መጽሐፈ መክብብ 5
5
1ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ፥ ለመስማት መቅረብ ከሰነፎች መሥዋዕት ይበልጣልና፥ እነርሱም ክፉ እንዲያደርጉ አያውቁምና። 2እግዚአብሔር በሰማይ፥ አንተም በምድር ነህና በአፍህ አትፍጠን፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቃልን ይናገር ዘንድ ልብህ አይቸኵል፥ ስለዚህም ቃልህ ጥቂት ትሁን። 3ሕልም በሥራ ብዛት ይታያል፥ እንዲሁም የሰነፍ ድምፅ በቃሉ ብዛት ይሰማል። 4ሰነፎች ደስ አያሰኙትምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ትፈጽመው ዘንድ አትዘግይ፥ የተሳልኸውን ፈጽመው። 5ተስለህ የማትፈጽም ብትሆን ባትሳል ይሻላል። 6ሥጋህን በኃጢአት እንዳያስተው ለአፍህ አርነት አትስጥ፥ በመልአክም ፊት፦ ስሕተት ነበረ አትበል፥ እግዚአብሔር በቃልህ ይቈጣ ዘንድ የእጅህንም ሥራ ያጠፋ ዘንድ ስለምን ትሻለህ? 7ብዙ ሕልም ባለበት ዘንድ፥ እንዲሁም ደግሞ ብዙ ቃል ባለበት ስፍራ በዚያ ብዙ ከንቱ ነገር አለ፥ አንተ ግን እግዚአብሔርን ፍራ።
8ከፍ ካለው በላይ ከፍ ያለ ይመለከታልና፥ ከእነርሱም በላይ ደግሞ ሌሎች ከፍ ይላሉና በአገሩ ድሆች ሲገፉ፥ ፍርድና ጽድቅም ሲነጠቅ ባየህ ጊዜ በዚህ ነገር አታድንቅ። 9በጠቅላላው ግን የአገሩ ጥቅም እርሻን የሚወድድ ንጉሥ ቢኖር ነው።
10ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም፥ ባለጠግነትንም የሚወድድ ትርፉን አይጠግብም፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 11ሀብት ሲበዛ የሚበሉት ይበዛሉ፥ ሀብቱን በዓይኑ ብቻ ከማየት በቀር ለባለቤቱ ምን ይጠቅመዋል? 12እጅግ ወይም ጥቂት ቢበላ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው የባለጠጋ ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል።
13ከፀሐይ በታች የሚያሳዝን ክፉ ነገር አየሁ፥ ለመከራው በባለቤቱ ዘንድ የተቈጠበች ባለጠግነት ናት። 14ያችም ባለጠግነት በክፉ ነገር ትጠፋለች፥ ልጅንም ቢወልድ በእጁ ምንም የለውም። 15ከእናቱ ሆድ ራቁቱን እንደ ወጣ እንዲሁ እንደ መጣው ይመለሳል፥ ከጥረቱም በእጁ ሊወስድ የሚችለውን ምንም አያገኝም። 16ይህም ደግሞ የሚያሳዝን ክፉ ነገር ነው፥ እንደ መጣ እንዲሁ ይሄዳል፥ ድካሙም ለነፋስ ከሆነ ጥቅሙ ምንድር ነው? 17ዘመኑን ሁሉ በጨለማ በኀዘን በብስጭት በደዌና በቍጣ ነው።
18እነሆ፥ እኔ ያየሁት መልካምና የተዋበ ነገር ሰው እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፥ ከፀሐይ በታችም በሚደክምበት ድካም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው፥ ይህ እድል ፈንታው ነውና። 19እግዚአብሔር ለሰው ሁሉ ባለጠግነትንና ሀብትን መስጠቱ፥ ከእርስዋም ይበላና እድል ፈንታውን ይወስድ ዘንድ በድካሙም ደስ ይለው ዘንድ ማሠልጠኑ፥ ይህ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። 20እግዚአብሔር በልቡ ደስታን ስለ ሰጠው እርሱ የሕይወቱን ዘመን እጅግ አያስብም።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 5: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ