መጽሐፈ መክብብ 4
4
1እኔም ተመለስሁ፥ ከፀሐይ በታችም የሚደረገውን ግፍ ሁሉ አየሁ፥ እነሆም፥ የተገፉት ሰዎች እንባ፥ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፥ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፥ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም። 2እኔም እስከ ዛሬ በሕይወት ካሉት ይልቅ በቀድሞ ዘመን የሞቱትን አመሰገንሁ፥ 3ከእነዚህም ከሁለቱ ይልቅ ገና ያልተወለደው ከፀሐይም በታች የሚደረገውን ግፍ ያላየው ይሻላል።
4ደግሞም የሰውን ድካምና የብልሃት ሥራውን ሁሉ ተመለከትሁ፥ በባልንጀራም ዘንድ ቅንዓት እንደሚያስነሣ አየሁ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። 5አላዋቂ እጆቹን አጥፎ ይቀመጣል፥ የገዛ ሥጋውንም ይበላል። 6በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ፥ በእርጋታ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል።
7እንደገና፥ ከፀሐይ በታችም ከንቱ ነገር አየሁ። 8አንድ ሰው ብቻውን ይኖራል፥ ማንም አብሮት የለም፥ ልጅም ሆነ ወንድም የለውም፥ ለድካሙም መጨረሻ የለውም፥ ዐይኖቹም ሳይቀሩ ሀብትን አይጠግቡም። እንግዲህ ለማን እደክማለሁ፥ ሰውነቴንስ መልካሙን ነገር ለምን እነፍጋታለሁ? ይላል። ይህም ደግሞ ከንቱ ነገር ክፉም ጥረት ነው። 9ድካማቸው መልካም ዋጋ አለውና አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል። 10ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋልና፥ አንዱ ብቻውን ሆኖ በወደቀ ጊዜ ግን የሚያነሣው ሁለተኛ የለውምና ወዮለት። 11ሁለቱም በአንድነት ቢተኙ ይሞቃቸዋል፥ አንድ ብቻውን ግን እንዴት ይሞቀዋል? 12አንዱም አንድን ሰው ቢያሸንፍ፥ ሁለቱ ግን ይቋቋሙታል፥ በሦስትም የተገመደ ገመድ በፍጥነት#4፥12 በቀላሉ። አይበጠስም።
13ድኀና ጠቢብ ወጣት ተግሣጽን መቀበል ካቃተው አላዋቂ ሽማግሌ ንጉሥ ይሻላል። 14ምንም እንኳን ችግረኛ ሆኖ ቢወለድ፥ ከእስር ቤት ለመንገሥ ወጥቶአልና። 15ከፀሐይ በታች የሚሄዱት ሕያዋን በሙሉ እርሱን የተካውን ወጣት ሲከተሉ አየሁ። 16ከእርሱ በፊት የተገዙለት ሕዝብ ሁሉ ስፍር ቍጥር አልነበራቸውም፥ በኋላ የሚመጡት ግን በእርሱ ደስ አይላቸውም። ይህም ደግሞ ከንቱ፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። 17ወደ እግዚአብሔር ቤት በገባህ ጊዜ እግርህን ጠብቅ፥ ለመስማት መቅረብ ከአላዋቂዎች መሥዋዕት ይበልጣልና፥ እነርሱም ክፉ እንደሚያደርጉ አያውቁምና።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 4: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ