነ ነፋስን ለመጨበጥ እንደ መሞከር ነው። እጆቹን አጥፎ የሚቀመጥ ሞኝ ሰው ራሱን በራብ ይገድላል። ነፋስን እንደ መጨበጥ ከሚቈጠር ላልተጨበጠ ሐሳብ ብዙ አገኛለሁ ብሎ ከመድከም ይልቅ ከኅሊና ዕረፍት ጋር ጥቂት ለማግኘት መሥራት ይሻላል። በዚህ ዓለም ያለውን ሌላውንም ከንቱ ነገር ተመለከትኩ፤ እነሆ፥ ብቻውን የሚኖር አንድ ሰው አለ፤ ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፤ ይሁን እንጂ ዘወትር በሥራ ከመድከም አይቦዝንም፤ ባገኘውም ሀብት በቃኝ ማለትን አላወቀም፤ “እርሱም የምደክመው ለማን ነው? ለራሴስ ደስታን የምነፍገው ለምንድን ነው?” ብሎ ራሱን ይጠይቃል፤ ይህ ሁሉ የባሰ ከንቱና የሥቃይ ሕይወት ነው።
መክብብ 4:4-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ደግሞም የሰውን ድካምና የብልሃት ሥራውን ሁሉ ተመለከትሁ፥ በባልንጀራም ዘንድ ቅንዓት እንደሚያስነሣ አየሁ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። አላዋቂ እጆቹን አጥፎ ይቀመጣል፥ የገዛ ሥጋውንም ይበላል። በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ፥ በእርጋታ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል። እንደገና፥ ከፀሐይ በታችም ከንቱ ነገር አየሁ። አንድ ሰው ብቻውን ይኖራል፥ ማንም አብሮት የለም፥ ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፥ ለድካሙም መጨረሻ የለውም፥ ዐይኖቹም ሳይቀሩ ሀብትን አይጠግቡም። እንግዲህ ለማን እደክማለሁ፥ ሰውነቴንስ መልካሙን ነገር ለምን እነፍጋታለሁ? ይላል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነገር ክፉም ጥረት ነው።