የሐዋርያት ሥራ 12
12
በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የደረሰ ተጨማሪ ስደት
1በዚያም ወራት ሄሮድስ የቤተ ክርስቲያንን ሹሞች ያዛቸው፤ መከራም አጸናባቸው። 2የዮሐንስንም ወንድም ያዕቆብን በሰይፍ ገደለው። 3አይሁድንም ደስ እንዳላቸው አይቶ ጴጥሮስን ደግሞ ያዘው፤ ያንጊዜም የፋሲካ በዓል ነበር። 4#ዘፀ. 12፥1-27። ይዞም ወኅኒ ቤት አስገባው፤ ለሚጠብቁት ለዐሥራ ስድስቱ ወታደሮችም አሳልፎ ሰጠው፤ ከፋሲካም በኋላ ወደ ሕዝብ ሊያቀርበው ወድዶ ነበር። 5ጴጥሮስንም በወኅኒ ቤት ይጠብቁት ነበር፤ በቤተ ክርስቲያንም ዘወትር ስለ እርሱ ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩ ነበር።
መልአክ ጴጥሮስን ከወኅኒ ቤት እንደ አወጣው
6ሄሮድስም ማለዳ ያቀርበው ዘንድ በወደደባት በዚያች ሌሊት ጴጥሮስ ሁለቱን እጆቹን በሰንሰለት ታስሮ በሁለት ወታደሮች መካከል ተኝቶ ነበር፤ ጠባቂዎችም የወኅኒ ቤቱን በር ይጠብቁ ነበር። 7የእግዚአብሔርም መልአክ ወርዶ በአጠገቡ ቆመ፤ በቤትም ውስጥ ብርሃን ሆነ፤ ጴጥሮስንም ጎኑን ነክቶ ቀሰቀሰውና፥ “ፈጥነህ ተነሥ” አለው፥ ሰንሰለቶቹም ከእጆቹ ወልቀው ወደቁ። 8መልአኩም፥ “ወገብህን ታጠቅ፥ ጫማህንም ተጫማ” አለው፤ እንደ አዘዘውም አደረገ፤ “ልብስህንም ልበስና ተከተለኝ” አለው። 9ተከትሎትም ወጣ፤ ጴጥሮስ ግን ራእይ የሚያይ ይመስለው ነበረ እንጂ በመልአኩ የሚደረገው ነገር እውነት እንደ ሆነ አላወቀም ነበር። 10መጀመሪያውንና ሁለተኛውን ዘብ አልፈው ወደ ከተማ ወደምትወስደው ወደ ብረቱ መዝጊያ ደረሱ፤ ያንጊዜም መዝጊያው ራሱ ተከፈተላቸው፤ ወጥተውም በአንድ ስላች መንገድ ሄዱ፤ መልአኩም ጴጥሮስን ትቶት ሄደ። 11ያንጊዜም የጴጥሮስ ልቡና ተመለሰለትና፥ “እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ ከሄሮድስ እጅና የአይሁድ ሕዝብ ይጠብቁት ከነበረው ሁሉ እንደ አዳነኝ በእውነት አሁን ዐወቅሁ” አለ። 12ከዚህም በኋላ በአስተዋለ ጊዜ ብዙዎች ወንድሞች ተሰብስበው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት ሄደ። 13ጴጥሮስም በሩን አንኳኳ፤ ሮዴ የምትባል ብላቴናም ልትከፍትለት መጣች። 14የጴጥሮስም ድምፅ መሆኑን ዐውቃ ከደስታ የተነሣ አልከፈተችለትም፤ ነገር ግን ጴጥሮስ በበር ቆሞ ሳለ ሮጣ ነገረቻቸው። 15እነርሱም “አብደሻልን? አንድ ጊዜ ታገሺ”#“አንድ ጊዜ ታገሽ” የሚለው በግሪኩ የለም። አሉአት፤ እርስዋ ግን እርሱ እንደ ሆነ ታረጋግጥ ነበር። እነርሱም፥ “ምናልባት መልአኩ ይሆናል” አሉ። 16ጴጥሮስ ግን በሩን ማንኳኳቱን ቀጠለ፤ ከፍተውም ባዩት ጊዜ ተደነቁ። 17እርሱ ግን ዝም እንዲሉ በእጁ አመለከታቸው፤ ከወኅኒ ቤትም እግዚአብሔር እንደ አወጣው ነገራቸው፤ “ይህንም ለያዕቆብና ለወንድሞች ሁሉ ንገሩ” አላቸው፤ ከዚያም ወጥቶ ወደ ሌላ ስፍራ ሄደ።
18በነጋ ጊዜም ወታደሮች፥ “ጴጥሮስ ምን ሆነ?” ብለው ታወኩ። 19ሄሮድስ ግን አስፈልጎ ባጣው ጊዜ ጠባቂዎችን መረመረ፤ ይገድሉአቸውም ዘንድ አዘዘ፤ ከዚህም በኋላ ከይሁዳ ወደ ቂሳርያ ወርዶ በዚያ ተቀመጠ።
የሄሮድስ ሞት
20ሄሮድስም በጢሮስና በሲዶና ሰዎች ተቈጥቶ ነበር፤ በአንድነትም ወደ እርሱ መጥተው የንጉሡን ቢትወደድ በላስጦስን እንዲያስታርቃቸው ማለዱት፤ የሀገራቸው ምግብ ከንጉሥ ሄርድስ ነበርና። 21ከዚህም በኋላ አንድ ቀን ሄሮድስ ልብሰ መንግሥቱን ለብሶ፥ በአደባባይ ተገኝቶ ይፈርድ ጀመረ። 22ሕዝቡም፥ “የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ የሰው ቃልም አይደለም” እያሉ ጮኹ። 23ለእግዚአብሔርም ክብር ስለ አልሰጠ ያንጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቀሠፈው፤ ተልቶም ሞተ። 24የእግዚአብሔርም ቃል ከፍ አለ፤ በዛም። 25በርናባስና ሳውልም አገልግሎታቸውን ፈጽመው ከኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ማርቆስ የተባለውን ዮሐንስንም አስከትለውት መጡ።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 12: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ