2 ሳሙኤል 22:31-37
2 ሳሙኤል 22:31-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔርም ቃል የነጠረ ነው፤ ለሚታመኑበትም ሁሉ ጋሻ ነው፤ ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን አለና፤ ከአምላካችንስ በቀር ዐለት ማን ነው? ኀይልን የሚያስታጥቀኝ፣ መንገዴንም የሚያቀና እርሱ አምላኬ ነው። እግሮቼን እንደ ብሆር እግሮች ያበረታል፤ በከፍታዎችም ላይ አጽንቶ ያቆመኛል። እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፤ ክንዶቼም የናስ ቀስት ይገትራሉ። የማዳንህን ጋሻ ሰጥተኸኛል፤ ድጋፍህ ታላቅ አድርጎኛል። ርምጃዬን አሰፋህ፤ እግሮቼም አልተሰነካከሉም።
2 ሳሙኤል 22:31-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው፥ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፥ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው። ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችንስ በቀር አምባ ማን ነው? ኃይልን የሚያስታጥቀኝ፥ መንገዴንም የሚያቃና፥ እግሮቼን እንደ ብሆር እግሮች የሚያረታ፥ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው። እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል፥ በክንዴ የናስ ቀስት እገትራለሁ። የማዳንህንም ጋሻ ሰጠኸኝ፥ ተግሣጽህም አሳደገኝ። አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ እግሮቼም አልተንሸራተቱም።
2 ሳሙኤል 22:31-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የእግዚአብሔር መንገድ ፍጹም ነው፤ ቃሉ የጠራ ነው፤ እርሱን መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻቸው ነው። ከእግዚአብሔር በቀር ማን ነው አምላክ? ከእርሱስ በቀር መጠጊያ የሚሆን ማነው? ብርታትን የሚሰጠኝና መንገዴን የሚያቃናልኝ እግዚአብሔር ነው። እርሱ እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች ያጠነክራል፤ በከፍታ ቦታዎችም ያለ ሥጋት ለመቆም ያስችለኛል። እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፤ የነሐስን ቀስት መሳብ እንዲችሉ ክንዶቼን ያበረታል። አምላኬ ሆይ! የማዳን ጋሻህ ሰጠኸኝ፤ የአንተ ኀይልም ያጸናኛል። አረማመዴን አሰፋህ፤ እግሮቼም አልተንሸራተቱም።
2 ሳሙኤል 22:31-37 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የኀያል አምላክ መንገድ ንጹሕ ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል ጽኑዕ ነው፤ በእሳትም የጋለ ነው፤ በእርሱም ለሚታመኑት ጠባቂያቸው ነው። ከእግዚአብሔር በቀር ጽኑዕ ማን ነው? ከአምላካችንስ በቀር ፈጣሪ ማን ነው? በኀይል የሚያጸናኝ ኀያል እርሱ ነው፤ መንገዴንም ንጹሕ አድርጎ አዘጋጀ፤ እግሮቼን እንደ ዋልያ እግሮች አጸና፤ በኮረብቶችም አቆመኝ። ለእጆቼ ጦርነትን ያስተምራል፤ ለክንዴም የናስ ቀስት አዘዘ። የመድኀኒቴንም ጋሻ ሰጠኸኝ፤ መልስህም አበዛችኝ፤ በሜዳም አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፤ እግሮቼም አልተንሸራተቱም።
2 ሳሙኤል 22:31-37 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው፤ የጌታም ቃል የጠራ ነው፤ ለሚታመኑበትም ሁሉ ጋሻ ነው፤ ከጌታ በቀር አምላክ ማን ነው፤ ከአምላካችንስ በቀር ዓለት ማን ነው? ኃይልን የሚያስታጥቀኝ፥ መንገዴንም የሚያቀና እግዚአብሔር ነው። እግሮቼን እንደ ብሆር እግር ያበረታል፤ በከፍታዎችም ላይ አጽንቶ ያቆመኛል። ክንዶቼም የናስ ቀስት መሳብ እንዲችሉ፥ እጆቼን ለጦርነት ያሰለጥናል። የማዳንህን ጋሻ ሰጥተኸኛል፤ ምላሽህም ታላቅ አድርጎኛል። እርምጃዬን አሰፋህ፤ እግሮቼም አልተሰነካከሉም።