መጽሐፈ መክብብ 4
4
1እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፥ እነሆም፥ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፥ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፥ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፥ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም። 2እኔም እስከ ዛሬ በሕይወት ካሉት ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱትን አመሰገንሁ፥ 3ከእነዚህም ከሁለቱ ይልቅ ገና ያልተወለደው ከፀሐይም በታች የሚደረገውን ግፍ ያላየው ይሻላል።
4ደግሞም የሰውን ድካምና የብልሃት ሥራውን ሁሉ ተመለከትሁ፥ በባልንጀራውም ዘንድ ቅንዓት እንዲያስነሣ አየሁ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። 5ሰነፍ እጆቹን ኮርትሞ ይቀመጣል፥ የገዛ ሥጋውንም ይበላል። 6በድካምና ነፋስን በመከተል ከሁለት እጅ ሙሉ ይልቅ አንድ እጅ ሙሉ በዕረፍት ይሻላል።
7እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም ከንቱ ነገር አየሁ። 8አንድ ሰው ብቻውን አለ፥ ሁለተኛም የለውም፥ ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፥ ለድካሙ ግን መጨረሻ የለውም፥ ዓይኖቹም ከባለጠግነት አይጠግቡም። ለማን እደክማለሁ፥ ሰውነቴንስ መልካሙን ነገር ለምን እነፍጋታለሁ? ይላል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነገር ክፉም ጥረት ነው። 9ድካማቸው መልካም ዋጋ አለውና አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። 10ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋልና፥ አንዱ ብቻውን ሆኖ በወደቀ ጊዜ ግን የሚያነሣው ሁለተኛ የለውምና ወዮለት። 11ሁለቱም በአንድነት ቢተኙ ይሞቃቸዋል፥ አንድ ብቻውን ግን እንዴት ይሞቀዋል? 12አንዱም አንዱን ቢያሸንፍ ሁለቱ በፊቱ ይቆማሉ፥ በሦስትም የተገመደ ገመድ ፈጥኖ አይበጠስም።
13ድሀና ጠቢብ ብላቴና ተግሣጽን መቀበል ከእንግዲህ ወዲህ ከማያውቅ ከሰነፍ ሽማግሌ ንጉሥ ይሻላል። 14ምንም በመንግሥቱ አገር ደግሞ ችግረኛ ሆኖ ቢወለድ፥ ከግዞቱ ቤት ወደ መንግሥት ወጥቶአልና። 15ከፀሐይ በታች የሚሄዱትን ሕያዋን ሁሉ በእርሱ ፋንታ ከሚነሣው ከሌላው ጎበዝ ጋር ሆነው አየሁ። 16ከእርሱ በፊት የተገዙለት ሕዝብ ሁሉ አይቈጠሩም፥ በኋላ የሚመጡት ግን በእርሱ ደስ አይላቸውም። ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 4: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ