የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 12:6-16

የሐዋርያት ሥራ 12:6-16 አማ05

ሄሮድስ በማግስቱ ጴጥሮስን ለሕዝቡ ሊያቀርበው አስቦ ነበር፤ ጴጥሮስም በዚያች ሌሊት በሁለት ሰንሰለት ታስሮ በሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ሌሎች ወታደሮችም የወህኒ ቤቱን በር ይጠብቁ ነበር። በዚያን ጊዜ የጌታ መልአክ ተገልጦ ታየ፤ በወህኒ ቤቱም ውስጥ ብርሃን በራ፤ መልአኩ የጴጥሮስን ጐን መትቶ ቀሰቀሰውና “በፍጥነት ተነሥ!” አለው፤ ሰንሰለቶቹም ከእጆቹ ላይ ወደቁ። መልአኩም “ልብስህን ልበስ! ጫማህንም አድርግ!” አለው። ጴጥሮስ እንደታዘዘው አደረገ፤ መልአኩም “ነጠላህን ልበስና ተከተለኝ!” አለው። ጴጥሮስም ወጣና ተከተለው፤ ራእይ የሚያይ መሰለው እንጂ መልአኩ ያደረገው ነገር ሁሉ እውነት አልመሰለውም። አንደኛውንና ሁለተኛውን ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚወስደው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ። መዝጊያውም ሰው ሳይነካው እንዲሁ ተከፈተላቸውና ወጥተው በአንድ ስላች መንገድ አልፈው ሄዱ፤ በድንገትም መልአኩ ከጴጥሮስ ተለይቶ ሄደ። ጴጥሮስም ወደ ልቡናው ተመልሶ፥ “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠባበቁት ከነበረው ነገር ሁሉ ያዳነኝ መሆኑን አሁን ገና በእውነት ዐወቅሁ!” አለ። ይህን ካረጋገጠ በኋላ ብዙ ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው ወደሚጸልዩበት ወደ ማርያም ቤት ሄደ፤ ይህችም ማርያም ማርቆስ የተባለው የዮሐንስ እናት ነበረች። ጴጥሮስ እዚያ ደርሶ የውጪውን በር ባንኳኳ ጊዜ ሮዳ የምትባል አንዲት ገረድ ማን እንደ ሆነ ለማወቅ ወደ በሩ መጣች። የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑን ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ ብዛት የተነሣ በሩን ሳትከፍት ሮጣ ወደ ውስጥ ገባችና “ጴጥሮስ በበር ቆሞአል!” ስትል ተናገረች። እነርሱም “አብደሻል!” አሉአት። እርስዋ ግን “በእውነት እርሱ ነው!” ስትል አረጋገጠች፤ እነርሱም እንግዲያውስ “የእርሱ ጠባቂ መልአክ ይሆናል” አሉ። ጴጥሮስ ግን በር ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ እነርሱም በሩን ከፍተው ባዩት ጊዜ ተገረሙ።