የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 12

12
በክርስቲያኖች ላይ የደረሰ ታላቅ ስደት
1በዚያን ዘመን ንጉሥ ሄሮድስ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ማሳደድ ጀመረ፤ 2የዮሐንስን ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ አስገደለው። 3ይህ ነገር አይሁድን ደስ እንዳሰኛቸው ባየ ጊዜ ጴጥሮስንም ደግሞ አስያዘው፤ ይህም የሆነው አይሁድ የቂጣ በዓልን በሚያከብሩባቸው ቀኖች ነበር። 4ጴጥሮስን ካስያዘ በኋላ ወደ ወህኒ ቤት አስገባው፤ ከአይሁድ የፋሲካ በዓል በኋላ ለሕዝቡ እስኪያቀርበው ድረስ አራት አራት ሆነው እንዲጠብቁት ለአራት ጭፍሮች አስረከበው። #ዘፀ. 12፥1-27። 5ስለዚህ ጴጥሮስ በወህኒ ቤት ተይዞ ይጠበቅ ነበር፤ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር በጥብቅ ትጸልይ ነበር።
መልአክ ጴጥሮስን ከእስር ቤት እንዳወጣው
6ሄሮድስ በማግስቱ ጴጥሮስን ለሕዝቡ ሊያቀርበው አስቦ ነበር፤ ጴጥሮስም በዚያች ሌሊት በሁለት ሰንሰለት ታስሮ በሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ሌሎች ወታደሮችም የወህኒ ቤቱን በር ይጠብቁ ነበር። 7በዚያን ጊዜ የጌታ መልአክ ተገልጦ ታየ፤ በወህኒ ቤቱም ውስጥ ብርሃን በራ፤ መልአኩ የጴጥሮስን ጐን መትቶ ቀሰቀሰውና “በፍጥነት ተነሥ!” አለው፤ ሰንሰለቶቹም ከእጆቹ ላይ ወደቁ። 8መልአኩም “ልብስህን ልበስ! ጫማህንም አድርግ!” አለው። ጴጥሮስ እንደታዘዘው አደረገ፤ መልአኩም “ነጠላህን ልበስና ተከተለኝ!” አለው። 9ጴጥሮስም ወጣና ተከተለው፤ ራእይ የሚያይ መሰለው እንጂ መልአኩ ያደረገው ነገር ሁሉ እውነት አልመሰለውም። 10አንደኛውንና ሁለተኛውን ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደሚወስደው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ። መዝጊያውም ሰው ሳይነካው እንዲሁ ተከፈተላቸውና ወጥተው በአንድ ስላች መንገድ አልፈው ሄዱ፤ በድንገትም መልአኩ ከጴጥሮስ ተለይቶ ሄደ።
11ጴጥሮስም ወደ ልቡናው ተመልሶ፥ “ጌታ መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠባበቁት ከነበረው ነገር ሁሉ ያዳነኝ መሆኑን አሁን ገና በእውነት ዐወቅሁ!” አለ።
12ይህን ካረጋገጠ በኋላ ብዙ ሰዎች በአንድነት ተሰብስበው ወደሚጸልዩበት ወደ ማርያም ቤት ሄደ፤ ይህችም ማርያም ማርቆስ የተባለው የዮሐንስ እናት ነበረች። 13ጴጥሮስ እዚያ ደርሶ የውጪውን በር ባንኳኳ ጊዜ ሮዳ የምትባል አንዲት ገረድ ማን እንደ ሆነ ለማወቅ ወደ በሩ መጣች። 14የጴጥሮስ ድምፅ መሆኑን ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ ብዛት የተነሣ በሩን ሳትከፍት ሮጣ ወደ ውስጥ ገባችና “ጴጥሮስ በበር ቆሞአል!” ስትል ተናገረች። 15እነርሱም “አብደሻል!” አሉአት። እርስዋ ግን “በእውነት እርሱ ነው!” ስትል አረጋገጠች፤ እነርሱም እንግዲያውስ “የእርሱ ጠባቂ መልአክ ይሆናል” አሉ።
16ጴጥሮስ ግን በር ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ እነርሱም በሩን ከፍተው ባዩት ጊዜ ተገረሙ። 17እርሱ ግን ዝም እንዲሉ በእጁ አመልክቶ ጌታ ከወህኒ ቤት እንዴት እንዳስወጣው አወራላቸውና “ይህን ነገር ለያዕቆብና ለቀሩት ምእመናን ንገሩ” አላቸው። ተለይቶአቸውም ወደ ሌላ ቦታ ሄደ።
18በነጋም ጊዜ ወታደሮቹ “ጴጥሮስ ምን ደርሶበት ይሆን?” በማለት እጅግ ታወኩ። 19ሄሮድስም በበኩሉ ጴጥሮስን አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ዘብ ጠባቂዎችን ከመረመረ በኋላ እንዲገደሉ አዘዘ፤ ከዚህም በኋላ ሄሮድስ ከይሁዳ ወደ ቂሳርያ ሄዶ እዚያ ተቀመጠ።
የሄሮድስ አሟሟት
20ሄሮድስ በጢሮስና በሲዶና ሰዎች ላይ በጣም ተቈጥቶ ነበር፤ እነርሱም በአንድነት መጡና፤ የንጉሥ ባለሟል ብላስጦስ እንዲተባበራቸው ለምነው እሺ ካሰኙትም በኋላ ንጉሡን ዕርቅ ጠየቁ፤ ይህንንም ያደረጉት አገራቸው ምግብ የምታገኘው ከንጉሡ ግዛት ስለ ነበረ ነው።
21በተቀጠረው ቀን ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለበሰና በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ለሕዝቡ ንግግር አደረገ። 22ሕዝቡም “ይህ የአምላክ ድምፅ ነው እንጂ የሰው ድምፅ አይደለም!” እያሉ ጮኹ። 23ሄሮድስ ለእግዚአብሔር ክብር ሳይሰጥ በመቅረቱ ወዲያውኑ የጌታ መልአክ ቀሠፈውና ተልቶ ሞተ።
24የእግዚአብሔር ቃል ግን ዘወትር እያደገና እየተስፋፋ ይሄድ ነበር። 25በርናባስና ሳውል አገልግሎታቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ተመለሱ፤ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስንም ከእነርሱ ጋር ይዘውት መጡ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ