መጽሐፈ መክብብ 3
3
1ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከሰማይ በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። 2ለልደት ጊዜ አለው፥ ለሞትም ጊዜ አለው፥ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው፥ 3ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፥ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመገንባትም ጊዜ አለው፥ 4ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሳቅም ጊዜ አለው፥ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው፥ 5ድንጋይን ለመበተን ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፥ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፥ 6ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፥ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፥ 7ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፥ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፥ 8ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፥ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው። 9ለሠራተኛ የድካሙ ትርፍ ምንድነው?
10እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ የሰጣቸውን ጥረት አይቻለሁ። 11ነገርን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘላለማዊነትን#3፥11 ሊደረስበት የማይቻል ምሥጢርን ወይም ዓለምን። በልቡ ሰጠው። 12ሰው ደስ ከሚሰኝበትና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚፈጽምበት በቀር ሌላ መልካም ነገር እንደሌለ አወቅሁ። 13ደግሞም የእግዚአብሔር ስጦታ ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ ነው። 14እግዚአብሔር የሚያደርገው ሁሉ ለዘለዓለም እንደሚኖር አወቅሁ፥ ምንም የሚጨመርበት ወይም የሚቀነስለት የለም፥ እግዚአብሔርም ሰዎች ይፈሩ ዘንድ አደረገ። 15አሁን ያለው በፊት ነበረ፥ የሚሆነውም በፊት ሆኖ ነበር፥ እግዚአብሔርም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል።
16ደግሞም ከፀሐይ በታች በፍርድ ስፍራ ክፋት፥ በጽድቅም ስፍራ ክፋት እንዳለ አየሁ። 17እኔም በልቤ፦ ለማንኛውም ነገርና ለማንኛውም ሥራ ጊዜ አለውና በጻድቅና በክፉ ላይ እግዚአብሔር ይፈርዳል አልሁ። 18እኔ በልቤ ስለ ሰው ልጆች፦ እንደ እንስሳ መሆናቸውን#3፥18 ፍርድናና ጽድቅን በማጉደላቸው። እንዲያዩ እግዚአብሔር ይፈትናቸዋል አልሁ። 19የሰው ልጆችና የእንስሳ እድል ፈንታ አንድ ነው፥ አንድ ዓይነት መጨረሻ ይገጥማቸዋል፤ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፥ የሁሉም እስትንፋስ አንድ ነው፥ ሁሉም ከንቱ ነውና ሰው ከእንስሳ ብልጫ የለውም። 20ሁሉ ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፥ ሁሉም ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል። 21የሰው ልጆች መንፈስ ወደ ላይ እንደሚወጣ የእንስሳም ነፍስ ወደ ታች ወደ ምድር እንደምትወርድ የሚያውቅ ማን ነው? 22ያም እድል ፈንታው ነውና ሰው በሥራው ደስ ከሚሰኝበት ነገር በቀር ሌላ መልካም ነገር እንደሌለው አየሁ፥ ከእርሱ በኋላስ የሚሆነውንስ ወስዶ ማን ያሳየዋል?
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 3: መቅካእኤ
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ