መጽሐፈ መክብብ 3
3
1ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። 2ለመወለድ ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፥ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፥ 3ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፥ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ 4ለመሥራትም ጊዜ አለው፥ ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፥ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፥ 5ድንጋይን ለመጣል ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፥ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፥ 6ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፥ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፥ 7ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፥ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፥ 8ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፥ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው። 9ለሠራተኛ የድካሙ ትርፍ ምንድር ነው?
10እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ የሰጣቸውን ጥረት አይቻለሁ። 11ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፥ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለምነትን በልቡ ሰጠው። 12ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። 13ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። 14እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለዘላለም እንዲኖር አወቅሁ፥ ሊጨመርበት ወይም ከእርሱ ሊጐድል አይቻልም፥ እግዚአብሔርም በፊቱ ይፈሩ ዘንድ አደረገ። 15አሁን ያለው በፊት ነበረ፥ የሚሆነውም በፊት ሆኖ ነበር፥ እግዚአብሔርም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል።
16ደግሞም ከፀሐይ በታች በፍርድ ስፍራ ኃጢአት፥ በጽድቅም ስፍራ ኃጢአት እንዳለ አየሁ። 17እኔም በልቤ፦ በዚያ ለነገር ሁሉና ለሥራ ሁሉ ጊዜ አለውና በጻድቅና በኃጢአተኛ ላይ እግዚአብሔር ይፈርዳል አልሁ። 18እኔ በልቤ ስለ ሰው ልጆች፦ እንደ እንስሳ መሆናቸውን እንዲያዩ እግዚአብሔር ይፈትናቸዋል አልሁ። 19የሰው ልጆችና የእንስሳ እድል ፈንታ አንድ ነው፥ ድርሻቸውም ትክክል ነው፥ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፥ የሁሉም እስትንፋስ አንድ ነው፥ ሁሉም ከንቱ ነውና ሰው ከእንስሳ ብልጫ የለውም። 20ሁሉ ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፥ ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል። 21የሰው ልጆች ነፍስ ወደ ላይ እንደምትወጣ የእንስሳም ነፍስ ወደ ታች ወደ ምድር እንደምትወርድ የሚያውቅ ማን ነው? 22ያም እድል ፈንታው ነውና ሰው በሥራው ደስ ከሚለው በቀር ሌላ መልካም ነገር እንደሌለው አየሁ፥ ከእርሱ በኋላስ የሚሆነውን ያይ ዘንድ የሚያመጣው ማን ነው?
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 3: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ