ሐዋርያት ሥራ 12:6-16
ሐዋርያት ሥራ 12:6-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሄሮድስም ማለዳ ያቀርበው ዘንድ በወደደባት በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ ሁለቱን እጆቹን በሰንሰለት ታስሮ በሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም የወኅኒ ቤቱን በር ይጠብቁ ነበር። የእግዚአብሔርም መልአክ ወርዶ በአጠገቡ ቆመ፤ በቤትም ውስጥ ብርሃን ሆነ፤ ጴጥሮስንም ጎኑን ነክቶ ቀሰቀሰውና፥ “ፈጥነህ ተነሥ” አለው፥ ሰንሰለቶቹም ከእጆቹ ወልቀው ወደቁ። መልአኩም፥ “ወገብህን ታጠቅ፥ ጫማህንም ተጫማ” አለው፤ እንደ አዘዘውም አደረገ፤ “ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ” አለው። ተከትሎትም ወጣ፤ ጴጥሮስ ግን ራእይ የሚያይ ይመስለው ነበረ እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ሆነ አላወቀም ነበር። መጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደምትወስደው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ ያንጊዜም መዝጊያው ራሱ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም በአንድ ስላች መንገድ ሄዱ፤ መልአኩም ጴጥሮስን ትቶት ሄደ። ያንጊዜም የጴጥሮስ ልቡና ተመለሰለትና፥ “እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ በእውነት አሁን ዐወቅሁ” አለ። ከዚህም በኋላ በአስተዋለ ጊዜ ብዙዎች ወንድሞች ተሰብስበው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ። ጴጥሮስም በሩን አንኳኳ፤ ሮዴ የምትባል ብላቴናም ልትከፍትለት መጣች። የጴጥሮስም ድምፅ መሆኑን ዐውቃ ከደስታ የተነሣ አልከፈተችለትም፤ ነገር ግን ጴጥሮስ በበር ቆሞ ሳለ ሮጣ ነገረቻቸው። እነርሱም “አብደሻልን? አንድ ጊዜ ታገሺ” አሉአት፤ እርስዋ ግን እርሱ እንደ ሆነ ታረጋግጥ ነበር። እነርሱም፥ “ምናልባት መልአኩ ይሆናል” አሉ። ጴጥሮስ ግን በሩን ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ ከፍተውም ባዩት ጊዜ ተደነቁ።
ሐዋርያት ሥራ 12:6-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሄሮድስም ጴጥሮስን ሕዝቡ ፊት ሊያቀርበው አስቦ ሳለ፣ ጴጥሮስ በዚያው ሌሊት በሁለት ሰንሰለት ታስሮ፣ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ የወህኒ ቤት ጠባቂዎችም እስር ቤቱ በር ላይ ቆመው ነበር። የጌታ መልአክም ድንገት ታየ፤ በክፍሉም ውስጥ ብርሃን በራ፤ መልአኩም የጴጥሮስን ጐን መታ አድርጎ ቀሰቀሰውና፣ “ቶሎ ተነሣ!” አለው፤ በዚህ ጊዜ ሰንሰለቶቹ ከእጆቹ ወደቁ። መልአኩም፣ “ልብስህን ልበስ፤ ጫማህንም አድርግ” አለው። ጴጥሮስም እንደ ታዘዘው አደረገ። መልአኩም ቀጥሎ፣ “መደረቢያህን ከላይ ጣል አድርገህ ተከተለኝ” አለው። ጴጥሮስም ተከትሎት ከእስር ቤት ወጣ፤ ነገር ግን ራእይ የሚያይ መሰለው እንጂ መልአኩ የሚያደርገው ነገር በእውን መሆኑን አላወቀም ነበር። የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዘብ ዐልፈው ወደ ከተማዪቱ በሚወስደው መንገድ ላይ ወዳለው የብረት መዝጊያ ዘንድ ደረሱ። መዝጊያውም ራሱ ዐውቆ ተከፈተላቸው፤ እነርሱም ወጥተው ሄዱ፤ አንዲት ስላች መንገድ እንዳለፉም ወዲያው መልአኩ ተለየው። ጴጥሮስም ሲረጋጋ፣ “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና አይሁድ ካሰቡብኝ ሁሉ እንዳወጣኝ አሁን ያለ ጥርጥር ዐወቅሁ” አለ። ይህን ከተረዳ በኋላም፣ ብዙ ሰዎች ተሰብስበው በአንድነት ወደሚጸልዩበት፣ ማርቆስ ወደተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ። እዚያ ደርሶ የውጭውን በር ባንኳኳ ጊዜ፣ ሮዳ የተባለች አንዲት የቤት ሠራተኛ ማን እንደ ሆነ ለማጣራት ወደ በሩ ሄደች። የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ፣ በጣም ከመደሰቷ የተነሣ በሩን ሳትከፍት ሮጣ በመመለስ፣ ጴጥሮስ በሩ ላይ ቆሞ እንደሚገኝ ተናገረች። ሰዎቹም፣ “አብደሻል እንዴ!” አሏት፤ እርሷ ግን ይህንኑ ደጋግማ በነገረቻቸው ጊዜ፣ “እንግዲያውስ የእርሱ መልአክ ነው” አሉ። ጴጥሮስ ግን በር ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ እነርሱም በሩን ከፍተው ባዩት ጊዜ ተገረሙ።
ሐዋርያት ሥራ 12:6-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሄሮድስም ሊያወጣው ባሰበ ጊዜ፥ በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ በሁለት ሰንሰለት ታስሮ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ሆነው ወኅኒውን ይጠብቁ ነበር። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና፦ “ፈጥነህ ተነሣ” አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ። መልአኩም፦ “ታጠቅና ጫማህን አግባ” አለው፥ እንዲሁም አደረገ። “ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ” አለው። ወጥቶም ተከተለው፤ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ሆነ አላወቀም። የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም አውቆ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ። ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ፦ “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ” አለ። ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ። ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሉአት አንዲት ገረድ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤ የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሣ ደጁን አልከፈተችም፥ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች። እነርሱም፦ “አብደሻል” አሉአት። እርስዋ ግን እንዲሁ እንደ ሆነ ታስረግጥ ነበር። እነርሱም፦ “መልአኩ ነው” አሉ። ጴጥሮስ ግን ማንኳኳቱን አዘወተረ፤ ከፍተውም አዩትና ተገረሙ።
ሐዋርያት ሥራ 12:6-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሄሮድስ በማግስቱ ጴጥሮስን ለሕዝቡ ሊያቀርበው አስቦ ነበር፤ ጴጥሮስም በዚያች ሌሊት በሁለት ሰንሰለት ታስሮ በሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ሌሎች ወታደሮችም የወህኒ ቤቱን በር ይጠብቁ ነበር። በዚያን ጊዜ የጌታ መልአክ ተገልጦ ታየ፤ በወህኒ ቤቱም ውስጥ ብርሃን በራ፤ መልአኩ የጴጥሮስን ጐን መትቶ ቀሰቀሰውና “በፍጥነት ተነሥ!” አለው፤ ሰንሰለቶቹም ከእጆቹ ላይ ወደቁ። መልአኩም “ልብስህን ልበስ! ጫማህንም አድርግ!” አለው። ጴጥሮስ እንደታዘዘው አደረገ፤ መልአኩም “ነጠላህን ልበስና ተከተለኝ!” አለው። ጴጥሮስም ወጣና ተከተለው፤ ራእይ የሚያይ መሰለው እንጂ መልአኩ ያደረገው ነገር ሁሉ እውነት አልመሰለውም። አንደኛውንና ሁለተኛውን ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚወስደው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ። መዝጊያውም ሰው ሳይነካው እንዲሁ ተከፈተላቸውና ወጥተው በአንድ ስላች መንገድ አልፈው ሄዱ፤ በድንገትም መልአኩ ከጴጥሮስ ተለይቶ ሄደ። ጴጥሮስም ወደ ልቡናው ተመልሶ፥ “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠባበቁት ከነበረው ነገር ሁሉ ያዳነኝ መሆኑን አሁን ገና በእውነት ዐወቅሁ!” አለ። ይህን ካረጋገጠ በኋላ ብዙ ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው ወደሚጸልዩበት ወደ ማርያም ቤት ሄደ፤ ይህችም ማርያም ማርቆስ የተባለው የዮሐንስ እናት ነበረች። ጴጥሮስ እዚያ ደርሶ የውጪውን በር ባንኳኳ ጊዜ ሮዳ የምትባል አንዲት ገረድ ማን እንደ ሆነ ለማወቅ ወደ በሩ መጣች። የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑን ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ ብዛት የተነሣ በሩን ሳትከፍት ሮጣ ወደ ውስጥ ገባችና “ጴጥሮስ በበር ቆሞአል!” ስትል ተናገረች። እነርሱም “አብደሻል!” አሉአት። እርስዋ ግን “በእውነት እርሱ ነው!” ስትል አረጋገጠች፤ እነርሱም እንግዲያውስ “የእርሱ ጠባቂ መልአክ ይሆናል” አሉ። ጴጥሮስ ግን በር ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ እነርሱም በሩን ከፍተው ባዩት ጊዜ ተገረሙ።
ሐዋርያት ሥራ 12:6-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሄሮድስም ሊያወጣው ባሰበ ጊዜ፥ በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ በሁለት ሰንሰለት ታስሮ ከሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም በደጁ ፊት ሆነው ወኅኒውን ይጠብቁ ነበር። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ቀረበ፤ በቤትም ውስጥ ብርሃን በራ፤ ጴጥሮስንም ጎድኑን መትቶ አነቃውና “ፈጥነህ ተነሣ፤” አለው። ሰንሰለቶቹም ከእጁ ወደቁ። መልአኩም “ታጠቅና ጫማህን አግባ፤” አለው። እንዲሁም አደረገ። “ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ፤” አለው። ወጥቶም ተከተለው፤ ራእይንም የሚያይ ይመስለው ነበር እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደሆነ አላወቀም። የመጀመሪያውንና የሁለተኛውንም ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚያወጣው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ እርሱም ራሱ ዐውቆ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም አንዲት ስላች አለፉ፤ ወዲያውም መልአኩ ከእርሱ ተለየ። ጴጥሮስም ወደ ልቡ ተመልሶ “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ አሁን በእውነት አወቅሁ፤” አለ። ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ። ጴጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሉአት አንዲት ገረድ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤ የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሣ ደጁን አልከፈተችም፤ ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ጴጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች። እነርሱም “አብደሻል!” አሏት። እርሷ ግን እንዲሁ እንደሆነ ታስረግጥ ነበር። እነርሱም “መልአኩ ነው፤” አሉ። ጴጥሮስ ግን ማንኳኳቱን አዘወተረ፤ ከፍተውም አዩትና ተገረሙ።